የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና በዓለም አትሌቲክስ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በአንጋፋነቱ እና በፈታኝነቱ የሚጠቀስ ነው። እኤአ ከ1973 ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናው ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፤ እኤአ ከ2011 ወዲህ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሆኗል። ይህም የሆነበት ምክንያት በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድሩ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በመቆጣጠር ያሳዩት የበላይነት ባስከተለው ጫና ነው።
በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በተሳትፎ ታሪኳ ታላላቅ ውጤቶችን አስመዝግባለች። በኦሊምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶች የተገኙትም ከፈታኙ የአገር አቋራጭ ሩጫ እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው እንዳላት ስኬት አስተናጋጅ ለመሆን አልታደለችም። በአንፃሩ ኬንያ ቻምፒዮናውን በማስተናገድ የመጀመሪያዋ ምስራቅ አፍሪካዊት አገር ናት።
ዩጋንዳን፣ ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እንዲሁም ኬንያ በ2007 የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል። ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ያስተናገዱ ከተሞች ሲሆኑ፤ አሜሪካም ከአንድ ጊዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች። ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናን አስተናግደዋል። በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እድሏ ሰፊ ቢሆንም አልተሞከረም ወይም አልተሳካም። የዓለም አትሌቲክስ ከ1 ዓመት በፊት ዘንድሮ በአውስትራሊያ ከሚካሄደው ቻምፒዮና በኋላ ቀጣዮቹን አስተናጋጅ አገሮች አስታውቋል። በ2024 45ኛውን ቻምፒዮና የአውሮፓዋ ክሮሽያ ስታስተናግድ፤ በ2026 ደግሞ 46ኛውን ቻምፒዮና አሜሪካ ታዘጋጃለች።
ኢትዮጵያ ባለፉት 43 ዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች 275 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። በ2019 በዴንማርክ አርሁስ የተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናም የኢትዮጵያ ቡድን በ5 የወርቅ በ3 የብርና በ3 ነሐስ በአጠቃላይ በ11 ሜዳልያዎች ሰብስባ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ማግኘቷ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ በቻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪክ በአዋቂዎች ምድብ የአጭርና ረጅም ርቀት ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት የመጀመሪያው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው። ቀነኒሳ በአጭር ርቀት 4 ኪሎ ሜትርና በረጅም ርቀት 12 ኪሎ ሜትር ውድድሮች በ5 ቻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን እኤአ በ2008 በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል። በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና በአዋቂዎች ምድብ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ጥሩነሽ ዲባባ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ዋናዎቹ ናቸው። ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት 1 ጊዜ በማሸነፍ ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ትልቁን ውጤት አስመዝግበዋል።
በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና የመጀመሪያውን የሜዳልያ ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊ አትሌት በአዋቂዎች ምድብ በወንዶች የ 12 ኪሎ ሜትር ውድድር መሐመድ ከድር ያስመዘገበው የብር ሜዳልያ ሲሆን ጊዜው እኤአ በ 1981 ነው። አትሌት መሐመድ ከድር ከዓመት በኋላም በ1982 በተመሳሳይ ረጅም ርቀት አሸንፎ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል። በአዋቂ ወንዶች የ 12 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን እኤአ ከ2002-2008 በተካሄዱት የዓለም ቻምፒዮናዎች ነው። ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ደግሞ መሐመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል።
በአዋቂ ሴቶች የ 8 ኪሎ ሜትር የረጅም ርቀት ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ ሜዳልያ የተገኘው እኤአ በ1991 ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው። የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ እኤአ በ1995 ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 እና በ2000 ማሳካት ችላለች። በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም በወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል።
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች። በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የዓለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ መሪነቱን ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ 14 ወርቅ ሜዳሊያዎች በሴቶቹ ምድብ አንደኛነቱን ይዛለች። በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና የተሳትፎ ታሪካቸው ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት የኢትዮጵያ አትሌቶች ክብረወሰኑ አላቸው። እነሱም ሃይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2015