አምስተኛ ዓመቱን እያስቆጠረ ያለው ሀገራዊ ለውጥ በብዙ ፈተናዎች እየተናጠ ቢሆንም፤ እንደ ሃገር አዳዲስ እውነታዎችን እንድንለማመድ እድል እየሰጠን ነው። ከነዚህም ውስጥ አለመግባባቶችን በውይይትና በድርድር መፍታት መቻል መምጣታችን አንዱና ዋነኛው ነው።
የለውጥ ወቅት ካለው ውስብስብ ባሕሪያት አንጻር፤ ለብዙ አለመግባባቶች፤ ከዚህ በሚመነጩ ግጭቶችና ሁከቶች የሚጨናነቅበት ሁኔታ ብዙም አዲስ/ እንግዳ ነገር አይደለም፤ በየትኛውም የለውጥ ንቅናቄ በታየባቸው ሀገራት የተስተዋለና የሚስተዋል ነው።
ለውጥ በራሱ በአሰተሳሰቦች ተቃርኖ/ በአሮጌ፤በቆየው እና በአዲስ አስተሳሰብ መካከል/ የሚፈጠር፤ የሚያድግና አቅም ገዝቶ ማኅበረሰብን የሚወርስ ከመሆኑ አንጻር የለውጥ /የአስተሳሰብ ሽግግሩ አልጋ በአልጋ የሚሆንበት አጋጣሚ አይኖርም። ይልቁኑ ብዙ ውጣውረዶች ይጠብቁታል።
በአንድ በኩል የለውጡ አስተሳሰብ የቀደመውን ያለአግባብ ተጠቃሚነቴን ያሳጣኛል በሚል በጠላትነት ፈርጆ የሚንቀሳቀስ ቡድንና/ኃይል መኖሩ፤በሌላ በኩል በለውጡ ወቅት ግራ መጋባቶችን ሥራዬ ብለው በመፍጠር አጋጣሚውን ወደ ሥልጣን መረማመጃ አቋራጭ መንገድ አድርገው ለመጠቀም የሚተጉ ኃይሎች መኖር ለለውጡ ዋነኛ ተግዳሮት ናቸው።
ከዚህ ባለፈም አጠቃላይ ስለሆነው የለውጡ አስተሳሰብና ለውጡ ይዞት ሊመጣ ስለሚችለው ትሩፋት ተገቢውን ግንዛቤ መያዝ ያልቻሉ፤ተገቢውን ግንዛቤ ለመያዝም ፈቃደኝነት የሌላቸው፤ሁሉንም በጥድፊያና በሩጫ ጀምረው ለመጨረስ የሚመክሩ ተጨማሪ ኃይሎች መኖራቸው ለለውጡ ስኬት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርጋቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፍ ለውጥ የቱንም ያህል ከፍያለ ማኅበራዊ ትሩፋት ይዞ ቢመጣም፤ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ከስሜትና ከእልህ በወጣ መንገድ፤በስክነት መምራት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ አለመቻል ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የከፋና ሃገርንና ሕዝብን ሊፈትን የሚችል ነው።
የለውጡን የአስተሳሰብ መሠረት በማኅበረሰብ ውስጥ እንዲሰርጽ ከማድረግ ጀምሮ ፤የለውጡ ትርክት ”ከአሸናፊ ተሸናፊ ”የቡድን ጩኸት ወጥቶ ሃገርንና ሕዝብን አሸናፊ ወደ ሚያደርግ አስተሳሰባዊ መሠረት መሸጋገር ይኖርበታል።
ይህ አይነቱ የለውጥ ጉዞ በባሕርይው/ከተገዛበት የአስተሳሰብ መሠረት/ብዙ ዋጋ መክፈልን፤ በተጨባጭም ሕዝባዊነትን የሚጠይቅ ነው። ከራስና ከቡድን ፍላጎት ወጥቶ ሀገርና ሕዝብን ማስቀደም የሚያስችል እውነተኛ ተቆርቋሪነት የሚፈተንበትም ነው ።
በተለይ እንደኛ አይነት “በአሸናፊ ተሸናፊ” ትርክት ረጅም ዘመን ላሳለፉ፤ትርክቱ የፖለቲካ ባህላቸው አልፋና ኦሜጋ ሆኖ ለሚሰማቸው ፖለቲከኞች፤ ሃገርንና ሕዝብን አሸናፊ ወደሚያደርግ አዲስ የፖለቲካ ባህል የሚደረግ ሽግግር ግራ መጋባትና ግርምት መፍጠሩ የማይቀር ነው።
በተለይም በለውጥ ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በኃይል ከመድፈቅ ይልቅ በድርድርና በውይይት በመፍታት ፤ ለውጡን ዘላቂ አድርጎ ለማስቀጠል የሚወሰዱ እርምጃዎች፤ የለውጥ ኃይሉ ለለውጡ ያለውን ቁርጠኛነት በተጨባጭ አመላካች ናቸው።
በእኛም ሀገር የለውጥ ኃይሉ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ፤የሚያጋጥሙ ችግሮችን በድርድርና በውይይት ለመፍታት የሄደባቸው ርቀቶች በመላው ሕዝባችን፤ ከዚያም አልፎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ተቀባይነትንና ከበሬታን አትርፏል።
የተፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ካለመረዳትና እና ቀደም ባለው ወቅት ለድርድርና ለውይይት ከነበረው የተዛባ አመለካከት የተነሳ አንዳንድ ወገኖች ዕድሉን መጠቀም እንዳይቻል በማድረጋቸው ሃገርና ሕዝብ ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆኗል።
ይህም ሆኖ ግን የለውጥ ኃይሉ እያጋጠሙ ያሉ ሃገርን እንደ ሃገር የሚፈትኑ ከባባድ ጉዳዮችንና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር እየፈታበት ያለው መንገድ ፤ሃገርና ሕዝብ አላስፈላጊ ዋጋ እንዳይከፍሉ ትልቅ ሀገራዊ አቅም መሆን ችሏል።
ችግር ፈጣሪዎች ሆኑ የችግር ነጋዴዎች በተናበበ ሁኔታ ሃገርን በማተራመስ ፤በሕዝብ ጭንቀት ፤ የልብ ስብራት ፤መከራና ስቃይ ለመቆመር የሚያደርጉትን ጥረት፤ ምኞትና ሟርታቸው ፍሬ እንዳያፈራ አድርጓል። ሕዝባችን በእያንዳንዱ የሴራ ትርክት የተሸከመውን ሸክም እንዲያራግፍ እና እፎይ እንዲል አስችሎታል ።
ከሁሉም በላይ እንደሃገር “ከአሸናፊ ተሸናፊ” ትርክት ወጥተን በውይይት እና በድርድር ችግሮቻችንን እየፈታን ወደ ምንመኛቸው ነገዎች መሻገር እንደምንችል ዓይናችን ተከፍቶ ማየት እንድንችል የተሻለ እድል ፈጥሯል!
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም