‹‹ማይስ›› ቱሪዝም በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ገቢን የሚያንቀሳቅስና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመራጭ እየሆነ የመጣ ንኡስ የቱሪዝም ዘርፍ ነው። ይህ የቱሪዝም ዘርፍ በሆቴልና ሆስፒታሊቲ፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባ፣ ለማበረታቻና ሽልማት የሚካሄዱ የተቋማት ስብሰባዎች እንዲሁም ወቅትን ጠብቀው በሚካሄዱ የንግድ ኤግዚቢሽኖች ላይ የሚያተኩር የቱሪዝም አይነት ነው።
ያደጉ አገራት ከመስህብ ቱሪዝም በተጨማሪ ምጣኔ ሀብታቸውን በሚደግፈው በዚሁ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የተካሄደ ዓለም አቀፍ ጥናት ማይስ ቱሪዝም አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆን ችሏል። ጥናቱ ይህ አሃዝ እስከ 2025 (ከሁለት ዓመታት በኋላ) ወደ አንድ ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር እምደሚመነደግ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል። ከዚህ መረዳት የምንችለው የሆቴል፣ ኮንፍረንስ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም ልዩ ልዩ የማይስ ቱሪዝም ንኡሶችን የሚይዘው ኢንዱስትሪ ለዓለማችን የምጣኔ ሀብት ምንጭ እንደሆነ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢሮዎች ያሉባት የአፍሪካ መዲና ነች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለማይስ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ መናሃሪያ ያደርጋታል። ዘርፉ በዋናነት የጉባዔ፣ የአውደ ርእይና ባዛር፣ የንግድ ውይይትና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ዋና ማጠንጠኛው በመሆኑ አገሪቱ ምጣኔ ሀብቷን እንድታሳድግ፣ ተመራጭ የስብሰባ ቱሪዝም ከተማ እንድትሆንና ያንን ተከትሎ ዜጎች በሚፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ እድል ይሰጣል።
የማይስ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ትግበራ ካለፉት 10 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል። መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎም የማይስ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽን ቢሮም በይፋ ተመስርቷል፡፡ ይህ ቢሮ ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ ጉባዔዎች እና ሁነቶች የቱሪዝም ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ምስረታው በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተናግረው ነበር።
ፕሬዚዳንቷ በወቅቱ ኮንቬንሽን ቢሮ መመስረቱ ታሪካዊ መሆኑን በመጥቀስ በአግባቡ ከተሰራበት ለውጥ እንደሚያመጣ አስታውቀዋል። ቢሮው በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የማይስ ቱሪዝም ወይም የጉባኤ፣ የጉዞ ማበረታቻ፣ ኮንፈረንሶች፣ ሁነቶች እና አውደ ርዕዮችን መሰረት ካደረገው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማይስ ቱሪዝም ላይ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም፣ የሚፈለገውን ያህል ግን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አበረታች የሆኑ እርምጃዎች ይኑሩ እንጂ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጠቀሜታን ይዞ የሚመጣውን ይህን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ የሚደረገው ጥረት አሁንም በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቁ ነው እነዚሁ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዘቡት።
አቶ ቁምነገር ተከተል ይባላል። የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ አማካሪ ድርጅት ዳይሬክተር ነው። በስብሰባ (ኮንፈረንስ) ኢንዱስትሪው ላይ ለዓመታት ሰርቷል። እርሱ አገራት ኢንዱስትሪውን በየራሳቸው መንገድ እንደሚተረጉሙት ይናገራል። አንዳንዶቹ ከማይስ ቱሪዝም አውደ ርእይና ባዛርን በመውሰድ የትኩረት ማእከል ለመሆን፤ ሌሎች ደግሞ በስብሰባና መሰል የኢንዱስትሪው ክፍሎች ላይ በማተኮር እንደሚሰሩ ይገልፃል።
“ቱሪዝምን በመዝናኛ ዘርፍ ማለትም የመስህብ ስፍራዎችን ማስጎብኘት እና በማይስ ቱሪዝም ልንከፍለው እንችላለን” የሚለው አቶ ቁምነገር፣ አሁን አሁን አገራት ትላልቅ ማእከላትን በመክፈት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በአገራቸው እንዲደረጉ በመሳብ በቱሪዝም ዘርፉ ገቢን የማስገኛ ዘዴን መፍጠር እንደቻሉ ይገልፃል። ለመዝናኛ ጉዳይ ከሚደረገው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጋር ሲነፃፀርም “ማይስ” ወይም የስብሰባ ቱሪዝም የተሻለና ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም እያስገኘላቸው እንደሆነ ያመለክታል። ይህም በአሃዝ ሲሰላ ከመዝናኛ ቱሪዝሙ የ 300 እና 400 እጥፍ ገቢ እንደሚያስገኝ መረጋገጡን ያስረዳል።
አቶ ቁምነገር ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት በማይስ (ስብሰባ) ቱሪዝም ላይ ትኩረት አድርጋ እንድትሰራ ሲጎተጉቱ መቆየታቸውን ያስታውሳል። የኮንቬንሽን ቢሮ እንዲቋቋም በዋናነት ምክረ ሃሳብ በማቅረብ መሳተፉንም ይገልጻል። ጥረቱ ተሳክቶም ይህ ተቋም ወደ ስራ መግባት መቻሉን ተናግሮ፣ ቢሮው በዋናነት እንዲሰራ የታቀደው በገበያ ልማት ላይ እንደሆነም ያስረዳል።
“እንዲህ አይነት ተቋማት መመስረታቸው ብቻ ሳይሆን ለመስሪያ ቤቱ ተገቢውን በጀት መመደቡን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” የሚለው አቶ ቁምነገር፤ ዓለም አቀፍ የገበያ ስራ ለመስራት በቂ በጀት መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነም ይገልፃል። አሁን አሁን በትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እየተሰሩ ያሉት ጅምር የማስተዋወቅ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክቶ፣ ይህም ኢትዮጵያ የስብሰባ ቱሪዝም በስፋት የሚካሄድባት ተመራጭ ሀገር እንድትሆን እንደሚያግዝ ያስረዳል።
በተለይ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ምቹ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች መካከል ቀዳሚውና የተሻለው (መጭበርበር የሌለበት) የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት የማይስ ቱሪዝም መሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራል፡፡ ለእዚህም አንደኛው ዋንኛው ምክንያት ይህን መሰል ሁነት የሚያዘጋጁት ግዙፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሆናቸውን በመጥቀስም ክፍያዎች ያለምንም ውስብስብ መንገድ ወደ አገር ካዝና እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል። በሁለተኝነት አገር ከማይስ ቱሪዝም ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆነች ለማወቅና ትክክለኛ መለኪያ ለማግኘት ተመራጭ ኢንዱስትሪ እንደሆነም ጠቁሟል።
“በአገራችን አሁን ያለው አሰራር አያስኬድም” የሚለው አቶ ቁምነገር፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አሁን ካለበት መንገድ በተሻለ መምራት እንደሚያስፈልግ ይገልፃል። በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘውን 36ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደ ምሳሌ አንስቶ “እስካሁን ይህንን አቅም ለመጠቀም ምን የተለየና አዲስ አካሄድ አምጥተናል?” በማለት ጥያቄ ያነሳል። ከሆቴሎች ኪራይ ውጪ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ተጨማሪ ገቢ አገሪቱ እያስገኘች አልነበረም ይላል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶችን ከማይስ ቱሪዝም አንፃር ኢትዮጵያን ተጨማሪ ጥቅም በምን መልኩ ማስገኘት ይቻላል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ቁምነገር ሲመልሱ “ አዳዲስ የማይስ ቱሪዝም ጥቅሎችን በማዘጋጀት ከስብሰባው ውጪ በከተማዋ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን ከማስጎብኘት ጀምሮ በርካታ ስራዎችን መስራት ይቻላል” በማለት ምላሹን ይሰጣል።
በተለይ አዳዲስ ሁነቶችን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በመቅረፅ በዚያ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁሞ፣ በግል በመኪና ኪራይም ሆነ በልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪነት የተመዘገቡ የግል ድርጅቶች በዚህ ወቅት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ተከትሎ የሚገኝን የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ ሪፖርት የሚያደርጉበት ሥርዓት በመዘርጋትና አገር ተጠቃሚ እንድትሆን መስራት እንደሚገባም ያሳስባል።
በተጨማሪ የመሪዎች ስብሰባ በሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ እንደሚደረግ ጠቅሶ፣ ገቢ የሚያስገኙ ሁነቶችም የዚያኑ ያህል በጥንቃቄ ሊዘጋጁ እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ ይሰጣል።
“በዓለም ላይ ከፍተኛ የስብሰባ ቱሪዝም ከጤናና ከኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚመጣ ነው” የሚለው አቶ ቁምነገር፤ አገራት ከዚህ ተጠቃሚ ለመሆን ተወዳዳሪና ጨረታዎችን የማሸነፍ አቋም ሊገነቡ እንደሚገባም ይመክራል። ከዚህ በተጨማሪ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በኢትዮጵያ ሲካሄዱ ውጤቱን መለካት እንደሚያስፈልግ እና የተገኙ ስኬቶችም ሆኑ የታዩ ችግሮችን ገምግሞ ከዚያ ትምህርት መውሰድ እንደሚያሻ አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ባዛሮችን እያሰናዳች ትገኛለች፤ ከዚህ ውስጥ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር “17ኛውን የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ” በስኬት አዘጋጅቶ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ሌላው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚዎች ጉባኤን ጨምሮ የመሪዎች ጉባኤና በየደረጃው የሚካሄዱ ስብሰባዎችን እንደ ህብረቱ መቀመጫነቷ በየጊዜው ታካሂዳለች። ይሄ ደግሞ ከስብሰባ ቱሪዝም እድገትና ከዚያም ለሚገኘው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ የራሱ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
በአዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ የሚገኘው የህብረቱ ሀገሮች የመሪዎች ጉባዔም ከዲፕሎማሲያዊ ድሉ ባሻገር ኢትዮጵያ በሆስፒታሊቲው ዘርፍ ትልቅ ጥቅም የምታገኝበት እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ሚኒስቴር ልዩ ልዩ የቱሪዝም ጥቅሎችን በማዘጋጀት በኢትዮጵያ የሚገኙ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች የተቋሙ ሰራተኞች በኢትዮጵያ ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እና የከተማዋን መዳረሻዎች እንዲጎበኙ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት የህብረቱን ጉባኤ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት፤ ለመሪዎች ጉባዔ ታዳሚዎች ከአቀባበል ጀምሮ በጥሩ መስተንግዶ ቆይታቸው አስደሳች እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል። ለጉባዔው ተሳታፊዎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅና እንዲጎበኙ ለማድረግ አስጎብኚዎችና ሆቴሎች ዝግጁ ሆነዋል፡፡
የጉባዔው ተሳታፊዎች በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን የሚያውቁበትና ለመጎብኘት መረጃ የሚያገኙበት አዲስ መተግበሪያ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል፡፡ መተግበሪያው በመዲናዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን፣ የመዝናኛ ሥፍራዎችንና አጠቃላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ የሚያስተዋውቁ መረጃዎችን የያዘ እንደሆነ ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው የማይስ ቱሪዝም በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ድርሻ ያለው ግዙፍ ኢንዱስትሪ ነው። በኢትዮጵያ ይህንን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት በትኩረት መስራት ከተቻለ በርካታ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያም ትልቅ አቅም እንዳላት ይታመናል።
በአዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ተገንብተው ለበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ የሆኑትን አንድነት፣ እንጦጦ እና ወዳጅነት ፓርኮችን ጨምሮ ሌሎች ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የሚችሉ ብዙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችም አላት። በዚህ ላይ የስብሰባ ቱሪዝም (ማይስ ቱሪዝም) ፅንሰ ሃሳብን ማስፋትና የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ማሳደግ ከተቻለ ከማይስ (ስብሰባ) ኢንዱስትሪው የሚገኘውን ሀብት ልክ እንደሌሎቹ አገራት መቋደስ ይቻላል።
36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና ከጉባኤው ጎን ለጎን የሚካሄዱት በርካታ መድረኮች እየተገባደዱ ናቸው፡፡ ጉባኤው በአዲስ አበባ ቢያንስ በአመት አንዴ የሚካሄድ እንደመሆኑ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በማይስ (ስብሰባ) ቱሪዝም ላይ በሚገባ በመስራት ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ይገባል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም