36ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ለዚህም መላው የአገሪቱ ሕዝቦች አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። የአህጉሪቱ መሪዎች በስብሰባው ከመሳተፍ ጀምሮ ያሳዩት ንቁ ተሳትፎና የደረሱበት ውሳኔ አህጉሪቱ በአዲስ መነቃቃት ላይ እንዳለች ያመላከተ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በተለመደው አትዮጵያዊነት እንግዶችን ተቀብለው በማስተናገድ ያሳዩት ጨዋነትና ትብብር የሚመሰገን ነው።
በስብሰባው መሪዎቹ የአህጉሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት በፓን አፍሪካ አስቤ በማጎልበት፤ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተደማጭነት ለማሳደግ፤ የሕዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ቀደም ሲል የተጀመሩ ሥራዎችን በተጠናከረ መንገድ ለማስቀጠል የደረሱበት ውሳኔ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።
በተለይም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን ከማጠናከር ጀምሮ፤ በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት የደረሱበት ውሳኔ ከፍያለ ቁርጠኝነትና ብዙ መስራትን የሚጠይቅ የመሪዎቹ የቤት ስራ ቢሆንም በስብሰባው ለጉዳዮቹ የተሰጠው ትኩረት የአህጉሪቱን መጻኢ ተስፋ ታሳቢ ያደረገ ነው።
አፍሪካውያን ከነጻነት ትግሉ ዋዜማ ጀምሮ ስለ ኢኮኖሚ ውህደታቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት ቢጀምሩም፤ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ነገሮች እንዳሰቧቸውና እንደተመኗቸው ሳይሆኑ ቀርተው የተገላቢጦሽ አኅጉሪቱ በግጭቶች ስትናጥ ቆይታለች። በዚህም ሕዝቦቿ ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገደዋል። ለብዙ ሞት፣ ስደትና እንግልትም ተዳርገዋል።
ዛሬም ቢሆን ስለ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት በስፋት በሚነገርበት፣ ጉዳዩ ትልቅ አህጉራዊ አጀንዳ በሆነበት ሁኔታ፣ በግጭት የሚናጡ አገራት ጥቂት አይደሉም፤ ይህ እየሆነ ባለበት አህጉራዊ እውነታ ውስጥ ነጻ የንግድ ቀጣና ለማቋቋም የሚደረጉ ጥረቶች የቱን ያህል በፈተና ሊሞሉ እንደሚችሉ ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ከአብዛኞቹ ግጭቶች በስተጀርባ የውጪ ጣልቃ ገብነት መኖሩ ደግሞ ለችግሩ ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት የአህጉሪቱ መሪዎች፤ ለሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸው፤ በተለይም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል ለአህጉሪቱ ችግሮች አዲስ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ፤ በዚሁ አቅጣጫ በቁርጠኝነት ለመሄድ የደረሱበት ስምምነት የንግድ ቀጣናውን እውን በማድረግ ሂደት ወሳኝ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
የአህጉሪቱን ሕዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ህይወት ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር፤ የአህጉሪቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማስፈን ሰላምና ደህንነት ካለው የማይተካ አስተዋጽኦ አንጻር፤ በጉባኤው የአጉሪቱ መሪዎች ከቀደሙት ጊዜያት ይልቅ ለአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ከንግግር ባለፈ መንቀሳቀስና የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም በአህጉሪቱ ለሚፈጠሩ የትኞቹንም አይነት ችግሮች አፍሪካዊ በሆነ መፍትሄ በውይይትና በድርድር የመፍታትን ባህል ማዳበር፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርባቸዋል። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ስለ አህጉሪቱ ነገዎች እና ስለ መጪው ትውልድ የተሻለ እጣ ፈንታ ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም። ይህንን ደግሞ በአግባቡ ለመረዳት ትክክለኛው ጊዜ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ ለተጀመረው አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ምስረታ ዋነኛ ተግዳሮት የነበረው የሰላምና የደህንነት ጉዳይ በቀጣይም አጀንዳ ሆኖ እንዳይቀጥል ለችግሩ ከፍያለ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶች በቀደሙት ወቅቶች ያስከፈሉንን እና፤ በቀጣይም ሊያስከፍሉን የሚችሉትን ማሰብ፤ በዚህም ተጠቃሚው ማን ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም