ትዝታና ስንብት

“በድንገት ያለፈውን ጊዜ በትዝታ

ባስበው ተጉዤ ወደኋላ

እንባ ባይኔ ሞላ”

ይህ የትዝታ እንባ ደርሶ ዛሬ ላይ እኛኑ ሆድ ሊያባባን ይመስላል። መሄድ በራሱ አንድ ሆድ የሚያስብስ ነገር አለው። ትዝታን ጥሎ መሄድ ደግሞ ይባስ ፍቅር የወለደው መከፋት ይወራል። በትዝታ ዳር ድንበሩ ሁሉ ሰፍሮ፣ ለዘመናት ስሜታችንን ሲንጠው ከቆየ በኋላ አሁን በቃኝ ስንብትን ሽቻለሁኝ ሲለን ጊዜ ባር ባር ቢለን እውነት አለን።

ከእንግዲህ ወዲያ ከአዳዲስ ትዝታዎች ጋር ልንመለከተውና ልናደምጠው እንደማንችል እያሰብን በሀሳብ ትዝታ ብንብከነከን ግድ የሆነው እውነታ አንዳች ጎዶሎ ስሜት ሊጥልብን ሁሉ ይችላል። ምክንያቱም ትዝታን የምንወድ ሁሉ ንጉሷን ከፊታችን ለማጣት አንፈልግምና። በትዝታ ነግሦ ያነገሣት ጌታዋ ግን በቀሪ ዘመኑ እፎይታን ተመኝቷል። ግን ትዝታ አባዜ ናትና እንዲሁ እንደዋዛ በይ ደህና ሁኚ ለማለት አይቻልም። ቀኑ ሲገፋ ደግሞ ትዝታ ታይላለች።

እድሜ ከኋላ ተነስቶ ድክ ድክ ሲል፣ ወደ ጀንበር መጥለቂያ ሲገሰግስ ትዝታውም ይበረታል። ኖረው ኖረው አመሻሹ ላይ ከተራራው አናት የምትታየው ወርቃማ ጀንበር ልብን በትዝታ ታላውሳለች። የመጡበት መንገድ፣ ያለፉት ትናንት ዛሬ ላይ ቆመው በትውስታ የሀሳብ በረሃ ሽቅብ እየወጡ፣ ቁልቁል መውረድ ነው።

ትዝታ ጣፋጩ የምናብ ፈገግታና ስቅታ ናት። ማንም ሊመለከታት የማይችል፣ የብቻችን የሆነች የሰላም ውቅያኖስ፣ የህይወታችን አድማስ ናት። እዚህ ከራስ ጋር በትዝታ ሲነጉዱ ልባችን በሀሴት ይጥለቀለቃል። አዕምሯችን በፈገግታ ይፍነከነካል። ኋላ ዞረን በሄድንበት ሩቅ መንገድ ፊት አሻግረን እንመለከታለን።

ሰማይ ከደመና፣ ተራሮችም ከምድር አይጋርዱንም። ታዲያ በዚህ ዓለም ላይ መንግሥት ማለት ከመታደል ሁሉ በላይ ነው። ይሄው ንጉሥ ግን ዙፋኑን ማውረስ ተመኘ።

ስሙን ሳይጠሩ ይህን ንጉሥ ካላወቁ እርሱ “ዝምታ ነው መልሴ” ሲል እኔም “ትዝብት ነው ትርፉ” ብል እውነት አለኝ። ትዝታና ፍቅርን፣ ህይወትና ሙዚቃን እንደ ጢቢኛ በአንድ ጠፍጥፎ ያበሰለ፣ እንደ መሀሙድ አህመድ ያለውን ፈልጎ ለማግኘት የሚቻል አይመስለኝም።

ትዝታ ከአራቱ የሀገራችን የሙዚቃ ቅኝቶች አንደኛዋ ናት። ትዝታ ከዘመነ መሀሙድ አስቀድማ የነበረች ናት። ትዝታን ያላንጎራጎረ እውቅ ድምጻዊ የለም። ታዲያ ግን ከዚህ ሁሉ ነገር መሃል አልፎ የትዝታው ንጉሥ መሀሙድ አህመድ የሆነው እንዴትስ ነው? እርግጥ ነው ከመሀሙድ በፊት አስቀድማ ትዝታ ተወልዳ ነበር። ግን መሀሙድ ላይ ደርሳ ዳግም በእርሱ መወለድ አማራት። ዘመናይ ሆና ከዘመኑ ጋር መሽቀርቀርን ስለሻተች “አባቴ ሁን?” ስትል ጠየቀችው።

“ትዝታዬ ለኔ ትዝታዬ ላንቺ

የሚሏት ዘፈን የሚሏት ዘፈን

ታጫውተኛለች ብቻዬን ስሆን”

በቃ እርሱም ያለ እርሷ ለመኖር የማይቻለው መሆኑን ገለጸላት። እርሱ ሙዚቃን ብሎ አንድ እርምጃ ባነሳ ቁጥር ሁሉ ፊቱ ድቅን የምትለው ትዝታ ናት። ይሄዳል በትዝታ። ይቆማል አሁንም በትዝታ። ደግሞ ጥቂት ያስብና ቃል ያወጣል በዚህቹ ትዝታ። መነሻውም፣ መድረሻውም እሷ ብቻ ናት።

“በትዝታ ቅኝት በሀሳብ ተጉዤ

ይሄው ለዚህ በቃሁ

ስንቱን ነገር ይዤ”

ይሄው ነው ህይወት ሙሉ ትዝታው። ይሄው ሰው ነው ዛሬ ከትዝታ ደጃፍ መሄዴ ነውና ስንብቴን ባርኩልኝ ያለው። አዲስ ነገር ሳንጠብቅ በሰጠን ብቻ ስናንጎራጉር ልንኖር ነው። እድሜ የሚሏት አጭር ገመድ፣ እርጅና የሚሉት ክፉ መንገድ መጥቶ ፊት ተደነቀረና መድረክ ለቆ፣ ትዝታን ተሰናብቶ መሄዱ ግድ አለው። “ምነው ትዝታ ሲሄድ አንቺም ጨክነሽ ዝም አልሽ?” ቢሏት “መሸ በሩን ዝጉት ከቀረ ልማዴ፤ እርሱንስ ስሸኘው ቅር እያለው ሆዴ” ነበር ምላሽዋ።

ታዲያ ይህ ሁሉ ስንብት ምንድነው? ወዴትስ ነው ሽኝቱ? የሚሸኝስ ማነው? ጉዳዩ እንግዳ ነው። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለውን የስንብት አጀብ ሰምተንም ሆነ ተላምደን አናውቅም። ከሁለት ሳምንት በፊት ግን የሰማነው ይህንኑ ነበር። እንደሚታወቀው የክብር ዶክተር አርቲስት መሀሙድ አህመድ ትዝታውን አዝሎ በሙዚቃው የተራራ አናት ሲወጣ፣ በሃሳብ ስምጥ ሸለቆ ሲንደፋደፍ፣ በኮረብታው ሲያስተክዘን ደግሞ በሜዳው ፈገግ ሲያሰኘን፣ በስሜት ጫካው አብሮ ሲያስማስነን እልፍ የትዝታ ዘመናት አልፈው እርሱም ድክም ብሎታል።

እድሜው እየገፋ በእርጅና ወጥመድ ስር ለመውደቁ አናቱ ላይ የሰፈሩት ሽበቶች ይናገራሉ። ካደለን ሁላችንም ተያይዘን ወደዚያው ወደሚሄድበት ነን። እርሱ ግን የሙዚቃን ዳገት ከዚህ በላይ የመውጣት አቅሙ በመሟጠጥ ላይ ስለሆነ ቀሪ ዘመኑን በእረፍት ለማሳለፍ ወስኗል። ከሙዚቃው ውጣውረድ ተገሎ ለራሱ ህይወት፣ ራሱን የሚያደምጥበት የዝምታ ጊዜ አስፈልጎታል። ደግሞም ያስፈልገዋል።

ግን ውለታው ከንቱ፣ ድካሙም መና፣ መልሱም ዝምታ እንዳይሆን አድናቂ ወዳጆቹ አልፈቀዱለትም። ብዙዎች ያላገኙትን ትልቅ ዕድል አግኝቶ በህይወት ሳለ ወግ ማዕረጉን ሊያይ ነው። እናም እስከዛሬ ድረስ በሙዚቃ ህይወቱ ላበረከትልን ምስጋና፣ ለውለታው ታላቅ ክብር፣ ለቀሪ ዘመኑ መልካም ምኞታችንን ገልጸን፤ እርሱን ለመሰናበት የታሰበ ልዩ ዝግጅት የሚጠብቀው ጥር 3ቀን2017 ዓ.ም ነው።

ታላቁ የጥበብ ሰው የቀሪ ዘመን የእረፍት ሻንጣውን ሸክፎ ለስንብት ሲሰናዳ በዝምታ የሚተወው የለም። ትክክለኛው ነገር በትክክለኛው ሰው ተጀምሯል፤ ያለፈው የሚያሳዝን ቢሆንም። ይህን መሰል የስንብት መድረክ ለማዘጋጀት እድሜ ጌታው ነው። በሥራ ላይ ናቸው ብለን “አሉ…አለሁ” እያሉም ድንገት አለመኖር ይከሰታል። በጉብዝና ወራት ላይ ያለውን “እንሰናበትህ” ሊሉት ስለማይችሉ ስንብቱም መቃብር ላይ በጉንጉን አበባ ይሆናል። ቢኖርም በእድሜ ገና ሳሉ ለተለዩን ጸጸቱ ስንብትን የማያካትት ይሆናል።

ሆኖም ግን በእርጅናም ይሁን በሌላ ወደ መጨረሻው ማክተሚያ መዳረሳቸውን እያወቅን በዝምታ የሸኘናቸውም ቀላል አይደሉም። ለአብነትም፤ ከድምጻዊያኑ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን እንኳን ብንመለከት አሳዛኙን አካሄድ ነበር የሄደው። ሰውነቱ በድን ሆኖ አስክሬኑ ወደ መቃብር ሲሸኝ ቢናገረው ኖሮ ምናልባትም በመሀሙድ ሙዚቃ እንዲህ ባለ ነበር፤

“ለዋልኩት ውለታ ይሄ ነው ወይ ውርሴ

ልፋቴ ድካሜ ይሄ ነው ወይ ውርሴ

እንግዲህ ምን ልበል ይህ ከሆነ ቅርሴ

አሀሀሀ ዝምታ ነው መልሴ”

በእርግጥም የሞተ ሰው ጩኸቱም በዝምታ ነው። ፍርጃም ቢሉት እጣ ፈንታ የዛሬውን ውዳሴ ያገኘውም መቃብር ከዋለ በኋላ ነበር። መሀሙድንም ከሚያብከነክኑት ነገሮች አንዱ ይሄው የጥላሁን ጉዳይ ነው። ታላቁ ድምጻዊ ያጣውንና የተነፈገውን በማስታወስ ምን ያህል እንደሚያንገበግበው ሲናገርም ሰምተን ይሆናል። ይሁንና ለትንሽ ትልቁ አሳቢነቱና ተቆርቋሪነቱ መሀሙድ ዛሬ ላይ እንዲታሰብለት አድርጎታል። “ነግ በኔን” በቅጡ የተረዳ ውለታ አብሳይ ነው።

የክብር ዶክተር አርቲስት መሀሙድ አህመድ የአንድ የራሱ ብቻ የሆነ የጥበብ ሰው አይደለም። ገሚስ ማንነቱና ህይወቱ ዙሪያው ለተሰበሰቡት አድናቂና ወዳጆቹ ነው። እነርሱም ለእርሱ ያላቸው ክብርና ታማኝነት ከየትኛውም ደቀመዝሙር የተለየ ነው። በጥቂቱ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው ኮንሰርቶችን ማጤን በቂ ነው።

ለኮንሰርቱ ታዳሚ ይበቃል ተብሎ የተዘጋጀ የመግቢያ ትኬት ገና በጊዜ እጥብ ብሎ በሽሚያ ለመግባትም የማይቻልባቸው ነበሩ። በጊዜ መፈራረቅ መካከል ሳይለዋወጡና ሳይለወጥ፣ ሲከተሉትና ሲያስከትላቸው ዛሬ ላይ ደርሰው አሁን ደግሞ ለስንብት የተሰናዱለትም እነርሱው ሆነዋል። ሥራ የጋራ ቢሆንም ሀሳብ ግን ከአንድ ጉድጓድ ሊፈልቅ ይችላል። ከሁለት ዓመታት በፊት እኚሁ አድናቂ፣ ወዳጆቹ ሰብሰብ ብለው አንድ ሀሳብ ከሰቱ። “ሁላችንም በግልጽ እንደምንመለከተው ጋሼ እድሜው ገፍቶ፣ ከእረፍት ዘመኑ ላይ ተቃርቧል። ስለዚህ አንድ የስንብት መድረክ ብናዘጋጅስ” የተባባሉ ይመስለኛል።

ይሄን መሰሉ ቅዱስ ሀሳብ የማይታለፍ ነበርና በሀገራችን ያልተለመደ ቢሆንም በውሳኔ ቆርጠው ገቡበት። የወተት ላምን ከወደዱ ከነኩበቷ ነውና ሊገጥማቸው የሚችለውን ከነ ፈተናው ለመቀበል ተዘጋጅተው ገቡበት። ጥቂቶችም ተመራርጠው ኮሚቴ አዋቀሩ። “ይህን ጉዳይ ይዘን የተለያዩ ሰዎች ጋር ስንሄድ ምን ሆነ መሀሙድ ሲሉ ይጠይቁናልና ለመከበር ምንም መሆን የለበትም። ጋሽ መሀሙድ እኮ ታላቁን የሚያከብር ሰው በማይገኝበት ዘመን ታናሹን የሚያከብር ሰው ነው” ሲል ከኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ የሆነው፣ እውቁ የሙዚቃ ባለሙያ አብርሃም ወልዴ ነበር የተናገረው።

እናም ያሰቡት ሰምሮ፣ የዘሩት አሽቶም ከሁለት ዓመታት ድካም በኋላ በጥር 3 ቀን እውን ሊሆን ነው። የልፋትን ፍሬ መብላት እንዴት ያለውን ሀሴት የሚቸር መሆኑን ከእነርሱ የተማሩም ነገ በሌላ ታላቅ ሰው መቀጠሉ አይቀርም። እነርሱ ግን ፊተኞች ሆነው አስቀድሰውታል።

“የክብር ዶክተር አርቲስት መሀሙድ አህመድ ከክብር ክብር! ክብር! ክብር! ይገባዋል በማለት አድናቂና ወዳጆቹ ተሰባስበን ኮሚቴ በማዋቀር ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ስንሠራ ቆይተናል” በማለት የሁለቱን ዓመታት ጉዞ፣ የአሁኑን መዳረሻና የስንብት መጀመሪያውን ኮሚቴው አስቀምጦታል። ለአርቲስቱ ስንብት ደፍ ደፍ በተባለባቸው በእኚህ ሁለት ዓመታት ምንስ ታሰቦ፣ ምን ተሠራ? ሁሉንም ነገሮች ጉዟቸው ወደ ጥር 3 ነው።

ከተሠራባቸው ነገሮች አንዱ የስንብት ኮንሰርት ነው። ኃላፊቱን ከኮሚቴው ወስዶ በሰፊው ሲንቀሳቀስበት የቆየው ጆርካ የሁነት አዘጋጅ ተቋም ዝግጅቶቹን በጥራት ስለማገባደዱ ጥቅምት 22 ቀን 2017ዓ.ም ከኮሚቴው ጋር ሆኖ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል። በሁለተኛነት የታላቁን የጥበብ ሰው የህይወት ታሪክ የሚዳስስ መጽሐፍ ሥራው ተጠናቆ ለንባብ የሚበቃ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን የህይወት ታሪክ ጽፎ የነበረው ጋዜጠኛና ደራሲ ወሰን ደበበ አሁን ደግሞ የመሀሙድን ህይወት ከልጅነት እስከ ሽበት፣ እንዲሁም የሙዚቃ ህይወቱን በሰፊው የሚተርከውን መጽሐፉን አጠናቆታል። በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ሲለፋባቸው የከረሙ ሌሎች ሦስት ጉዳዮች ደግሞ መጨረሻቸውን በጥር 3ቱ መድረክ ይፋ የሚደረጉ መሆናቸውን ኮሚቴው ተናግሮታል።

በመንግሥት ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቶ ስፍራ ያልተወሰነለት አንደኛው ጉዳይም በስሙ መንገድና አደባባይ ማሰየም ነው። ምናልባትም ደግሞ “መሀሙድ ጋር…” እንደሚሆን ይጠረጠራል። በሂደት ላይ ያለው ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ምስለ ቅርጽ ማቆም ነው። በህይወት ሳለ ይህን የራሱን ምስለ ቅርጽ ቆሞ የተመለከተ ዕለት ለርሱም ለሌላውም ትልቁ የህይወት ዘመን ስኬት ይሆናል። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ መሀሙድስ ተቀብሎ ብቻ ሊወርድ? አያደርገውም! በእርግጥም አላደረገውም። የመጨረሻውን የሙዚቃ ስጦታ፣ የትዝታውን መታወሻ ሲዲ ያበረክትልናል። ለዕለቱ መድረስ አለመድረሱን ኮሚቴውም እርግጠኛ ባይሆንም አዲሱን ገጸ በረከቱን በቅርቡ ልናደምጥ መሆኑ ግን እሙን ነው።

ጥር 3 የትዝታውን ንጉሥ በክብር ለመሸኘት ወገቧን ታጥቃ፣ መቀነቷን አስራ ከወዲሁ ሽር ስትል እንዳለች ታሳብቃለች። ሁሌም መታወሻው ሆና ስለምትኖር ለርሷም ቢሆን ትልቅ ዕድል ነው። ከቀናት ሁሉ ልዩ ቀን ለመሆን በመብቃቷ ኩራትም ደስታም እንዳፈናት ግልጽ ነው። ከአመሻሹ ላይ ግን የእንባ ሲቃ ሳይተናነቃት አይቀርም። ስንብቱ ብቻ ሳይሆን እንዲያ ፈክታ የዋለችባቸውን ሰዓታት ጥር 4 ደርሶ ሊቀበላት መቃረቡን ስታስብ የእውነትም ቅር ሊላት ይገባል።

ጥር 3 ቀን 2017ዓ.ም ሚሊኒየም አዳራሽ፣ መሀሙድና ጥር 3 ትልቁ የዘመን ግጥምጥሞሽ ይሆናሉ። ዕለቱስ ምን ያስመለክተን ይሆን? መሀሙድ የዚያን ዕለት መድረክ ቆሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትውልዱን ይሰናበታል። ጥበቡን ከአደራ ጋር ያወርሳል። የተሰማውንና ለዘመናት ሲሰማው የነበረውን ይናገራል። ብዙዎች ከአዳራሹ ሆነው በደስታ ወይ በእንባ ያደምጡታል። የሚናገረውን ተናግሮ፣ የሚመክረውን መክሮ፣ የሚዘክረውን ይዘክራል። ትዝታውን እያወጋን፣ ትዝታውን ጥሎብን ይወርዳል።

ዝግጅቱ ለመሀሙድና የመሀሙድ ቢሆንም ብቻውን ተናግሮ፣ ብቻውን ዘፍኖ፣ መድረኩን ለብቻው አይጨርሰውም። ሌሎች ዝግጅቶች እንዳሉ ሆነው በዕለቱ ከሚቀርቡት አንዱ ሙዚቃ ካልሆነማ የስጋ ነጋዴውን ሰርግ በሽሮ እንደመሰረግ ነው። ከዳቢቱም፣ ከምላስ ሰንበሩም፣ ብርንዶውን ካልቆረጡማ ምኑን ተሰረገ…ታዲያ እነማን ይሆኑ የተመረጡት ሚዜዎች? ብለን ማሰባችን አይቀርም። ይሁንና የኮንሰርቱ ቀኛዝማች ጆርካና የድግሱ ፊታውራሪው ኮሚቴ በይደር ይዋል ሲደርስ እንገልጸዋለን ብለዋል።

ነገር ግን የሙዚቃ ድግስ ስለሆነ ብቻ ማንም ና! ውጣ የሚባልበት መድረክ አለመሆኑን አበክረው ተናግረውታል። “ራሱን መሀሙድን የሚመጥን ድምጻዊ ሊሆን የግድ ነው” ሲሉ ይበልጥ መድረኩ ላይ የሚወጣውን ድምጻዊ ጓጉተን እንድንጠብቀው አድርገውታል። እነርሱ እንዲያ ቢሉም መገመት አያስነውርምና እኛ ግን አንደኛውን እንገምታለን። የመገመቱን ዕድል ከሰጣችሁኝ ዘንዳ ምናልባትም ከመሃከል አንደኛው ጎሳዬ ተስፋዬ ይሆናል እላችኋለሁ። እንዴትስ እሱን ልትል ቻልክ ያላችሁ እንደሆን ግን…ድምጻዊ ጎሳዬ የተቀዳው ከመሀሙድ አህመድ የትዝታ ወንዝ ላይ ነው።

ከላይ መግቢያው ላይ መሀሙድ ከጀመራት የትዝታ ስንኝ ጎሳዬ ይቀጥልባታል።

“…ይቅርና ማሰብ በትካዜ

አጫውተኝ ስላለፈው ጊዜ” ይለዋል።

ትዝታን በአደራ፣ ጥበብን በፍቅር እንጀራ ይጎራረሳሉ። ጎሳዬ ለመሀሙድ ጋቢውን ሲደርብለት ያለችዋንም ቅጽበት አንረሳትም። አንዱ ጥበብ አውራሽ፣ ሌላውም ክብር አልባሽ ነው። ጥር 3 ግን ሚሊኒየም አዳራሽ ጀንበር አትጠልቅም።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You