የአረንጓዴው ወርቅ አምራቾች ተስፋ ፈንጣቂ ውጤት

አቶ ታጠቅ ደምሴ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ በቡና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብት ናቸው።በአሁኑ ጊዜ በ254 ሄክታር መሬት ላይ የቡና እርሻ ልማት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። የቡና ኢንቨስትመንት ስራ አድካሚ፣ ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ ቢሆንም ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምርታቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙት አቶ ታጠቅ፤ የግብርና ባለሙያዎች እስከታች ድረስ ወርደው ከችግኝ አፈላል ጀምሮ ክትትል በማድረግ ለአምራቹ የሚያደርጉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ባለሀብቶች ብቻ በቡና ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ይሰሩ ነበር። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ቡና በጥራት ወደ ማምረት የገባበት ሁኔታ አለ የሚሉት ባለሀብቱ፤ ይህም እንደሀገር የተገኘውን የቡና ምርታማነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያስቻለ እንደሆነና መንግሥትም በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን መቅረፍ ከቻለ የተሻለ ማምረት የሚቻልበት እድል መኖሩን አመላካች መሆኑን ይጠቁማሉ።

አቶ ታጠቅ እንደሚገልጹት፤ በ2012 እና 2013 ዓ.ም በአካባቢው መጠነኛ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች በመኖራቸው ለተወሰኑ ጊዜያት ስራ ተቀዛቅዞ ነበር። በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም ተገኝቶ ሁሉም ሰው ወደ ስራ ገብቷል።ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ፋይዳ ሊያመጣ በሚችል ሁኔታ ቡና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲመረት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ሰፊ መሬት በመያዝና በርካታ ችግኞችን በመትከል ምርታማነት ይገኛል የሚል የተሳሳተ እሳቤ እንደነበራቸው የሚያነሱት ባለሀብቱ፤ በስራው ረጅም ዓመታትን በማሳለፋቸው ከአነስተኛ ማሳ ጥራት ያለው ምርት በማምረት የተሻለ ገቢ በማግኘት ራስንም ሆነ ሀገርን መጥቀም እንደሚቻል መገንዘባቸውን ይናገራሉ።

የትኛውም መሬት ያለው ኢንቨስተር የተሻለ ምርት በማምረት በዓለም ገበያዎች ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚፈልግ የሚጠቁሙት አቶ ታጠቅ፤ ምርታቸውን በማሳደግና ገበያ በማፈላለግ ከሶስት ዓመታት በላይ ቡናን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ያመላክታሉ።

ትክክለኛ ሂደትን ባልጠበቀ መልኩ ማዘጋጀት የቡናውን ጥራት የሚቀንሰው በመሆኑ ከባለሙያዎች የሚሰጠውን ድጋፍ ተከትሎ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ

የሚያነሱት ደግሞ በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ በቡና ምርት ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ጥላሁን ጨዋቃ ናቸው።

በሚኖሩበት አካባቢ ቡና በስፋት የሚመረት ሲሆን፤ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በቡና ምርት ላይ እንደተሰማሩ በማንሳት፤ ከቡና ምርት ከሚያገኙት ገቢ የወለዷቸውን አስር ልጆች አሳድገው ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን ይናገራሉ።

ባላቸው ሶስት ሄክታር መሬት የቡና ማሳ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ለገበያ አቅርበው የተሻለ ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኙ የሚገልጹት አቶ ጥላሁን፤ ይህንን ቋሚ ቅርስ ለልጆቻቸው በማስተላለፍ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ሰርተው የተሻለ ምርት እንዲገኝ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያዎች ከባቢን ሳይጎዳ የተመረተ ቡና እጅጉን ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል። የቡና ማሳን ማብዛት ብቻ ሳይሆን በዓለም ገበያዎች ከሚቀርቡ የቡና ምርቶች ጋር መገዳደር የሚያስችል ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት ያስፈልጋል።

መንግሥት የቡና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት እጅጉን የሚደገፍ ነው። በአተገባበሩ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ለአምራቾች እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ አካባቢው ለቡና ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ሌሎችም መጥተው ማምረት እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ6ኛው ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ለቡና ምርት እና ጥራት መጨመር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በዚህም በቡና ምርት ኢትዮጵያ በዓለም ከብራዚልና ቬተናም በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቡና ምርት ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረበት 500 ሺህ ቶን ወደ አንድ ሚሊዮን ቶን በማሳደግ ግባችንን አሳክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአምናና ከአቻ አምና መካከል የቡና ምርት እድገት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አንስተው፤ ከገቢ አንጻርም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ይህን አሃዝ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ይሰራል። በዘንድሮ ዓመትም ከ450 እስከ 500 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነትም ትርጉም ባለው መልክ እድገት አሳይቷል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን ከዓለም ከፍተኛ ቡና አምራች ሀገራት አንዷ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥት በተጨማሪ ላኪዎች የቡና ምርት ጥራትን ለሚያሻሽሉ ተግባራት ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You