ሀገሮች ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመንና ምርትን በሚፈለገው መጠን በማቅረብ የዜጎቻቸውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት የማድረጋቸው ጉዳይ እንግዳ አይደለም። ጥረት ማድረግ ብቻም አይደለም፣ ጥቂት የማይባሉ ሀገራት ከራሳቸው ፍጆታ ተርፎ ምርታቸውን ለሌሎች ሀገራት በማቅረብ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በወጪ ንግድ ሲገነቡ ማየት የተለመደ ነው ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለስንዴ ግብርና አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ብትሆንም፤ የማምረት አቅሟና ምርት መጠኗ ግን ለሀገር ውስጥ የሚበቃ ካለመሆኑም በላይ፣ በየዓመቱ የሚጨምረው ፍላጎትና ተፈላጊው አቅርቦት ሊጣጣም አልቻለም ። እንደውም መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ2009 እስከ 2013 ዓ.ም 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በ15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ በመግዛት ወደ አገር ውስጥ አስገብታለች ።
አሁን ይህ ሁሉ እየተቀየረ ያለ ታሪክ ወደ መሆኑ እየመጣ ያለ ይመስላል። በተለይ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስንዴ ልማት ላይ የተሻለ ሥራ እየተከናወነ መምጣቱ ለዚህ ተገቢ ማሳያ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንዲኖራት ባለፉት ሦስት ዓመታት በበጋ የስንዴ ልማት የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥርና የክላስተር እርሻዎች በማስፋፋት የበጋ ስንዴ ምርቷን መጨመር ላይ አተኩራ በመስራቷ ውጤት ማግኘት ስለመቻሏ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በተለይ በያዝነው ዓመት የተሻለ የስንዴ ዝርያ አቅርቦት፣ የአፈርና የውኃ አጠቃቀምና ሌሎች ድጋፎች በማድረግ፤ እንዲሁም፣ መንግስት በተለይም የግብርና ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ጥረት ስንዴ በተያዘው ዓመት ከውጭ ገበያ አለመገዛቱ በቡድን ሰባት ሀገሮች ስብሰባ ላይ የተገለጸ መሆኑ ይታወሳል ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ እንደገለጹት፤ በአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ስንዴን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እቅድ ተይዟል። ይህን ተከትሎም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ከባለሀብቶችና ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ሲሰራ ቆይቷል።
ቀደም ሲል የስንዴ ምርት የሚለማው በክረምት ወቅት ብቻ ነበር ። አሁን ግን ዓመቱን ሙሉ ለማልማትና ምርቱን ለመጨመር የበጋን ወቅት መጠቀም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ይላሉ።
የበጋ ስንዴ ልማት ሥራዎች ከተጀመሩ በኋላም አምና ለስንዴ ምርት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን 180ሺህ ሄክታር ወደ 400ሺህ ሄክታር ማሳደግ የተቻለ መሆኑን ይናገራሉ ። የመስኖና ቆላማ አካባቢዎችን አሟጦ በመጠቀም ረገድ ሦስት አማራጮች ተዘጋጅተው በዚያው መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አስታውሰው፤ የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በመስኖ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች ወደ ስንዴ ምርት እንዲገቡ ለማድረግ መሰራቱንም ይናገራሉ፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፤ ስንዴ በስፋት መመረቱ ተገቢ ብቻ ሳይሆን “የዘገየ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ ። ነገር ግን፣ ምንም እንኳ ምርት በሰፊው ቢኖርም ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ መክተት እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙት ኢኮኖሚስቱ አቶ ሰይፈሥላሴ ገብረእግዚአብሔር፤ በምዕራብ አርሲ ዞን የተመረተውን በማስታወስ፤ ስንዴ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ካላለፈ እና አርሶ አደሩንም ሆነ ሸማቹን ማህበረሰብ ካልጠቀመ ማምረት ብቻውን ግብ መምታት እንደሆነ አድርጎ መውሰድ ተገቢነት የጎደለው መሆኑንም ያመለክታሉ።
እንደ ኢኮኖሚስቱ ማብራሪያ፤ ለዳቦና ለዱቄት የሚደረገው ድጎማ መንግሥት ላይ ያስከተለው የወጪ ጫና የሚታወቅ ነው ። ከዚህ አኳያ ምርቱ በስፋት መኖሩ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ። ነገር ግን፣ በፍጆታ ረገድም በዚህ ዓመት ከስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የስንዴ ፍላጎት እንደሚኖር ታውቋል፤ እንደ ዳቦና ፓስታ ያሉ የስንዴ ውጤቶች ፍላጎት ሊጨምር ስለሚችል ወደ ውጭ መላክን በሚመለከት ደጋግሞ ከማቀድ በተጨማሪ፣ ፍጆታውን ለመሸፈን ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ።
ኢኮኖሚስቱ እስከ አሁንም የስንዴ ፍላጎት እየጨመረ በተቃራኒው አቅርቦቱ በሚፈለገው መጠን ባለመሆኑ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ምርት ከውጭ በማስገባት ሀገሪቱ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገች፣ ሕዝቡም ከስንዴ ጋር የተያያዙ ምርቶችን በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት ተገዶ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በዋናነት ምርቱ በስፋት መኖሩ ለውጪ ንግድ ሳይሆን የህዝቡን ፍላጎት ለማጣጣም ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል ።
የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማርካት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱ በበጎ ገፅታ የሚታይ ቢሆንም፤ በውጭ ገበያም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ሌሎች ሥራዎችም መሠራት እንዳለባቸው አመልክተዋል ። በግብርናው ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎች አርሶ አደሩ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርት መስራት አለባቸው ያሉ ሲሆን፤ የምርት ጥራትን ማሳደግ እና የግብይት ሥርዓቱን ማዘመን ላይ ጎን ለጎን ሊሠራ ካልቻለ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አዳጋች ይሆናል የሚል እምነትም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ከክልሎች በሚሊዮን ኩንታል የሚገመት ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተስራ ስለመሆኑ እየተነገረ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ ምርቱ ወደ ውጭ መላኩ መልካም እና ለሀገር እና ለሕዝብ ይጠቅማል ተብሎ ቢታሰብም በተቃራኒው የዓለምን ሁኔታ ማየት የሚገባ መሆኑንም ያስረዳሉ። ኢኮኖሚስቱ አቶ ሰይፈስላሴ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንዴ ፖለቲካ እንደሆነ ሌሎች ሀገሮች ሆን ብለው በገበያው ላይ ችግር ለመፍጠር የሚጥሩበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ቀድሞ ማጥናት ያስፈልጋል ይላሉ ።
ሀገሪቱ በመደበኛነት ከምታመርተው ስንዴ በተጨማሪ በበጋ በስፋት እያመረተች መሆኑ ጎረቤት ሀገራትንም ሆነ ሌሎች በሩቅ ያሉ ሀገራትን ያስደስታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሉት ኢኮኖሚስቱ አቶ ሰይፈስላሴ፣ በውጪው ገበያ ሊያጋጥም የሚችለውን እንቅፋት ቀድሞ ለመከላከል የሀገር ውስጥ የገበያ ሥርዓቱን ማዘመን እና የምርት ጥራትን ማስጠበቅ መሰረታዊ እና ወደ ውጭ ከመላክ በፊት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ባይ ናቸው ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በስንዴ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የጥራጥሬ እህሎች ላይ ያሉ ህገ-ወጥ ደላሎች ሲያምታቱ ክትትል በማድረግ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ።
እንደ እኚሁ ኢኮኖሚስት ማብራሪያ፣ የክረምት ስንዴ የግብርና ምርት ማደግም ሆነ የበጋ ስንዴ ምርት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እና እየሰፋ መሄዱ አንዳንዴ ጥቅሙ ከሀገር የሚያልፍ ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ የጎረቤት ሀገራት፣ በተለይ ጅቡቲ የመግዛት ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች። ለጎረቤት ሀገራት ምርትን ማቅረብ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ ለቀጠናዊ ትስስር የሚኖረው ፋይዳም የሚናቅ አይደለም፡፡
መንግስት በዱቄት ላይ ድጎማ በመስጠት የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ ያግዛል ማለት ትርጉሙ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስንዴ በስፋት መመረቱ ለድጎማ እና ለስንዴ ግዢ ይውል የነበረው ገንዘብ የሀገሪቷን ዕዳ ለማቃለል ወይም ሌሎች የልማት ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዝ መረሳት የለበትም ብለዋል ።
በኢኮኖሚስቱ የተነሳው እና ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል የተባለው ሌላው ጉዳይ አምራች አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግን የተመለከተ ነው ። የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ወጪ እና በመስኖ ሲያለማም የነዳጅ ወጪውን ሸፍኖ ተመጣጣኝ ትርፍ የሚያገኝበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ስንዴን በበጋ ማምረት እንደትልቅ አትራፊ ጉዳይ ከማየት ይልቅ በተቃራኒው እንደከንቱ ድካም እንዳይታይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል ።
መንግስት ስንዴ አምራቾችን ይደግፋል የሚል እምነት ያላቸው መሆኑን የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ አርሶ አደሩ በአንድ ሔክታር የሚያገኘው ምርት ከወጪው እና ከጉልበቱ፤ ከአጠቃላይ ድካሙ አንፃር ትርፋማ የሚሆንበት ሁኔታ በደንብ ታስቦበት ሊሠራ እንደሚገባ፤ ያለበለዚያ ግን ውጤቱ በተቃራኒው እንዳይሆን ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል ። በተለይም ስንዴ ላኪዎች የዓለም የስንዴ ገበያ የሚበላሽበት አጋጣሚ ሲፈጠር ችግሩን ወደ ታች ወደ አርሶ አደሩ የሚያወርዱት ከሆነ አርሶ አደሩ የሚጎዳበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል ።
እንደ እኚሁ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በቅርብ ኬኒያ ስንዴ ትገዛለች ተብሎ ቢገመትም ምርቱን ከኢትዮጵያ ባነሰ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ካገኘች ግዢውን የማትፈፅምበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ። ወይም ሆነ ተብሎ በጎረቤት ሀገራት የስንዴ ዋጋ አነስተኛ እንዲሆን የሚሠራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ። ይህንን በጥንቃቄ በማየት ምርቱ ወደ ውጪ የሚላክበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ።
በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ ለስንዴና ስንዴ ምርት ምቹ የአየርም ሆነ አፈር፤ ውሃም ሆነ መልክአ ምድርን የተቸረች ብትሆንም፤ ስንዴን ለሕዝቡ በበቂ መጠን ሳታቀርብ ዘመናት ተቆጥረዋል። አሁን ደግሞ የተትረፈረፈ ምርት ስለመመረቱ እየተነገረ ነው ። ይህ መልካም ቢሆንም፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ ሲታይ እንደነበረው ተስፋ አስቆራጭ ከፍተኛ የዋጋ መርከስ አርሶ አደሩን አጋጥሞት ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ አለበት ። አንዳንድ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሴራዎችን አስቀድሞ በማሰብ ከተሰራ ጉዳዩ ትልቅ የአገርና ህዝብ ተስፋ መሆኑ የሚካድ አለመሆኑንም ተናግረዋል ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም