‹‹ጀግናን ማን ይዘክራል?›› ከተባለ ቀዳሚው መልስ የሚሆነው ኪነ ጥበብ ነው።የታሪክ መጽሐፎች ሁነቱን ያስቀምጣሉ ኪነ ጥበብ ወደ ድርጊት በቀረበ መንገድ ታሪኩን ያሳያል፤ ይዘክራል።ኪነ ጥበብ ሲባል የግድ ቴአትርና ፊልም፣ ዘፈንና ግጥም ብቻ አይደለም።በኪነ ጥበብ መድረኮች ላይ የሚደረጉ ንግግሮች በራሳቸው አነቃቂና ዘካሪ ይሆናሉ።ችግሩ ግን ጀግኖችን ለማሰብ ብቻ ተብሎ የሚዘጋጅ መድረክ አለመኖሩ ነው።ከኖረም ወቅት ጠብቅ የዓድዋ ወይም የሆነ የድል በዓል ጠብቅ በዓመት አንዴ ነው።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ‹‹ብሌን የስነ ጽሑፍ ምሽት›› በየወሩ ያካሂዳል።ባለፈው ሚያዝያ 1 ቀን የተካሄደው ወርሃዊ የስነ ጽሑፍ ምሽት ጀግኖችን የሚዘክር ነበር።በዝግጅቱ ላይም አባት አርበኞች፣ ሽማግሌዎች፣ ገጣሚያንና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።ምንም እንኳን የተባለውን ያህል ባይሆንም ጀግነነትን የሚያወሱ ሽለላና ፉከራም ቀርቧል።
ከመድረኩ ደባብ እንጀምር
መድረኩ ቀዝቀዝ ያለ ነበር።ቀዝቀዝ ያለ ያልኩበት ምክንያት ደግሞ እንዲህ ነው።የመድረክ ታዳሚ የሚጯጯህ ነገር ይወዳል።ያ አልነበረም።ያሉት አቅራቢዎች ሰከን ያሉና በዕድሜም ብዙ ያዩ ናቸው። መድረክ መሪውም በአዋቂነት የዕድሜ ደረጃ ላይ ስለሆኑ ቀዝቀዝ አድርገው ነው የሚናገሩት።እንዲህ አይነት መድረክ ደግሞ ለእውቀት እንጂ ለጭብጨባ አይሆንም።
በነገራችን ላይ መድረኩ ላይ የተበሳጨሁበትን አንድ ትልቅ ትዝብት ልንገራችሁ።አንዲት ስመጥር ገጣሚ ተጋብዛ ነበር።ግጥም እንድታነብ ወደ መድረክ ተጠራች።ግጥም ማንበብ ጀመረች።እኔ የግጥም ባለሙያ አይደለሁም፤ ዳሩ ግን ቢያንስ ከባድ ቅኔ ያለው ግጥም ይክበደኝ እንጂ ለሹፈት የተጻፈን እንቶፈንቶ ግጥም ማወቅ ደግሞ በጣም ቀላል ነው።ገና ግጥሙን ስትጀምረው ‹‹ውይ ይሄ ከእሷ ይጠበቅ ነበር?›› አልኩ።መጨረሻውን አይቼ ይሻላል ብዬ ስጠብቅ በቀልድ አለቀ።ለሹፈት እንደገጠመችው ደግሞ ራሷ ሳታስበው መሰከረች (አስባበትም ሊሆን ይችላል)።ግጥሙን እያነበበች በአንድ ጥግ በኩል ያሉ ሰዎች አጨበጨቡ።ስለእነዚህ አጨብጫቢዎችም ትንሽ ልበል።እውነት ለመናገር ከቀበሌ ተከፍሏቸው የመጡ ነበር የሚመስሉት።ምንም የማያስጨበጭብበት ቦታ ላይ ሁሉ ያጨበጭባሉ።ይሄ በየመድረኩ የተለመደ ነው እንዳትሉኝ፤ እሱን አውቃለሁ።ግን የእነዚህ ደግሞ ይለይ ነበር።ተናጋሪው ማይክ ሲሞክር ሁሉ ሊያጨበጭቡ ይችላሉ።
ወደነገሩ ስመልሳችሁ እያነበበች የሆነ ስንኝ ላይ አጨበጨቡ።ማንበቡን ተወት አድርጋ ‹‹በነገራችን ላይ አንዳንዱ ግጥም ጭብጨባ ላያስፈልገው ይችላል›› በማለት የሚያስጨበጭብና የማያስጨበጭብ ግጥም እየለያችሁ፤ ይሄን ለሹፈት ነው የጻፍኩት አይነት መልዕክት ተናገረች።
ይሄንን ባትል ኖሮ በግጥሙ ብቻ አልፈርድም ነበር፤ ምክንያቱም ግጥም ሁሌ አይዋጣም፤ ጥሩ ገጣሚ ነችና ሁሌም ጥሩ ትግጠም አይባልም።በዚያ ላይ ደግሞ ያ ግጥም ለሌላው ሰው የተዋጣለት የሚባል ቢሆንስ? ችግሩ ግን እያሾፈች እንደሆነ ነገረችን።
ይችን ገጠመኝ መነሻ አድርገን ወደጥበብ ቲፎዞዎች እንሂድ።አንዳንዶቹ ጥበብን ፍለጋ ከሚሄዱት በቲፎዞ የሚሄዱት ይበልጣል።ያ መድረክ የልጅቷ ቲፎዞዎች ያሉበት አይደለም።እምቢ ላለማለት ብላ እንደሄደች ያስታውቃል።
አድናቆታችንም በዚሁ ልክ ነው።በሥራው ጥበብነት ሳይሆን በአቅራቢው ማንነት ወይም እነማን አደነቁ
የሚለውን ተከትለን የምንሄደው ይበልጣል።ፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ኪነ ጥበብም የመንጋ ጋጋታ ሆኗል፤ ኪነ ጥበብ ደግሞ እንዲህ ሲሆን አያምርበትም።
መድረኩ በዋናነት ጀግኖችን የሚዘክር ነው።የሚቀርቡ የግጥም፣ የዘፈን፣ የመነባንብም ሆነ ሌሎች ንግግሮች ጀግኖችን የተመለከቱ ነበሩ።በመድረኩ ላይ ከተገኙት አንዱ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቡድን መሪ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በዕለቱ እንደተናገሩት የጀግኖችን ታሪክ ለልጆች ማስተማርና ማሳወቅ ይገባል።‹‹ለሚመጣው ትውልድ ምንድነው የምናስረክበው? የተከበረች ኢትዮጵያ ወይስ የተበታተነች ኢትዮጵያ?›› ሲሉም ይጠይቃሉ።ይሄን የአባቶችን በጀግንነት አገር የማቆየት ጥበብ ለትውልድ የሚያስተላልፈው ደራሲ ነው፣ ገጣሚ ነው፣ ዘፋኝ ነው፣ ሁሉም ጥበበኛ በጀግኖች ላይ መሥራት አለበት።ለዚህም መደራጀት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።የኪነ ጥበብ ሰዎችና ደራሲዎች መተባበርና በጋራ መሥራት አለባቸው።
አባት አርበኞች ያላቸውን ትዝታ እንዲናገሩ ዕድል መስጠት፣ መድረክ ማመቻቸትና ለወጣቱ ማስተማር ያስፈልጋል።የአሁኑ ወጣት ዘመኑ የሚፈልገውን ጀግንነት መላበስ አለበት።አገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ሆና ዳቦ የሚራብ ህዝብ ሲኖር ያለመሥራት ችግር ነው።ጀግንነት እልህ ብቻ አይደለም።ብዙ ጊዜ ግጥሞቻችን የእልህ ናቸው፤ የቁጭት ናቸው።የሥራና የተስፋ የጥበብ ሥራዎችም መኖር አለባቸው።
ከረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ሀሳብ ሳንርቅ እዚያው መድረክ ላይ ያስተዋልኩት አንድ ነገር ልንገራችሁ።እዚያው መድረክ ላይ ያልኩት ያንኑ አጋጣሚ ለመጠቀም እንጂ ነገሩስ የትም መድረክ ላይ የምታዘበው ነው።
አባት አርበኞች ዕድል አልተሰጣቸውም።አባት አርበኞች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሙያ ላይ ይሁኑ
አባቶች ዕድል አልተሰጣቸውም።በዕለቱ በኢትዮጵያ አየር ወለድ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ጄኔራል ተስፋዬ ኃይለማርያም ተጋባዥ ነበሩ።ብዙዎቹ ተናጋሪዎች የተናገሩት ከ15 ደቂቃ አይበልጥም።እኚህ አዛውንት ጄኔራል ግን ከ30 ደቂቃ በላይ ተናገሩ። ምክንያቱ ግልጽ ነው። አንድ የሚናገሩት ብዙ እምቅ እውቀት አላቸው፤ ሁለት የሚናገሩበት መድረክ ተመቻችቶላቸው አያውቅም፤ ያን ሁሉ የዕድሜ ዘመን እውቀታቸውንና ገጠመኛቸውን ለማን ይናገሩት? እንዲህ አይነት ዕድል በተገኘበት አጋጣሚ ነው የሚናገሩት።
ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ መድረክ ላይ በዕድሜ አንጋፋ የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ በጣም ይቆያሉ። በውስጣቸው ያለውን ነገር ማውጣት ያምራቸዋል።መድረክ ብቻ ሳይሆን ካፌና ዛፍ ሥር እንኳን ቁጭ ብሎ የሚያዳምጣቸው አያገኙም። ብዙዎቻችን አንባቢነት ማለት አንድ ልቦለድ መጽሐፍ ይዞ መታየት ይመስለናል።ከእንዲህ አይነት አባቶች ጋር ብናወራ ብዙ ነገር እናገኛለን፤ ለዚያውም በገጠመኝ፣ በተረትና ቀልድ እያዋዙ።
አሁንም ወደ መድረኩ እንመለስ
ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በዕለቱ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ደራሲያን አንዱ ነው።ስለካራማራ ጀግ ኖች እንዳልተወራላቸው እና ስለፍትሕ ነው የሚ ነግረን።እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተሾሙ ዕለት ስለካራማራ ጀግኖች ሲናገሩ ብዙዎች ተገርመዋል(ተረስቶ ነበር ማለት ነው)።እነዚህን ጀግኖች መዘከር ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ የሰሩትን ከማመስገንና ከመዘከር ይልቅ ራሱ ተበደልኩ፣ ተገፋሁ የሚል ነው የሚበዛው።የተገፋ የተበደለ ላይ እናተኩራለን።ፍቅር እስከ መቃብር ላይ ያለውን በዛብህን የምንወደው የተገፋ
የተበደለ፣ ምስኪን ተንከራታች ስለሆነ ነው።
አበጀ በለው መሆን ያስፈልጋል።ፍትሕን መሟገት አለብን።በፊት የነበሩ ሰዎች ላወጡት ደንብ ተገዢ ነበሩ።አጼ ዘርያዕቆብ አንድ ከባድ ህግ አውጥተው ነበር።ያንን ህግ ተግባራዊ ያደረጉት ራሳቸው ልጆች ላይ ሳይቀር ነበር።ፍትሕን አያዛቡም።እንዲህ አይነቱን የመሪዎች ጥበብ መዘከር ያስፈልጋል።
መድረኩ ላይ ብዙ የግጥም ሥራዎች ቀርበዋል። ብዙዎቻችን ግን ጥበብ ማለት ሙዚቃና ግጥም ብቻ ስለመሰለ ለንግግሮችና ለረጃጅም ጽሑፎች ዋጋ እየሰጠን አይደለም።አንድ ቆየት ያለ ገጠመኝ ልንገራችሁ።
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው።ፕሮግራሙ የኪነ ጥበብ ምሽት ነው።የጋዜጠኝነትና የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የሚያዘጋጁት።እናም ይህን የሰሙ ጥበብ ናፋቂዎች አንድ ዕለት መጡ።እነርሱ የጠበቁት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ግጥም የነበረ ይመስላል።
ልክ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ውይይት ነበር።ለዚያውም እኮ ውይይቱ ፖለቲካዊ ወይም ሌላ ደረቅ ጉዳይ አይደለም።ውይይቱ እንዳለቀ አስተያየት ሊሰጡ እጅ አወጡ።‹‹እኛ የመጣነው የኪነ ጥበብ ምሽት መስሎን ነው እንጂ እንዲህ አይነቱማ ክፍል ውስጥ ያሰለቸን አይደል እንዴ!›› የሚል አስተያየት ሰጡ።
የሚገርመው የሚቀጥለው ሳምንት የውይይት ርዕስ የሆነው የነዚያ ሰዎች አስተያየት ነበር።‹‹ኪነ ጥበብ ማለት የት ድረስ ነው?›› የሚል።
እንግዲህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብዛኛው ወጣት ስለሆነ ነው ብለን እንለፈው።ትልልቅ ሰዎች ያሉበትም እንደዚሁ እየሆነ ነው።አባቶች ሲናገሩ አንሰማም።አባቶችም ዕድሉን ደግመው ስለማያገኙ ነገር ያስረዝማሉ።የመናገር ብቻ ሳይሆን የመስማትም ጥበብ ይኑረን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በዋለልኝ አየለ