ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ረገድ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባ ጉዳዮች አንዱ የሰው ሀብት ልማት ነው። ቴክኖሎጂው የሚፈለገውን በክህሎትና በእውቀት የዳበረ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ልዩ ተሰጥኦና ክህሎት ያላቸው ዜጎችን በማበረታታት ያላቸውን የፈጠራና የምርምር ሀሳብ ወደ ውጤት ለመቀየር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች የሚበረታቱበት ማዕከል አልነበረም። አሁን ግን ለእነዚህ ዜጎች እፎይታን የሚፈጥር ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ያላቸውን አካላት የሚያስተናገድ ተቋም ተቋቁሟል። የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት ባለልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ዜጎችን ለማስተናገድ የተቋቋመ ተቋም ነው። ኢንስቲትዩቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር የሚገኝ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ አሁን እያከናወነ ያለውን ተግባር በተመለከተ ኢንስቲትዩቱን በቅርበት ከሚመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና የምርምር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት የተቋቋመበት ዓላማ ምንድነው?
ዶክተር ባይሳ፡- ማዕከሉ በትምህርት ሚኒስቴርና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የማይስተናገድ ለየት ያለ ተሰጥኦና ችግር ፈቺ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶችን ወይም ሌሎች ጎልማሶችን አቅም በማበልጸግ ለመጠቀም የሚያስችል ተቋም እስካሁን አልነበረም።ችግር ፈቺም ብቻም ሳይሆን ወደ ፊት ልማታዊ አበርክቶ ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ ከተፈጥሮ ፀጋዎች በመነሳት ያንን ሀብት ወደ ልማት አቅም ይቀይራሉ ተብለው የሚታመኑ አካላትን ለመቀበልና ለማስተናገድ የሚያስችል ተቋም በአገሪቱ አልነበረም።ይህን ተቋም እውን ለማድረግ ነው ማእከሉ የተቋቋመው።ይህ ተቋም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነትና ፕሮጀክት አስጀማሪነት ተቋቁሞ በዚህ ዓመት ተመርቋል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ አሁን ላይ ምን እየሰራ ነው ?
ዶክተር ባይሳ፡– በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሙከራ /በፓይለት/ መልኩ በአገሪቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎችን ለማሰባሰብ የሚያስችል ጥሪ ቀርቦ እነዚህ አካላት ሥራቸውን እንዲያሳዩ ተደርጓል። ለእነዚህ አካላት በዚህ ማዕከል ስልጠና ይሰጣቸዋል፤ ድጋፍ ይደርግላቸዋል። ፕሮቶታይፕ ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ ሥራ መስራት የሚችል ግኝት ካወጡ በኋላ በምረቃ ጊዜ ታይቶ ወደ መከላከያ ኢንጂነሪንግ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ)፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ወደ ሌሎች ተቋማት ገብተው ይበልጥ የፕሮዳክሽንና የዲዛይን ድጋፎች እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡
በ2015 ዓ.ም አጫጭር ሥራዎች ይጀመራሉ። በ2016 ዓ.ም እንደ ፕሮጀክት የራሱ በጀት፣ የራሱ ሀብት እና የሰው ኃይል እንዲኖረው በማድረግ ራሱን እንዲችል ተደርጎ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል።
አሁን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ ፕሮጀክት/ፕሮግራም ተቀርጾ እንደዚህ አይነት ሌላ ቦታ የማይስተናገድ የተለየ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች ወስደን ያንን ሀሳብ ያንን ተስጥኦ የማበልጸግ፣ የማሳደግ፣ የማስፋት፣ ለአገራችን አበርክቶ እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ እንሰራለን፡፡
ይህ ሥራ ዞሮ ዞሮ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽንን ሊያረጋግጥ የሚችል የቴክኖሎጂ ክምችት በአገራችን በብዛትና በጥራት እንዲኖር የሚያደርግ ነው።በድምሩ የኢኖቬሽን ኢኮ ሲስተም አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር የሚያደርግ ሥራ እንሰራለን።አሁን እየሰራን ባለነው አጫጭር ስራ ዜጎችን ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አወዳድረን እንቀበላለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በ2015 ዓ.ም በተደረገ ውድድር ምን ያህል ዜጎች መቀበል ችሏል?
ዶክተር ባይሳ፡– አሁን ላይ የመጀመሪያ ዙር ውድድር አልቋል። በመጀመሪያ ዙር ጥሪ 80 ባለልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ያላቸውን አስተናግዷል። ከእነዚህ ውስጥ 76ቱ ወንዶች ሲሆኑ፣ አራት ሴቶች ናቸው።
ለሁለተኛው ዙር ደግሞ ከመጀመሪያ ዙር ባገኘው ተሞክሮ መሠረት መስፈርቶች ወጥተው የሚሰጡ የትምህርት ኮርሶች ተለይተዋል።ለዚህ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናውን ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች እየተለዩ ናቸው። ጥሪውን ለማውጣት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል። የሁለተኛው ዙር ጥሪ በአጭር ጊዜ ይወጣና ወጣቶችን መቀበል እንጀምራለን። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ማስታወቂያው እንዲደርስ በማድረግ ተደራሽነቱን በማስፋት ያሉትን ባለልዩ ተሰጥኦ ዜጎች አወዳድሮ ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የሚቀበላቸው ዜጎች ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ በመሆናቸው የሚስተናገዱት እንዴት ነው?
ዶክተር ባይሳ፡- ይህ ሥራ ሲሰራም ሆነ መስፈርቱ ሲወጣ ተወዳዳሪዎችን የመለየቱ ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በጋራ ይከናወናል። ለእነዚህ ባለልዩ ተሰጥኦ ዜጎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲሟሉ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። ለትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ካሉ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲ በመተባበር እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡-እነዚህ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለተሰጥኦ ዜጎች በአንድ ላይ የሚስተናገዱት እንዴት ነው ?
ዶክተር ፡- ዋናው መሠረታችን ተሰጥኦ ነው። የአገር ችግር ሊፈታ የሚችል፤ የአገራችንን ልማት ሊያረጋግጥ የሚችል፤ ነገ ሳይንቲስት የነገ የዲጅታል አመራር ሊሆን የሚችል ሰው የሚወጣበት ማዕከል እስከሆነ ድረስ አንዳንዶቹ ቴክኖሎጂን ከማምጣት ምርታማነትን ከማረጋገጥ አንጻር ዛሬውኑ አስፈላጊ ምርት ያላቸውም አሉ።
የእያንዳንዱን ሰው ተሰጥኦ ማዕከል ባደረገ መልኩ ድጋፍ ይደረግለታል። በብዛት እንደሌሎቹ አሰባስበን አንድ ቦታ አስገብተን ድጋፍ የምናደርግበት አይነት ብቻ አይደለም። በጋራም የሚሰጣቸው እንዳለ ሆኖ ግን ኢንቨስትመንቱ ለእያንዳንዱ ተሰጥኦ በራሱ የሆነ ድጋፍ ይደረግለታል። ማዕከሉ ችግር ፈቺ ሀሳብ ያላቸው፣ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን በመውሰድ እነዚያን ተሰጥኦዎች በማስፋት እና በማሳደግ የማልማት ሥራ ይሰራል።እንደ ትምህርት ዘርፉ በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ተግባርን ማዕከል ያደረገ ስለሆነ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ችግር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ዜጎች የሚሰጠው ልዩ ድጋፍ ያለው ፋይዳ ምንድነው?
ዶክተር ባይሳ ፡- ከዚህ በፊት በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚታየው የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች የሠሩ ዜጎች ብልጭ ብለው ታይተው የሚጠፉበት (ወደኋላ የሚመለሱበት ሁኔታ) አለ። አሁን እንደዚህ አይነት ተሰጥኦ ያላቸውን አንደኛ ከመሠረቱ ጀምረን መደገፍ አለብን። በማስተማር፣ በማብቃት ከሚፈለገው ቦታ ለማድረስ እንሰራለን። እንደዚህ ካደረግን በኋላ በቂ የሆነ ብቁ ግኝት (ፕሮዳክት) ጋ ከደረሱ ወይም የሚፈለገው ውጤት ከመጣ ያ ግኝት ወደ ስታርትአፕ (ሥራ ፈጠራ) ይቀየራል። በስታርት አፕ (ሥራ ፈጠራ) ከትንሽ ጀምሮ ድጋፍ ይደረግለታል። ከዚያ ቀጥሎ ወደ ትላልቅ ኩባንያ እንዲሸጋገሩ ያደርጋል።
በአጠቃላይ ዓላማው የኢትዮጵያን ብራንድ ኩባንያ ፈጥረን አገራችንን ለብልጽግና ማድረስና ማብቃት ነው።አገር በቀል ሀብትና እውቀት አለን።እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ አይተን አገራችን የምትፈልገውን ብልጽግና እናረጋግጣለን።ያንን ለማድረግ ደግሞ አገራዊ ትላልቅ ኩባንያዎች በእኛው ሰዎች በአጭር ጊዜ እናደርሳለን ብለን ስለምናስብ ነው።በዚህም ከውጭ የሚገባውን እናስቀራለን፤ ወደ ውጪ የመላክ አቅም ይኖረናል ብለን በማሰብ ወደዚያ እየሄድን ነው፡፡
ባለልዩ ተሰጥኦ ዜጎችም ተሰጥኦዋቸው ይጨምራል፤ የስራ እድል ፈጥረው ሀብት ያካብታሉ፤ ቴክኖሎጂን ያሻግራል፤ የኢኖቬሽን ኢኮ ሲስተሙን ከማሳለጥ አንጻር ትልቅ ሚና ይኖረዋል።ኤክስፖርት የማድረግ አቅም ይፈጥራል። ከትንሽ ጀምረን ከሰራን ካቀድነው እንደርሳለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሥራው ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችስ ምንድናቸው?
ዶክተር ባይሳ፡- ከዚህ በፊት ከነበረው እጥረት በ2014 የተሻሻለው ፖሊሲ ላይ የተለዩት ነገሮች አንደኛው ለኢኖቬሽን ኢኮ ሲስተሙ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ በቂና በቁ የቴክኖሎጂ ክምችቶች አለመኖራቸው ነው።ሁለተኛው ደግሞ ያሉትን የቴክኖሎጂና የምርምር ውጤቶች ወደ ኢኖቬሽን (ውጤት) ከመቀየር አንጻር የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸው ነው።
አሁን የቴክኖሎጂ ክምችትን እንጨምራለን፤ በተጨማሪም እነዚህ ቴክኖሎጂዎች፣ የፈጠራ ስራዎች ሥራና ሀብትን መፍጠር ስላለባቸው ይህ እንዲሳካ እንሰራለን። አሁን ላይ የክህሎት ውስንነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። መካከለኛ፣ ከፍተኛና ዝቅተኛ ክህሎቶች ሊኖሩ ይችላሉ ብለን ለይተናል።
ከዚህ አንጻር ደግሞ ውጭ አገር ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት እንዲሁም በአገር ውስጥ ካሉ ምርምር ተቋም ጋር እንሰራለን። በተጨማሪም በውጭ አገር ከሚኖሩና በዘርፉ ላይ ልምድና እውቀት ካላቸው፤ እዚያ ያገኙትን ነገር ይዘው መምጣት ከሚችሉ፤ ስለአገራቸው ከሚናገሩና ከሚከራከሩ ተቆርቋሪ የዲያስፖራ አባላት ጋር ከሰራን የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ባይሳ፡- ተቋሙ በዚህ ዓመት በአጫጭር ስራዎች በሁለት ዙር ዜጎችን አወዳድሮ ይወስዳል።በዚህ ውስጥ ደግሞ ትምህርቶችን እናገኛለን፤ በውጭ ከሚገኙ አጋሮቻችን ጋር እንሰራለን። በአገር ደረጃ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እንሰራለን። በዚህም የተቀመጠውን እቅዳችንን እናሳካለን። አገር በቀል እውቀት አለ፤ ይህን የአገራችንን ሀብት ወደ ስራ በመቀየር አገራችን ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ እንሰራለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ባይሳ፡– ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ያላቸው የአገራችን ወጣቶች፣ ዜጎች በትኛውም የእድሜ ክልል ያሉ፣ ወደማምረት ደረጃ የደረሱ፤ እዚያ ከመድረስም በፊት ደግሞ ሀሳብ ያላቸው፣ በዲዛይን ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ ከዚያ ያለፈ ደግሞ ወደ ገበያ ለመግባት የራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ ላሉት በሙሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የድጋፍ ፓኬጆችን እያቀረበ ነው፡፡
የፋይናንስ ድጋፎችን አቅም በፈቀደ መልኩ ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመሆን እየሰጠን ነው።የቴክኒክ ድጋፎችንም ለመስጠት ከድጋፍ ሰጪና በዘርፉ ካሉ ሙያተኞች ጋር በመተባባር እየሠራ ይገኛል፡፡
መሠረተ ልማቶችን የኢንኩቤሽን ማዕከላትን፣ የሳይንስ ካፌዎችንና እና መሳሰሉት በክልሎች እንዲሁም በከተሞች እየተስፋፋ ነው። ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባባር በመስራት ላይ ነን። በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ድጋፍ የሚፈልጉ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚያወጣውን ማስታወቂያ እንዲከታተሉ፣ በአካል ቀርበው እንዲጠይቁ ባላቸው እውቀት እና ክህሎት ተጠቅመው ለአገራቸው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ይደረጋል ፡፡
በተለያዩ ፓኬቶች ከመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርሃ ግብር (UNDP) እና ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ድጋፎች እየተደረጉ ነው። እነዚያን ፕሮግራሞች በመከታተል ውድድር ማድረግ እንዲችሉና የራሳቸው አበርክቶ እንዲኖራቸው ጥሪ አቀርባለሁ ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ባይሳ ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም