“ኢትዮጵያ ከባህር በር ባለፈ ለውቅያኖስ ባለይዞታነቷም ታሪክ ምስክር ነው” – ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር) በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ከባህር በር ባለፈ ኢትዮጵያ የውቅያኖስም ባለይዞታነቷ የሚታወቅ መሆኑ ታሪክ ምስክር ነው ሲሉ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጥላሁን (ዶ/ር) በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ራሷ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ምዕራባውያንም ምስራቃውያንም ከፍ ሲል ዓለም በሙሉ የሚያውቀው ነው። ከባህር በር በዘለለ የውቅያኖስም ባለይዞታ መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ እኛ የባህር በር ቀርቶ የውቅያኖስ በር ያለን ነበርን። ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር ማዋል ሲያቅታቸው በተለያየ መንገድ እየገዘገዙና በአሳሾች እየሰለሉ፣ የሀገር ጎብኚዎች በመምሰል የሀገር ምስጢር እያወጡ ሲገዳደሩን ኖረዋል። ለምሳሌ በመጀመሪያ በአሰብ አካባቢ ጣሊያኖች የተቆጣጠሩት እና የሰፈሩት በቀላል መንገድ ነበር። በእዛ አካባቢ የነበሩ አንድ ሱልጣን ለዓሣ አስጋሪ ጣሊያናዊ ከአሰብ አካባቢ የተወሰነችን ቦታ መሸጣቸውን ያስታወሱት ጥላሁን (ዶ/ር)፣ ከዚያ በኋላ እንደ ፍልፍል እየፈለፈሉ አሁን ኤርትራ የምትባለውን አካባቢ ጣሊያኖቹ በቁጥጥር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። እሱ ስፍራም ከኤርትራ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ጂቡቲ መጨረሻ ድረስ ያለው ስፍራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን የባህር በር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት በዓለም የመጨረሻ ትልቋ ሀገር ናት። ትልቅ ሕዝብ ይዛ ወደ ባህር መውጫ በር የተነፈገች ሀገር መሆን ችላለች። ከዚያ በፊት ግን ሌላው ቀርቶ ከአፍሪካ በስተ ምዕራብ ያለው አትላንቲክ ውቅያኖስ ራሱ የጥንታዊ ግሪካውያን አሳሾች “ኢቲዮፒክ ኦሽን” የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ብለው ካርታ የሰሩለት መሆኑን ድርሳናት እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን ሕንድ ውቅያኖስን ተሻግራ የዛሬ የመንና ኦማን መሰል ሀገሮችን ከቀይ ባሕር አልፋ አስተዳድራ እንደምታውቅ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። ሕንድ ውቅያኖስ ጭምር የራሷ እንደነበር የትኛውም አካል ከታሪክ መረዳት ይችላል ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You