ህግና መሪ ከሌለው ሀገር አምባገነንንም አምባገነን መሪና ህግ ያለው ሀገር ይሻላል የሚል ብሂል አለ። ህግ ማክበር የስልጣኔዎች ሁሉ መጀመሪያ ነው። አንድ ማኅበረሰብ ሰለጠነ፤ አደገ የሚባለው ህግና ስርዓትን ማክበር ሲችል ነው። ህግና ስርዓት እንዲከበር ጥረት የማያደርግ አስተዳደርና ማኅበረሰብ ለግጭት፤ ሁከትና አለመረጋጋት ይዳረጋል። በልማት ወደኋላ ይቀራል፤ በኑሮ ውድነት ይሰቃያል፤ ድህነትና ጉስቁልናም መለያው ይሆናል።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግስት ስርዓት ያላትና ዜጎቿም በህግና በስርዓት መተዳደርን ልማድ ያደረጉ ህዝቦች መኖሪያ ናት። በርካታ የዓለም ሀገራት የመንግስት ስርዓት ባለቤት ሳይሆኑ በፊት ኢትዮጵያ ህግና ስርዓት ባለው መልኩ የመተዳደር ባህል ያለው ስልጡን ሕዝብ ያለባት ሀገር ነች። በጥንታዊ የገባር ስርዓት ሳይቀር መንግስት ተገቢውን ግብር እየሰበሰበ የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ሲያስጠብቅ ኖሯል። ለዘመናትም በጸናው የኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ ኬላዎችን ጨምሮ ግብር መሰብሰብ የመንግስት ብቸኛ መብትና ኃላፊነት ነው።
በኢትዮጵያ ኬላዎችን የመክፈትና የማስተዳደር ስልጣን የተሰጠው ለኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ቢሆንም በየስርቻው በጎበዝ አለቆች የሚመሩ ኬላዎች ተበራክተዋል። እነዚህ ኬላዎች እንዳሻቸው በሸቀጦች ላይ የዋጋ ትመና ከማድረጋቸው ባለፈ የግብርና ምርቶች ወደ ተጠቃሚው እንዳይደርስ ብሎም ዜጎች ከቦታ ቦታ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት እየሆኑ ነው። ይህም ለሸቀጦች ዋጋ መጨመርና ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ እየሆነ ከመምጣቱም ባሻገር እንደሀገር አለመረጋጋትን የሚፈጥር ነው።› በፌዴራል መንግስት የስድስት ወር አፈጻጸም ወቅት ህገ ወጥ ኬላዎች በአንዳንድ የኤክስፖርት ምርቶች አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ተመላክቷል።
ህገወጥ ኬላዎች የህገወጥ መሳሪያ፤ የአደንዛዥ እጽ፤ የህገወጥ ለሰዎች እና የኮትሮባንድ ዕቃዎች ዝውውር ዋነኛ መተላለፊያዎች ከመሆናቸውም በሻገር ህገወጦችና የሰፈር አለቆች እንዲበራከቱ በማድረግ ኅብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸውን እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ በሚቆጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካኝነት ህጋዊ ነጋዴዎችን አላስፈላጊ ገንዘብ በመጠየቅና ለእንግልትና ውጣውረድ በመዳረግ ላይ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሀሳባቸውን የሰጡ ግለሰቦች ያስረዳሉ። በተለይም እነዚህ ህገወጥ ሰዎች በየቦታው ባቋቋሟቸው ህገወጥ ኬላዎች አማካኝነት የግብርና እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለተደራራቢ ቀረጥ በመዳረጋቸው ምክንያት የግብርና ምርቶች ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ መዳረጋቸውን ኢፕድ ያነጋገራቸው የእህል በረንዳ ነጋዴዎች ገልጸዋል።
ከጥር እስከ መጋቢት ባለው ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ የሚወጡበትና የተሻለ የገበያ ዋጋ የሚኖርበት ጊዜ ቢሆንም በየቦታው በኬላዎች አካባቢ በሚታዩ ብልሹ እና ህገወጥ አሰራሮች ምክንያት የሰብል ምርቶች ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሊያሻቅብ ችሏል።
በየኬላው የሚፈጸመው ህገወጥ ቀረጥም የግብርና ምርቶች ወደ ተጠቃሚው በቀላሉ እንዳይደርስ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በተለይ በከተሞች አካባቢ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል።
የፌዴራል መንግስት በሚያስተዳድራቸው ነባር መንገዶች ጭምር እነዚህ ህገወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ተግባራት ምክንያት ሸቀጥና የኤክስፖርት ምርት ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ማድረስ አዳጋች ሆኗል። ከዚህም ባለፈ ህገ መንግስታዊ የሆነው የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብትንም የገደበ እስከ መሆን ደርሷል።
የአንድ መንግስት ቅቡልነት መለያ ከሆኑት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ኬላዎችን በአግባቡ ማስተዳደርና ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነውና ኬላዎችን ከሰፈር አለቆች ነጻ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይሆንም።
በአጠቃላይ በህገ ወጥ ኬላዎች ላይ የሚታዩት ህገወጥ ተግባራት ከግብርና ምርቶች ማሻቀብ በተጨማሪ ለህገወጥ መሳሪያ፤ ለአደንዛዥ እጽና ለህገወጥ ሰዎች የሚዳርግና ኮንትሮባንድንም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፋፋ በመሆኑ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠውና አፈጣኝ እርምጃ ሊወስድበት ይገባል። ጉዳዩ የሰዎችንም ተዘዋውሮ የመስራት መብትን የሚገድብና በየቦታው ተፈናቅለው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፎችንም ለማቅረብ እንቅፋት እየሆነ ስለሚገኝ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ህገወጦችን ስርዓት ሊያሲዛቸው ይገባል! ይህ የማይደረግ ከሆነ ይሄው ህገወጥ ተግባር አድጎና ጎልብቶ ለሀገርና ለሕዝብ ትልቅ ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም