ብዙዎች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሊቅ ብዕራቸውን እያነሱና በቃላት እያሞካሹ ይከትቡለታል። የእውቀቱንም ጥግ እየጠቀሱ በዓለማችን ግዙፍ በሆነው የስፔስ ሳይንስ የምርምር ማዕከል ወይም ናሳ ውስጥ ስለሰሯቸው ስራዎችም በልበ ሙሉነት ይመሰክራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ይህ ሰው ምናባዊ የፈጠራ ትርክት እንጂ በናሳ ውስጥ በጭራሽ አልነበረም ብለው ሲከራከሩ ታይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ‹‹በናሳ ውስጥ ሊሰሩ ይቅርና በበሯ እንኳን አላለፉም›› የሚሉ ወገኖች ሙግት ገጥመው አይተናል፡፡ የዚህ ሰው አወዛጋቢ የናሳ ተመራማሪነትና ክርክር ያስነሳ ማንነት ብዙዎች ያላዩት በአመድ የተዳፈነ ፍም እሳት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊው የናሳ ሳይንቲስት ዶክተር ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ።
የዚህ ሳይንቲስት ሕይወትና ታሪካዊ እውነታው ሚስጥር ለዘመናት ታፍኖ ከርሟል፤ ለምን? ምናልባትም የሰራበት የዓለማችን ትልቁ የሕዋ ምርምር ተቋም ናሳ ሚስጥራዊ ከመሆኑ የተነሳ? ወይንስ ከበስተጀርባው ሌላ ዓላማና ይዘት ያለው ታሪክ ይኖር ይሆን? አንዳንዶች እውነታውን መቀበል ለምን ከበዳቸው? የሳይንቲስቱ ጉዳይ ውስብስብ ሆኖ ከመቆየቱም ባሻገር በሁለት የተለያዩ ዓለማት ያሉ እውነታዎች አንዱ አንዱን በመርታት የእውነትን ዙፋን ላይ ለመቆናጠጥ እርስ በእርስ ሲፋጩ ቆይተዋል። በስተመጨረሻም ዙፋኑ የእውነተኛው እውነት ብቻ ነው። ብዙ የውሸት መቃብሮች አንዲትን እውነት የመቅበር አቅም የላቸውምና ያም ተባለ ይህ እውነታው ግን አንድና አንድ ብቻ ነው። ይሄውም ቅጣው እጅጉ ኢትዮጵያ ሀገራችን የምትኮራበት፣ የናሳ ሳይንቲስት ነበር። ለመሆኑ ይህ ሰው ከየት ተነስቶ የት ደረሰ፣ በሕይወት ዘመኑስ ለአገሩና ለዓለም ምንስ ማበርከት ቻለ፤ እውነታውን ተሞርኩዘን ዝናውን ጥግ ሳንክድ ስለ ሳይንቲስቱ ሕይወትና ስለ ተቀበሩ እውነታዎች ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት፡፡ የዚህ ሳይንቲስት የታሪክ እውነታ ሲጀምርም እንዲህ ነበር። በዚሁ ወር የካቲት 16 ቀን 1948 ዓ/ም በደቡብ ኢትዮጵያዋ ቦንጋ ከተማ ውስጥ ከእናታቸው ወይዘሮ አስካለ በላይነህ እና ከአባታቸው ከአቶ እጅጉ ሀይሌ መወለዱን የሚገልፁ በርካታ መዛግብት አሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በቦንጋ ዋከና ጀምሮ በጅማ ከተማ አጠናቀቀ። በዚህ ወቅት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ከሌላው ተማሪ በተለይ ልዩ ፍላጎትና ወጣ ያሉ የፈጠራ ሙከራዎችን በግሉ ያደርግ እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ። በሒሳብ እና ፊይዚክስ እንዲሁም የኬሚስትሪ ትምህርቶች ላይ የተለየ ፍቅርም ነበረው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጅማ ከተማ ተከታተለ።
የዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ ቀጣዩ ህልም ወደ አውሮፓ ሀገራት በመሄድ ቀሪውን የትምህርትና የሕይወት ዘመኑን እዚያው መግፋት ነበር። ምክንያቱም ደግሞ የትምህርት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሆነ የነጻነትና ትግል የፖለቲካ አቋም ስለነበረው ኑሮን በኢትዮጵያ ለመግፋት አስቸጋሪ ሆኖበት ነበር። ከዚህ በኋላም ወደ ጃፓን አገር በመሄድ በኦሳካ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና የጃፓን ኢኮኖሚ፣ በሄሮሺማ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የኢንዱስትሪ እና የአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ አጥንቶ አጠናቋል። በሀገረ ጃፓን በትምህርት ቆይታው በነበረው የተለየ ችሎታና ከዚያም ወጥቶ በሚሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ከወደ አሜሪካን ሀገር ሌላ የትምህርት እድል እንዲያገኝ ረዳው። እዚያም በመሄድ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪውን ተከታተለ። ቅጣው እጅጉ በሄደበት ሁሉ ተምሮ፣ እለት ከእለት የእውቀቱንም ማዕድ እየቆረሰ ጠግቤያለሁ የሚል ባለመሆኑ አብዝቶ የእውቀትን በር የሚያንኳኳና በስኬቱም የማይረካ የሕይወት ዘመን ተማሪ ነበር። በየሴኮንዱና በየደቂቃው አዳዲስ እውቀትን መሸመትም የሕይወት ፍልስፍናው ነው። ይህም ጥረቱ ለብዙዎች ህልም ሆኖ ወደሚቀረውና ጥቂት የዓለማችን ልሂቃን ብቻ ወደሚገቡበት ወደ ታላቁ የናሳ ግቢ ሰተት ብሎ እንዲገባ አድርጎታል፡፡
በናሳ ውስጥ ባደረገው ቆይታ በሁለት አበይት ዘርፎች በርካታ የምርምር ስራዎችን ማበርከት ችሏል። በዚህም በሲስተም መሃንዲስነትና በጠፈር ሳይንቲስትነት በመቀጠር የናሳ ጉዞውን ጀመረ። ከሌሎች መሃንዲስ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለእኛ ዓለምና ለሌሎች ፕላኔቶች የምርምር ስራ የሚረዱ የጠፈር ላይ መንኩራኩሮችን መፍጠር እንደቻለም የፅሁፍ ማስረጃዎች አሉ፡፡ የሰው ልጅን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር በወሰደው አፖሎ 11 መንኩራኩር ላይም አሻራውን አሳርፏል። ለአንዳንዶች ውሸት እስከሚመስል ድረስም ከፈጣሪ በተሰጠው ልዩ ችሎታና እውቀት በናሳ ውስጥ ሁለት የኤሮ- ስፔስ መወርወሪያ ሜካኒዝምን ለግዙፉ የአውሮፕላን ማምረቻ ለቦይንግ ኩባንያ ለመስራትም በቅተል። ኔክስት ጀኔሬሽን የተሰኘውን ዓለምአቀፍ ሳተላይትን ከፈለሰፉት ሳይንቲስቶች መካከል አንደኛው ዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡ ሌላው ደግሞ ‘ትራንስ ቴክ ኢንተርናሽናል’ በመባል የሚታወቀውን ድርጅት መስራች ጭምር መሆኑ ነው።
አንዳንድ እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ይሄ ትርክት እንጂ ቅጣው የሚባል ሳይንቲስት የለም ሲሉ መደመጣቸው እጅጉን የሚያስገርምም የሚያሳዝንም ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ የቴክኖሎጂና የመረጃ ዘመን ስለዚህ ሳይንቲስት እውነታውን አለማወቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ውሸት ነው ብሎ ሽንጥን ገትሮ መከራከር ግን ትልቅ ስህተት ነው። እንደሚባለው የዚህ ሳይንቲስት ታሪክ ምናባዊ የፈጠራ ትርክት አይደለም። ለዚህ እውነታ በቂ ማስረጃዎች ማግኘት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህልም የናሳ ሳይንቲስቶች በሚሞቱበት ወቅት ታሪካቸው የሚሰፍርበት የበይነ መረብ ባህረ መዝገብ አለው። በዚህ መዝገብ ላይም ዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ በናሳ ውስጥ በስፔስ ሳይንስ ዲፓርትመንት የጀት ፕሮፔልሽን ተመራማሪ ሳይንቲስት እንደነበር ከስራዎቹ ጋር አጣምሮ አስቀምጦታል። ይህንንም መረጃ አስደግፎ ሎሳንጀለስ ታይምስ የተሰኘው ታዋቂ ጋዜጣ፣ በፈረንጆቹ ጥር 18/2006ዓ.ም የሳይንቲስቱን ግለ ታሪክ ይዞ ወጥቷል።
‹‹ዶክተር ቅጣው እጅጉ በብዙዎች ዘንድ የተወደደ፣ በትህትናው የተመሰገነ ፣ በስራው የተደነቀ፣ በራዕዩ ብዙ ተከታዮችን ያፈራ፣ የብዙዎች ተስፋና አርዓያ እንዲሁም ለአገሩ ትልቅ ኩራት ነው›› ሲልም የነበረውን ስብእና ሳይቀር ይገልጸዋል። ሌላው ደግሞ ይህንን እውነታ የሚያረጋግጡልን በዓለም ባንክ፣ በናሳ እና በሌሎች ድርጅቶች የታተሙ ዶክመንቶች በግልጽ ተጽፈው ይገኛሉ። ለምሳሌ ከናሳ ዶክመንቶች አንዱ በ 1980 ነበር የተዘጋጀው። በዚያ ዘመን ኢንጂነር ቅጣው ‘ጀት ፕሮፖሉዥን ላብራቶሪ’ ውስጥ ይሰራ እንደነበር ይገልጻል።
ታዲያ አንዳንዶች ይህን የገሀድ እውነታ አምኖ መቀበል ስለምን ከበዳቸው? እውነታው የጥቂቶች ሳይሆን የዓለም ሁሉ ነው። ይህ እውነት ካልሆነ ነጮቹ ያውም ስለአንድ ጥቁር ኢትዮጵያዊ ስለምን ብለው ይጽፉታል? ጉዳዩን የውሸት አድርገው በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያራግቡ አንዳንድ አካላትን እንመለከታለን። የእነዚህ አካላት ትልቁ ዓላማም የሳይንቲስቱንና የአገርን ታሪክ አጠልሽቶ ሆዳቸውን የሚሞሉበትን ጊዜያዊ እንጀራ ከማግኘት የዘለለ አይደለም። በእነርሱ የውሸት አደባባይ እኛም ተከትለን ከዞርን የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ጭምር ነው። የሳይንቲስቱን ብቻ ሳይሆን አገራችን ኢትዮጵያ በናሳ ውስጥ ስሟን ያሰፈሩበትንም ታሪክ ጥላሸት መቀባትና ማደብዘዝ ይሆናል።
ሳይንቲስቱ የኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያን ይመራ በነበረበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የሚጠቁሙ መረጃዎችም አሉ፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም ቁጭ ብለው መነጋገራቸውን የሚገልፁ ሰነዶችም አሉ፡፡ ታዲያ የእውነትም ሳይንቲስት ካልነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተታለው ነበር ማለት ነው? እንዴት አንድ ሰው ያልሆነውን ነኝ በማለት ዓለምን ሁሉ ሊያታልል ይችላል?
የዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉን ማንነት ከትንሿ የቦንጋ ምድር እስከ አሜሪካው ናሳ ድረስ ሙሉ የሕይወት ታሪካቸውን የሚያስቃኝ ‘ልጃችን’ የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ሰኔ 20 ቀን 2007 ዓ/ም በሚሊኒየም አዳራሽ ለእይታ በቅቶ ነበር። ፊልሙ የ40 ደቂቃዎች ያህል ቆይታ ያለው ሲሆን እጅጉ ቅጣው ማን ነበሩ፣ ምንስ ሰሩ፣ በአጠቃላይ ከሕይወት ዘመን በቆይታቸው እስከ ህልፈተ ሞታቸው ድረስ የነበረውን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ፊልሙን ለመስራት ለሁለት ዓመታት ያህል ልዩ ጥናት የተካሄደ ሲሆን ይህንንም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 1.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ከፊልሙ የተገኘው ገቢም ለአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት በስጦታ መልክ ተበርክቷል።
ሌላው አከራካሪው ጉዳይ የሳይንቲስቱ አሟሟት ነው። አንዳንዶች ‹‹ቅጣው እጅጉ የናሳ ሳይንቲስት በመሆናቸው ሲያገለግሏት የቆየችው አሜሪካን ብዙ ሚስጥሮች እንዳይወጡባት ስትል በስተመጨረሻ የሞትን ጽዋ አስጎነጨቻቸው›› ሲሉ ሌሎች ደግሞ ‹‹ከወደ ኢትዮጵያ በነበራቸው የፖለቲካ አቋም ምክንያት ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ በኢትዮጵያ መንግሥት ነው የተገደሉት›› በማለት ሲሞግቱ ይደመጣሉ። አሁንም ግን እውነታው የትኛውም አይደለም።
ቅጣው እጅጉ ከሰራው በላይ እንዳይሰራ፣ ከናሳው ደጅ ላይ ስሙ ከወጣው በላይ እንዳይወጣ በሕይወቱ ላይ የተጋረጠ አንድ ትልቅ ችግር ነበረ። ቅጣው የልብ ህመም ታማሚ ነበር። በዚህ ላይ የቅርጫት ኳስን አብዝቶ ይወድ ነበር። ታዲያ በአንድ ወቅት ወደ ሁስትን ቴክሳስ ዘመዶቹን ለመጠየቅ ሄዶ በፈረንጆቹ ጥር 13 ቀን 2006 እንደ ወትሮው የቅርጫት ኳስ ተጫውቶ ከዘመዶቹ ቤት ተመለሰ። መታጠቢያ ቤት በመግባትም ሰውነቱን ታጥቦ እንደተመለሰ ያቺ መጥፎ ሰዓት ደረሰች። ሰውነቱ በድካም ራደ። ልቡም እየደከመ ሄዶ በስተመጨረሻም ነብሱን ከትልቅ እውቀት ጋር የሰጠው ፈጣሪ በ58 ዓመቱ መልሶ ተቀበላት። ይህም የሶስት ልጆቹ እናትና የትዳር አጋሩ ስቴላ እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹ የሚናገሩት ብቸኛው እውነታ ነው። በአንድ ሰው ታሪክ ውስጥ ሁለት አይነት ውሸቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ፈጽሞ ግን ሁለት አይነት እውነታ አይኖርምና ብቸኛው እውነትም ቅጣው እጅጉ በናሳ ውስጥ የነበረ ኩሩ የኢትዮጵያዊ የኛ ሰው መሆኑ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም