ወረርሽኝን በመከላከል ዙሪያ የክልሉ ርምጃዎች

በወረርሽኝ መልክ በመከሰት የህብረተሰብ ጤና እከል የሚሆኑ በርካታ በሽታዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ የማህበረሰብ ስጋት የሆኑ ወረርሽኞች አዲስ አሊያም ነባር ሊሆኑ ይችላሉ። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለሰው ልጆች ያልተጠበቀ ስጋት በመደቀን ሚሊዮኖችን የጨረሰ አዲስ በሽታ ነበር።

ኮቪድ 19 ባልተጠበቀ መልኩ የተከሰተ እና ለህክምና ባለሙያዎች ጭምር እንግዳ የሆነ የስርጭት ፍጥነት የነበረው ነው። ይህን መሰሉን ወረርሽኝ ሲከሰት ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተል አልፎ ሁለንተናዊ ምስቅልቅል የሚፈጥር ነው። በተቃራኒም ለዘመናት የሰው ልጆች ስጋት የሆኑ (ሄድ መለስ የሚሉ) ወረርሽኞችም አሉ። ከእነዚህ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ወረርሽኞች ውስጥ የማላሪያ፣ የወባ እና የኩፍኝ በሽታዎች ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ፈጣን የስርጭት መጠን ያላቸው እና በማህበረሰቡ ውስጥ ቀውስ የሚያስከትሉ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠንካራ ስራ ስትሰራ ቆይታለች። ይህ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳዩ መረጃዎች ከየቅጣጫው ይወጣሉ።

በሀገሪቱ እንደ አንድ የጤና ስጋት ተደርገው የሚቆጠሩ የወረርሽኝ በሽታዎችን ከመቆጣጠር እና ከመከላከል አንፃር ሰፊ ስራ ከሚሰሩ ክልሎች ውስጥ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይጠቀሳል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የወባ፣ ኩፍኝ እና ሌሎች ወረርሽኞች የመከሰት እድሉም ከፍተኛ እንደሆነ ይገለፃል።

ከሰሞኑ በአገሪቱ እንደ ስጋት ተቆጥሮ ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃ እየተወሰደበት የሚገኘው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኢምፖክስ) ቁጥጥር ከሚደረግባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ ነው። የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ተከትሎ ክልሉ በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሲዳማ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መስሪያ ቤት ዋና ሀላፊን አነጋግሯል።

ዶክተር ዳመነ ደባልቄ የሲዳማ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሲዳማ ክልል ጤና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰራቸው ስራዎች ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ እንዲሁም በጥናት እና ምርምር ዘርፍ ነው። ኢንስቲትዩቱ በዋናነት በላብራቶሪ፣ በመረጃ አያያዝና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ይሰራል። በተለይ በተላላፊ እና በወርሽኝ ነክ ከሚነሱ በሽታዎች አንፃር በአሁኑ ሰአት ወባ በክልሉ እንደ ችግር ሆኖ እየታየ ነው። ይህ ችግር ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ከዓመት በላይ አልፎታል። በመሃል የመቀነስ አዝማሚያ ነበረው ቢሆንም አሁን ግን ትንሽ ከክረምት ዝናብ ጋር ተያይዞ የመጨመር ምልክቶች አሉ።

ሌሎች ወረሽኞች ኮሌራም ሆነ ኩፍኝ በአሁኑ ሰዓት በክልላችን ውስጥ ታማሚዎች የሉም። ይሁን እንጂ ኮሌራን በተመለከተ ክረምት በመሆኑና ዋና የኮሌራ መተላለፊያ ከንፅህና ጋር ስለሚያያዝ ንፁህ ካልሆኑ የመጠጥ ውሃ ከሽንት ቤት አጠቃቀም ጋር የጥንቃቄና አስፈላጊ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም የመከላከል ስራዎች በሰፊው እየተሰራ ነው።

‹‹በክልሉ የኩፍኝ ወረርሽንም አምና ነበር ዘንድሮ ግን አልተከሰተም›› የሚሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ እሱንም በሚገባ ቅኝት እና አሰሳ ስራዎች በተገቢው እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ። ሌላው እንደ ሀገርም እንደ ክልሉ ስጋት ሆኖ ያለው በአሁኑ ሰዓት ኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ነው። ኤምፖክስ በመጀመሪያ ኦሮሚያ ውስጥ ሞያሌ አካባቢ ነው የተገኘው። የሲዳማ ክልልም የትራንዚት መስመር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ስጋት ቀጠና ሆኖ ይታያል። ወረርሽኙን ለመከላከል በየግዜው በየቀኑ የቅኝት ስራዎች እየተሰራ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ከተገኘ ለይቶ ማከሚያ ተቋም ከሆስፒታል ጀምሮ እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ በሚገባ ተደራጅቷል የሚሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ለባለሙያዎችም በየደረጃው ስልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑን ይናገራሉ። ከየመድሃኒት አቅርቦት አንፃርም በቂ ዝግጅት መደረጉን ይገልፃሉ። ምልክቶችም ካሉ ላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ ነው።

ዶክተር ዳመነ የላብራቶሪ ምርመራውን በክልሉ ለመጀመር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ያነሳሉ። ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ ከነ ህክምና ቁሳቁሱ በማዘጋጀት ባለሙያዎች ሰልጥነዋል። አንዳንድ ጉድለቶች ስላሉ (አቅርቦት ላይ) እሱን ለመፍታት እየተሞከረ ነው። ናሙናውን በማዕከል ከማድረግ ይልቅ እዚሁ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

‹‹በዋናነት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አለም ስጋት የሆነው ፓንደሚክ ኤምፖክስ ነው›› ያሉት ዶክተር ዳመነ፤ ሌላው ደግሞ ማሌሪያ ወረሽን መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪ ደግሞ ክረምት እየመጣ በመሆኑ የሳኒቴሽን ሃይጂን ሽፋናችን መቶ ፐርሰንት እስካልሆነ ድረስ ኮሌራን እንደ ስጋት እንቆጥረዋለን ይላሉ። በሌላ በኩል የምግብ እጥረት እና የተመጣጠነ ምግብ ስርጭት ዋና ዋና ብለው ከያዟቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

አጠቃላይ እንደ ኢንስቲትዩት ሰላሳ ስድስት በሽታዎች ተለይተዋል። ለምሳሌ 24 ወዲያውኑ ተለይተው ሪፖርት የሚደረጉ እና አስራ ሁለቱ ደሞ በየሳምንቱ ሪፖርት የሚደረጉ በሽታዎች ናቸው። እንደሀገር ኤምፖክስ ተገኘ ከተባለበት ቀን ጀምሮ እራሳችንን በተጠንቀቅ ላይ አደርገን ለሁሉም ህብረተሰብ ክፍል እስከ ቀበሌ ድረስ መልእክት ተላልፏል የሚሉት ዶክተር ዳመነ፤ በተለይ ኤምፖክሲ ምንድነው የሚለው ላይ፤ መተላለፊያ መንገዱ ፤ ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው፤ ህክምናው በምን መልኩ ይሰጣል በሚለው ላይ በአግባቡ መልእክቶች እየተላለፉ መሆኑን ይናገራሉ። መልእክቱ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በብዙሃን መገናኛ፣ በደብዳቤ ለሃይማኖት ተቋማት ለአገር ሽማግሌዎች በእኩል ለሁሉም ክፍል እንዲደርስ መደረጉን ይገልፃሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ክልልም ከሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር አንድ ትልቅ ማዕከል ተዘጋጅቷል። ከዚህ ቀደም በተፈጠረ ወረርሽኝ (ከኮቪድ) ብዙ ነገር ስለተማሩ ኤምፖክሲም (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ወይንም ወረርሽኝ ሆኖ ከተስፋፋ ለጥንቃቄና የመከላከያ ዘዴዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ ከአጋር ድርጅቶች በመተባበር ትልቅ ማዕከል ዝግጅት ተደርጓል።

‹‹ከዚህ ቀደም የሲዳማ ዞን ጤና ቢሮ የነበረው ግቢ እድሳት ተደርጎበት የህክምና ቁሳቁስ ገብቶ ባለሙያ መድበን ዝግጅት አድርገናል›› ያሉት ዶክተር ዳመነ፤ እነዚህ ምልክት ያለባቸው ሰዎችን በሙሉ ናሙናው ሄዶ ኔጌቲቭ እስከሚባል ድረስ እዛው ይቆያሉ ብለዋል። በቆዳ ሃኪም ታይተው ሌላ በሽታ ከሆነ ወይም ኤምፖክስ ካልሆነ የግድ ሌላ ስለሚሆን ያንን ከቆዳ እስፔሻሊስት ሃኪሞች ጋር እየተነጋገሩ ህክምና እያገኙ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የክልሉ ቦታዎች ከሆስፒታል እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ የለይቶ ማቆያ (አይሶሌሽን ሴንተር) እና ማከሚያ ተቋማት መደራጀቱን አብራርተዋል። በዛውም ልክ በማግስቱ ወዲያው ወደ አምስት መቶ እና ከዛ በላይ ለሚሆን ጤና ባለሙያ የአንድ ቀን ኦሬንቴሽን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመነጋገር እንደተሰጠ ይገልፃሉ። ቢያንስ ከቁጥጥር ውጪ የመውጣት ሁኔታው ከፈጠነ ቶሎ ለመቆጣጠር በሚል ስልጠና በመስጠት የለይቶ ማቆያ ማዕከል በየወረዳው በየጤና ጣቢያው እንዲዘጋጅ ተደርጓል። ሌላው ትልቁ ተግባር መከላከሉ ለማጠናከር እየተሰራ ያለው ስራ ቅኝት ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በትክክል መከሰቱን ለማወቅ ቅኝት ማድረጉ ተገቢ ነው የሚሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ ምክንያቱም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ሌላ ሽፍታ ሊሆን ይችላል ይላሉ። አንዳንዱ ምልክት አለርጂክ ሊሆን ይችላል በማለትም ይሄ ምልክት እየተለየና ናሙና እየተወሰደ በመስፈርቱ መሰረት ‹‹ኤምፖክስ ነው፣ አይደለም›› የሚለውን በቅኝት የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም በተደረገ ቅኝት እስከ ባለፈው አርብ ድረስ ሀያ ስድስት ናሙና (ኬዞችን) መወሰዱን ነግረውናል። በዚህ ቅኝት ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ኔጌቲቭ ውጤት ነው የተገኘው።

‹‹አሁን የአንዱ ብቻ ውጤት ነው የሚቀረው ሌሎቹ አብዛኛው ኔጌቲቭ ነው›› ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በክልሉ በቦረቻ ወረዳ ላይ አንድ ህፃን ብቻ ፖዘቲቭ ነበር ብለዋል፡፡ እሱም አስፈላጊው ክትትልና ህክምና ተደርጎለት ወደ ቤቱ ተመልሷል። እስካሁን ያለው ውጤት ኔጌቲቭ ቢሆንም ግን በዋናነት መከላከል ላይ ህዝቡ ግንዛቤ አግኝቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሰፊው እየሰራን ነው።

እንደ ዶክተር ዳመነ ገለፃ፤ በሽታ ወረርሽኝ ነው የምንለው በየሳምንቱ እየጨመረ ሲሄድ ነው። መጀመሪያ ከተመዘገበው ቁጥር እያሻቀበ ሲሄድና ከቁጥሩ ጋር ሲነፃፀር ከፍ እያለ ከሄደ ወረርሽኝ ይሆናል። በመሆኑም በሳምንቱ ከተመዘገበው በታች ነው መሆን ያለበት። ከተመዘገበው ቁጥር ለማውረድ ወይ በዛው ለመቀጠል ነው የሚሰራው። ስለዚህ በየደረጃው ላሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ትምህርት እየተሰጠ ነው። በወባ መከላከል በማኔጅመንቱና በመድሃኒት አቅርቦት ላይም ከጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በአግባቡ እየሰራን ነው። ዘንድሮም ወረርሽኝ ሆኖ ስጋት እንዳይሆን እየሰራን ነው።

ወባን ለመቆጣጠር የኬሚካል ርጭት እና አጎበር መስጠት አንዱ መከላከያ መንገድ ነው የሚሉት ዶክተር ዳመነ፤ ሆኖም በአጎበር አጠቃቀሙ ላይ ክፍተት እንዳለ ይናገራሉ። ይህ ክፍተት እንዳይፈጠርም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። አጎበሩ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‹‹አርጅቷል›› ብሎ ለህክምና ከተሰጠው ግልጋሎት ውጪ ወደሌላ ግልጋሎት የማዋል ዝንባሌዎች አሉ፡፡ እሱንም በትምህርት ግንዛቤ በመፍጠር እየተከላከሉ መሆኑን ያስረዳሉ። ነገር ግን አቅርቦቱም እንደበፊቱ አለመሆኑን፤ ለሁሉም ተጋላጭ ለሆነ አባወራ (ማህበረሰብ) አጎበር የሚደርስበት ሁኔታ ከባድ እንደሆነ ያነሳሉ። በጥቅሉ የአጎበር አጥረት አለ ብለዋል።

ኬሚካል ከዚህ በፊት አገር ውስጥ ነበር የሚመረተው ያሉት ዶክተር ዳመነ፤ አሁን ግን አገር ውስጥ እየተመረተ አለመሆኑን ይናገራሉ። ኬሚካሉ ለአካባቢው ብክለት አደገኛ ስለሆነ እንደ ሀገር ኬሚካል የሚያመርት ፋብሪካ የለም። ምርቱም ከውጭ በዶላር ተገዝቶ የሚመጣ ነው። በክልሉ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ (አምና አራት ወረዳ ላይ) ርጭት ተካሄዷል። ተጋላጭ የሆኑ ወረዳዎች ግን ከዛ በላይ ናቸው። ካለው የኬሚካል እጥረት አንፃር አራት ወረዳ ላይ ነው ርጭቱ ተካሄዷል። አጎብር አጠቃቀም ላይ ግን ያለውንም፣ የተቀደደውንም ሰፍተው እንዲጠቀሙ ተገቢ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው።

‹‹አኖፌለስ ስቴቨንሳይ›› ከምትባለው ከአዲሲቷ ወባ ትንኝ ጋር ተያይዞ በከተሞች አካባቢ ይስፋፋል የሚባል ወሬ መኖሩን ተከትሎ አስተያየት የሰጡት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ ከአዲሷ የወባ ወረርሽኝ (አኖፌለስ ስቴፈንሳይ) ጋር በተገናኘ በክልሉ የተገኘው አምና ላይ ነበር፡፡ ‹‹ሀዋሳ ከተማ ላይ አኖፌለስ ስቴፈንሳይ ከዚ በፊት የነበረች ነች፤ ወይስ አዲስ የመጣች ነች›› የሚለው ላይ ገና ተጨማሪ ጥናታዊ ምርምር ያስፈልጋል። ‹‹የነበረውን ነው ያገኘነው ወይስ አዲስ የመጣ›› ለሚለውም እንዲሁ ምርምር ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ‹‹የስቴቨንሰይ መገኘት ማለሪያ ላይ ምንድነው አስተዋፅኦ ያደረገው›› የሚለው ገና አልተጠናም፡፡ ወደፊት ምርምር ተደርጎ ተገቢ ጥናት ይፋ መደረግ ይኖርበታል።

‹‹ምርምርና ጥናት ለማድረግ ከባለሙያዎቻችንና ከኤክስፐርቶች ጋር እየተነጋገርን ነው›› ያሉት ዶክተር ዳመነ፤ ትንኟ ዲ ኤን ኤ ድረስ መጠናት አለባት በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኢንቲሞሎጅ ቡድን የግድ መጠናት እንዳለበትም መስማማቱን ገልፀዋል።

በጥናቱ ‹‹ትንኟ ከሌሎቹ የወባ ዝርያዎች ጋር ምንድነው የሚያመሳስላት፤ በፊት ከተለመደችው የወባ ወረርሽኝ ጋር የሚኖራት አስተዋፅኦ ምንድነው›› የሚለው ላይ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል። እሱ ከተጠና በኋላ ‹‹አዲሷ ትንኝ ይሄንን ያህል የወባ ወረርሽኝ አስተዋፅኦ አድርጋለች አይ አስተዋፆ የላትም›› የሚለው ጉዳይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ኢንተሞሎጂ ቡድኑ ዲ ኤን ኤዉን ወስዶ ምርምር መጀመሩን ገልፀዋል። በመሆኑም አጠቃላይ መረጃው ከተሰራ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You