የትኛውም ማኅበረሰብ በራሱ ማዕቀፍ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ የሚሆን በቂ ተፈጥሯዊ አቅም አለው። ትልቁ ችግር ይህን አቅም አውቆ በአግባቡና በኃላፊነት መንፈስ ፣ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ የሚያስችል ተነሳሽነት/ ፍላጎት የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ነው። ወደ ራስ ማየት አለመቻል፤ ከዚህም ተነስቶ ለራስ በቂ ክብር መስጠት የሚያስችል የአስተሳሰብ መሰረት አለማዋቀር ግን ይህንን አቅም በተፈለገው መጠን ሥራ ላይ እንዳይውል ያደርጋል።
ይህ ችግር በተለይም ባለንበት ዘመን፤ሁለንተናዊ ጣልቃ ገብነት በስፋት ጎልቶ በሚታይበት፤ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ ሀገራትን ፣ አህጉራትን እና ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ሳይቀር ከፍያለ ዋጋ እስከፈለ ይገኛል። ችግሩ በአግባቡ ሊገራ ካልቻለ በቀጣይም ያለመረጋጋት እና ሁከት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው።
ችግሩ በተለይ በአፍሪካውያን ላይ ጎልቶ የሚታይ ነው። አፍሪካውያኑ አንድም የችግሮቻቸውን እውነተኛ ምንጭ በአግባቡ ካለማስተዋል፤ ከዛም በላይ ለችግሮቻቸው መፍትሄ አድርገው የሚወስዷቸው የውጪ የመፍትሄ ሃሳቦች “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆነውባቸው ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ያሳለፏቸው ስድስት አስርት ዓመታት በአብዛኛው ያለመረጋጋትና የሁከት አመታት እንዲሆኑ አድርጎባቸዋል።
በርግጥ አፍሪካውያን በዘመናት መካከል በትውልዶች ቅብብሎሽ ያካበቷቸው፤ እጅግ ብዙ የችግር /የግጭት ማስወገጃ ባህላዊ እሴቶች ባለቤቶች ናቸው። ዘመናትን ተሻግረው መምጣት የቻሉትም በእነዚሁ አቅሞች ነው። በነጻነት ትግሉ ወቅትም እነዚህ እሴቶች የነበራቸው አስተዋጽኦም የማይተካ እንደነበር ይታወሳል።
ከነጻነት ዋዜማ ጀምሮ በአፍሪካውያን ምሁራን የተጀመረው የፓን – አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴም ቢሆን የነዚህን እሴቶች የማይተካ ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ላይ የተመሰረተ፤የአህጉሪቱን ሕዝቦች ቀጣይ እጣ ፈንታ ብሩህ ለማድረግ ሊኖራቸው የሚችለውን የላቀ ጠቀሜታ ከግምት ያስገባ ነው። አስተሳሰቡ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በብዙ ፈተናዎች ለማለፍ የተገደደውም ከዚሁ የተነሳ እንደሆነ ይታመናል።
ዛሬ ላይ አፍሪካውያን ስለነገዎቹ ትውልዶቻቸው እጣ ፈንታ ሲያስቡም፤ ከሁሉም በላይ ጥላ ሆኖ የሚያሳስባቸው፤ በውስጥ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶችና ጣልቃ ገብነቶቹ የሚፈጥሯቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች እና ሁኔታዎቹን ለመቀልበስ የሚከፈለው ውድ ዋጋ ነው።
ይህ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ አፍሪካውያኑ በራሳቸው እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም ያሳጣቸው የውጪ ጣልቃ ገብነት በራሱ የችግሮቻቸውም ምንጭ መሆኑ ለችግሮቻቸው ግዝፈት ዋነኛ አቅም ከመሆን አልፎ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል።
አፍሪካውያኑ አንድም የችግሮቻቸው ዋነኛ ባለቤት አለመሆናቸው፤ ከዚያም በላይ የተፈጠሩ ችግሮችንም በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ ዕድሉን መነፈጋቻው፤ ያልዘሩትን የመከራ ዘር እንዲያጭዱ ባልተገባ መልኩ ተፈርዶባቸው ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።
ከዚህ ከትውልድ ትውልድ እየተሻገረ የመጣን ችግር ለዘለቄታ ለመፍታት ከሁሉም በላይ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሄ ከማፈላለግ በፊት የችግሩን እውነተኛ ምንጭ አጥርተው ሊያውቁት ያስፈልጋል። ከእነርሱ በላይ ስለችግሮቻቸው ሊያስብ የሚችል ኃይል ሊኖር እንደማይችል ከቀደመው አሳዛኝ ታሪክ ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል።
የአህጉሪቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ነጻነታቸውን ለመቀናጀት ያጋጠማቸው ተግዳሮትና ተግዳሮቱን አሸንፎ ለመሻገር የከፈሉት መስዋእትነት፤ የፖለቲካ ነጻነቱን ሙሉ ለማድረግ ላለፉት ስድስት አስርቶች ያጋጠሟቸው ፈተናዎች እና ፈተናዎቹ እያስከፈሏቸው ያለው ዋጋ ከእነርሱ በላይ ስለነሱ ሊያስብላቸው የሚችል ላለመኖሩ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
አፍሪካውያን ከቀደመው ታሪካቸው ሆነ ከነጻነት ዋዜማ ጀምሮ ይዘዋቸው ከተነሷቸው በራስ የመተማመን መንፈስ አንጻር ለራሳቸው ችግሮች መፍትሄ ሆነው የመቆም ትልቅ አቅም ባለቤቶች ናቸው። ይህ ደግሞ በነጻነት ትግሉ ወቅት የተፈጠሩ ፈተናዎችን በአሸናፊነት ተሻግሮ ለማለፍ ወሳኝ አቅም ሆኗቸው ታይቷል።
በዚህ ወቅትም “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል የአህጉሪቱ ሕዝቦች በአዲስ መንፈስና መነቃቃት ቃላቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት ነው። በርግጥም እውነታው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ችግሩን ማንም ስለ ምንም ይፍጠረው አፍሪካውያን የትኞቹንም ችግሮች አሸንፈው መሻገር የሚያስችሉ ታላላቅ ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤቶች ናቸው!
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም