19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል። ቀኑ የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጎሉና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበርም አስታውቋል።
ታዲያ ህብረ ብሄራዊነት አንድነት ሲባል ምን ማለት ነው፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታስ ይህን እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል?
የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ህብረ ብሔራዊነት ማለት ብሔሮች በጋራ፣በህብር ሆነውና በአንድነት ተሰናስለው የሚኖሩበት ሥርዓት ነው ይላሉ።
ህብረ ብሔራዊነት እራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን በውስጡ አለው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ብሔሮች የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ የሚያሳድጉበት ፖለቲካዊ ሥልጣንን የሚያጎናጽፍ መሆኑንም ይናገራሉ።
የህብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ ሥርዓት የተለያዩ ብሔረሰቦች ህብር ፈጥረው ትልቅ ሀገር እንዲመሰርቱ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እውቅና የሰጠና የሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን ደንግጓል። ሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት የምትከተል በመሆኑ ለብዝሃነት እውቅና መሰጠቱን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር በመሆኗ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ተሰጥቶት ክልሎች መደራጀታቸውን የሚገልጹት ኃይለኢየሱስ (ዶ/ር)፣ነገር ግን የፌዴራሊዝም ሥርዓት በባህሪው ለህብረ ብሔራዊ ሀገራት ውስብስብ ነው ይላሉ።
ብዝሃ ብሔር ያለበት ሀገር ብዝሃ የሆነ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንዳለበት ገልጸው፤ ጥያቄዎቹን በብዝሃነትና በአንድነት መካከል ሚዛን በጠበቀ መልኩ በመመለስ እንደሀገር በጋራ መቀጠል የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ።
የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ መነሻው የአብሮነት እሳቤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ማንነቱን ከብሔራዊ ማንነትና ከራስ አስተዳደር ጋር አስተሳስሮ መሄድ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ።
በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ህብረ ብሔራዊነት ብሔሮች በሚኖሩበት አካባቢ ላይ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደሚሰጥ በመግለጽ፤ ነገር ግን በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይከበር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ያስረዳሉ።
የእኔ ክልል ስለሆነ የእኔ ባህል፣ቋንቋ፣ፍላጎት የሚስተናገድበት ነው የሚል እሳቤ እንደሚፈጠር ገልጸው፤ የራሴ ብቻ ፣እኔ ብቻ ነኝ መጠቀም ያለብኝ ብሎ ማሰብ አግላይ ብሔርተኝነት በሀገሪቱ ውስጥ እንዲታይ ያደርጋል ይላሉ።
በማንነት የተመሰረተ ክልል የራሱ መንግሥት፣ሚዲያ፣የሥራ ቋንቋ፣ባንዲራ ያለው በመሆኑ ለምን የራሴን ሀገር አልመሰርትም የሚል ፍላጎት ሊያሳድር እንደሚችል በመግለጽ፤ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ መኖር የሥርዓቱ ተግዳሮት መሆኑን ያስረዳሉ።
ሀገራዊ አንድነቱን፣ትስስሩን በማጠናከርና የጋራ ትርክትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች መቅረፍ ይቻላል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በኢትዮጵያ ብዝሃነት እንዳለና የሀገር መገለጫ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል ይላሉ።
በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎን ማጠናከርና የወጣ ፍላጎት ያላቸውን ወደ ጋራ እሳቤ እንዲመጡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ እራሱን ለማስተዳደር የተፈቀደለት የክልል መንግስት ዲሞክራሲያዊ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።
ብዝሃነትን የመቀበል አስተሳሰብን ወደ መሀል ማምጣት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣በሀገሪቱ ህብረ ብሔራዊነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዲይዝና ገዢ አስተሳሰብ እንዲሆን መሰራት አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።
መንግሥት በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የሚያጋጥሙ ትግዳሮቶችን እየቀረፈ መሄድ እንዳለበት የሚገልጹት ኃይለኢየሱስ (ዶ/ር)፣ ችግሮችን ሥርዓት በሚያጠናክሩ መልኩ እየፈቱ መሄድና ሥርዓቱን ዜጎች እንዲረዱ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።
የትምህርት ተቋማትም ብዝሃነት የኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑን ተረድተው ብዝሃነትን የሚቀበሉ፣ አብሮ ለመኖር ፍቃደኛ የሆኑ ዜጎችን መፍጠር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ችግሮችን በሕግ አግባብ መፍታትና የሰው ልጅ በጋራ መኖር እንደሚችል መሥራት አለባቸው። በተጨማሪም መሰረታዊ በሆኑ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ በመሆኗ ሀገራዊ መግባባትና የህብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ ናቸው።
ህብረ ብሔራዊነት ራስን በራስ የማስተዳደር፣የተለዩ መብቶችን ማስከበር ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ከማስከበር ጋር አብሮ የሚሄድ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ የራስ ማንነት ውስጥ ሆኖ የጋራ ሀገር መገንባት ግን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ።
ህብረ ብሔራዊ አንድነት በአንድ ሀገር ውስጥ ሁሉም ብሔረሰብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ተከብሮለት ለጋራ ዓላማ እንዲቆም ማድረግ መሆኑን ገልጸው፤ አንድነቱን ማረጋገጥ የሚቻለው በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ያሉ መስተጋብሮችና ግንኙነቶች ትብብርን መሰረት ባደረገ መንገድ በመምራት መሆኑን ይገልጻሉ።
ህብረ ብሔራዊነት በተፈጥሮው ፖለቲካዊ ነው የሚሉት አቶ ትግሉ፤ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ለራስ የተለዩ መብቶችን በሕግ ማስከበር፣ከመወከል ጋር የተገናኙ ጉዳዮች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ህብረ ብሔራዊነት የባህል ብዝሃነትን የሚያሳይ ሳይሆን ራስን በራስ ማስተዳደርን፣ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንን የሚገልጽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአንድ ሀገር መግባባት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ይናገራሉ።
በመጨረሻም እንደሀገር አንድ ለመሆን ህብረ ብሔራዊነት ላይ መግባባት ይጠይቃል ሲሉ ይገልጻሉ።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም