ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት ነበር? እንደተለመደው ሳምንቱን በትምህርት እና በጥናት እንዳሳለፋችሁ እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም እናንተ ጊዜያችሁን በአግባቡ የምትጠቀሙና በትምህርታችሁ የማትደራደሩ መሆናችሁን ስለማምን ነው።
ልጆች ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ተወርተው የማያልቁ በርካታ የጀግንነትና የሰማዕትነት ታሪኮች ያሏት በርካቶች የሚመኟት ውድ ሀገር ናት። ከእነዚህ በርካታ ታሪኮች መካከል ዛሬ በመከበር ላይ ያለው የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ታሪክ አንዱ ነው። ልጆች ስለሰማዕታት ቀን ምን ያህል ታውቃላችሁ? በዛሬው ፅሁፋችን ስለ ሰማዕታት ቀን ታሪክና ለምን እንደሚከበር እነግራችኋለሁ።
በ1879 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ደግሞ የካቲት 23 ቀን በ1888 ዓድዋ ላይ የጣሊያንን ጦር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት በማሸነፍ ድል አስመዝገበ፣ ድሉ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ድል ተብሎ የኢትዮጵያ ዝና በዓለም ናኘ። ጣሊያንም የሽንፈት ካባ ተከናንባ የኢትዮጵያን ምድር ለቃ ወጣች። የጣሊያን ዓድዋ ላይ መሸነፍ ያበሳጫቸው አውሮፓውያን ሀገራት ኢትዮጵያን ለመበቀል የተለያዩ ሴራዎችን ጠነሰሱ። ከእነዚህ ሴራዎች ውስጥ በ1898 ዓ.ም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ለንደን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር እንድትተዳደር መወሰናቸው አንዱ ነበር።
በ1928 ዓ.ም በእዚያ ዘመን በተፈፀሙት የወረራ ታሪኮች ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጣልያን ግዙፍ ኃይሏን አሰልፋ ኢትዮጵያን ድጋሚ ወረረች። ከመሬት በታንክ፣ በመድፍና በመትረየስ፣ ከአየር ቦምብ በሚጥሉ እና የመርዝ ጋዝ በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨፈጨፉ። ጊዜው የዓለም መንግሥታት ማህበር (League of Nations) ተመስርቶ የነበረበት ነበርና ኢትዮጵያ ለዚሁ ድርጅት ወረራው ተገቢ አይደለም ብላ አቤት ብትልም አጋርነት ካሳዩ ጥቂት ሀገራት ውጭ ሰሚ ማግኘት አልቻለችም።
ይሁንና የዓለም መንግሥታት ድርጅት (League of Nations) ከተመሰረተ ከአምስት ዓመታት በኋላ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦርነት ጀመረች። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትና አርበኞች ሀገርን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያንን ድርጊት አዲስ ለተቋቋመው የዓለም የመንግሥታት ድርጅት ለማመልከት ወደ ውጭ ሀገራት ቢሄዱም ሕግና ሉዓላዊነት በወቅቱ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ባለመሆናቸው ኢትዮጵያውያን የነጻነት ተጋድሏቸውን አጠናክረው ቀጠሉ።
የኢትዮጵያ ጦር ሀገሩን ላለማስደፈር ጠላትን በሰይፍና በጎራዴ ጭምር ተፋለመ። ነገር ግን የጣሊያን ጦር ይጠቀም የነበረው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ድረስ እንዲዘልቅ ረዳው። ጣሊያን አዲስ አበባ ድረስ መዝለቅ ቢችልም ኢትዮጵያውያን ግን በጠላት ጦር ላይ ጥቃት መሰንዘርን አላቆሙም ነበር። በዱር በገደሉ እና በዋና ዋና ከተሞች ከፈጸሟቸው ጥቃቶች መካከል አንዱ በግራዚያኒ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ዋናው ነበር።
ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ስለጣሊያን ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ልጅ መውለድ ደስታ ለማብሰር በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አዳራሽ ሹማምንቱንና ሕዝቡን ሰበሰበ። በዝግጅቱ አብርሃም ደቦጭ፣ ሞገስ አስግዶም፣ ስምኦን አደፍርስ፣ ስብሃት ጥሩነህ እና ሌሎች ወጣቶች ቦንብ ይዘው ወደ ስብሰባው ገቡ። በተለይ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም በኤርትራ በነበሩበት ወቅት የጣሊያን መንግሥት በኤርትራ ሕዝብ ላይ ይፈጽም የነበረውን ግፍ ያውቁ ስለነበር ከፍተኛ ቁጭት ነበረባቸው።
ወጣቶቹ ወደ አዳራሹ እንደገቡ ግራዚያኒ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለ አርበኞች እና ስለ ንጉሡ በንቀት ይናገር ነበር። ወጣቶቹ በግራዚያኒ የንቀት ንግግር እና በስብሰባው ውስጥ በታደመው ተሰብሳቢ ተናደዱ፤ ወደ ግራዚያኒ ቀስ ብለው በመጠጋት ሰባት ቦንቦችን በተከታታይ ወረወሩ። ተሰብሳቢው የመጀመሪያው ቦንብ ፍንዳታ የደስታ ርችት መስሎት ስለነበር አልተደናገጠም። በሁለተኛው የቦንብ ፍንዳታ ግራዚያኒ ተመትቶ ከብዙ ቦታ ላይ ቆሰለ፤ የጦር ኃይል አዛዥ የነበረው አውራሊያ ሊአታ አይኑ ጠፋ፤ እግሩም ተቆረጠ። ሌሎች ሹማምንትም ሕይወታቸው አለፈ። ወጣቶቹ ቦንቡን ወርውረው እና አዳራሹን አተራምሰው እንደወጡ በጓደኛቸው ከአዲስ አበባ ወደ ፍቼ በማቅናት ከአርበኞች ጋር ተቀላቀሉ።
በአብርሃም ደቦጭ እና በሞገስ አስግዶም በተሞከረበት የግድያ ሙከራ የተበሳጨውና የፋሺስትን ጦር የሚመራው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 14 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ከ30 ሺህ በላይ ሠላማዊ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል። ይህንን ተከትሎም በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለመዘከር የካቲት 12 በብሔራዊ ደረጃ እንዲዘከር በ1934 ዓ.ም ታወጀ። በ1951 ዓ.ም ደግሞ 6 ኪሎ አካባቢ የሚገኘው እና 28 ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገረው የሠማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል።
የካቲት 12 በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ የሚከበርና በሶስት ቀን ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታችውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ያስከበሩ ሰማዕታት የሚታወሱበት እንዲሁም የሚዘከሩበት ዕለት ነው። ይህንን ቀን ሰዎች በጋራ ተሰብስበው ስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት ጋር አርበኛ የነበሩ አባቶች እና እናቶች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
እንግዲህ ልጆች የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ተብሎ የሚከበርበት ምክንያት ይህንን ይመስላል። ሀገራችን በርካታ ታሪኮች ያላት እንቁ ሀገር ናት፤ እነዚህን ታሪኮች ደግሞ ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። የዛሬው መልዕክቴም ይህ ነው፤ የሀገራችሁን ታሪክ መፃሕፍትን በማንበብ ወይም ታላላቆቻችሁን በመጠየቅ ለማወቅ ሞክሩ እያልኩ በዚሁ ላብቃ ሳምንት በሌላ ጽሁፍ እስከምንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2015