“የማታ እንጀራ ስጠኝ” ይላል የአገሬ ሰው ሲተርት፡፡ አዎ ጉርምስና ብሎም ጉልምስና ተሰርቶ የማይጠገብበት። ተሩጦ የሚቀደምበት ፤እራብም ጥምም ችግርም ያን ያህል የማይጎዱበት ብቻ በአጠቃላይ ሁሉም ነገር እንደ አመጣጡ የሚመለስበትና የሚታለፍበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ጉርምስና አልፎ ጉልምስና ከዛም እርጅና ሲመጣ ደግሞ በወጣትነት ሮጠው ያፈሩትን መብላት አረፍ ማለት እንጂ ለስራ መነሳሳቱ እምብዛም አዋጭ አይሆንም፡ ፡ በስተርጅና እንደ ልብ ከማያራምድ የእድሜ ሁኔታ ጋር የጤና መቃወስ ከገጠመ ደግሞ ሁሉም ነገር ከባድ ይሆናል፡፡
በትናንትናው በተለይም በጉርምስናና ጉልምስና እድሜያቸው ላይ አገራቸውን በብዙ ያገለገሉ ጀግኖች ዛሬ ላይ ቀን ሲጥላቸው፤ወኔ ሲከዳቸው የወገን ያለህ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ዕድለኞች ከወደቁበት ሲነሱና ባለውለታነታቸው ሲታወስ ተመልክተናል፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ የት እንዳሉ እንኳን በውል አይታወቅምⵆ ጊዜ እራሱ አድሎ የሚፈጽም እስከሚመሰል ድረስ ለአገር ለወገን ብዙ የዋሉ ሰዎች ሳይታዩ ሳይከበሩ መከበሩ ቀርቶ ለኑሯቸው እንኳን አስፈላጊ ነገር ሳይሟላላቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እድሜያቸውን እንዲጨርሱ በለፉባት አገርና ህዝብ ዘንድ ዋጋ ቢስ ሆነው ተስፋ ሲቆርጡ መመልከት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡
የዛሬ የዚህ ዓምድ ባለታሪካችን በትናንትናው በተለይም በጉርምስናና ጉልምስና እድሜያቸው ላይ አገራቸውን በብዙ ያገለገሉ ጀግና ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በ1951 ዓ.ም ጥቅምት 1 ቀን በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ገንጂ ወረዳ ሲሆን እድገታቸውም እዛው አካባቢያቸው ላይ ነው፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአቅራቢያቸው ባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የተማሩት፡፡
“……አባቴ ባይማርም ለትምህርት ልዩ ፍቅር ስለነበረው ደጋግሞ ተማር ብታጣ እንኳን እንደ ቆሎ ተማሪ ለምነህ ተማር ኋላ እዚህ ገጠር ነው የምትቀረው ብሎኝ ነበር የሞተው ⵆ እኔም የመማር ፍላጎቱ ስለነበረኝ ለትምህርቴ ልዩ ትኩረት እሰጥ ነበር “ ይላሉ፡፡ ምንም እንኳን መብራት እንዲሁም መንገድ በሌለባት ጊምቢ ወረዳ ቢወለዱም ትምህርት የሁሉ ነገር ብርሃን ነው ብለው በሳምንት አርብ አርብ ስንቅ ከቤተሰቦቻቸው ለማምጣት 61 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ተጉዘው ገንጂ ወረዳ እየሄዱ ተምረው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪነትና የኢትዮጵያ ባንክ ገዢነት የደረሱ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው አቶ ዱባለ ጃሌ፡፡
አቶ ዱባለ ጃሌ ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ የተሞላበት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ 12ተኛ ክፍል ማትሪክ ተፈትነው 3ነጥብ 8 በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድልን አገኙ፡፡ የደሃው ልጅ አቶ ዱባለ ቀድሞም ቢሆን ራሳቸውን ያውቁ ነበርና በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደሚገቡም እርግጠኛ ስለነበሩ ፈተናውን ወስደው በነበረቻቸው ትርፍ ጊዜ በቆሎ ዘርተው አሳድገው በመሸጥ አስፈላጊ ግብዓቶቻቸውን አሟልተው እናታቸውን ሳያስቸግሩ ነው የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል አዲስ አበባ የገቡት፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ ያደረጉት አቶ ዱባለ ዛሬም ድረስ በአገሪቱ ትልልቅ የፋይናንስ አመራርነት ላይ የሚገኙት የቀድሞ ሚኒስትሮች አቶ ግርማ ብሩ ። ሶፊያን አህመድና ሌሎችም ጓደኞቻቸው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ዱባለ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ 1974 ዓ.ም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ላይ ሰርተዋል፡፡
የስራ አለምን “ሀ” ብለው የተቀላቀሉት ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሲሆን ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ በ1975 ዓ.ም ወደ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በመሄድ ለስምንት ዓመት ያህልም ሰርተዋል፡፡ በኦልማ ቱምሳ 1984 እስከ 19 87ዓ.ም ከዛም ከፍ ባለ ደረጃ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ተብለው ከ 1988 እስከ 19 89 ዓ.ም ለአንድ አመት ያህል አገልግለዋል፡፡
በ1989 ዓ.ም ደግሞ ከፍ ላለ የስራ ኃላፊነት የታጩት አቶ ዱባለ የብሔራዊ ባንክ ገዢ በመሆን እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በሌላ በኩልም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አማካሪ ሆነው 1993 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ የሰሩ ሲሆን፤ በኋላም የኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚና ፋይናንስ አማካሪ ሆነው 2003 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ስለመስራታቸው ይናገራሉ፡፡በተለይም የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው በአገለገሉባቸው ጊዜያት አለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ጨምሮ በርካታ ለኢትዮጵያ ብድር የሰጡ የዓለም አገሮች ዘንድ በመቅረብ በብድር ቅነሳና ስረዛ ዙሪያ ድርድሮችን አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹንም አሳክተው ተመልሰዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ መጣላታቸውን ተከትሎ የነበረውን የገንዘብ ለውጥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በቢሯቸው ጠርተው የቅያሪውን ሚስጥራዊ ሂደት አማክረዋቸዋል፡፡ አቶ ዱባለው የአገራቸውን ምስጢር በልባቸው ይዘው በተባለው መንገድ ስራዎች እንዲሰሩ አድርገው በሚፈለገው ልክና መልክ አሳትመው ይፋ መሆን በሚገባው ጊዜ ይፋ በማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር ያደረሱም ጀግና የአገር ባለውለታ ናቸው፡፡
ከዚህ ሁሉ የስራና የአገልግሎት ዘመን በኋላ ያለው የአቶ ዱባለ ኑሮ በእውነት አንገት ያስደፋል ፤ልብ ያደማል በሀዘን ጭብጥ ኩርምት ያደርጋል፡፡ “….አትመመኝ ማለት አይቻልም ግን ደግሞ መታከሚያ ገንዘብ አትንፈገኝ ይባላል” ፡፡ አቶ ዱባለ መጀመሪያ ከስራ ውለው ቤታቸው እረፍት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ ነበር በጭንቅላት ደም መፍሰስ (ስትሮክ) የተመቱት ፡፡ እሱን እንደምን ማገገም ቢችሉም ኩላሊታቸው በመድከሙ ምክንያት ዛሬ ላይ በሳምንት ሶስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት ዲያሊሲስ የሚፈልጉ ህመምተኛ ሆነዋል፡፡
“….ዛሬ እንዲህ ሆንኩ እንጂ ድሮማ ለረሀብም ለጥጋብም የማልበገር ፤ሰርቼ የማይደክመኝ፤ የሰው ሀቅ የማልፈልግ ፤አገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ሁሉ በአቅሜ በታማኝነት ያገለገልኩ፤ አዲስ አበባ ተቀምጬ ገጠር ያሉ ወገኖቼን የምደግፍ፤ ለልጆቼ አባት ለሚስቴም አባወራ ነበርኩ፡፡ ምን ያደርጋል ዛሬ አልሆነም “ ይላሉ አንገታቸውን ስብር አድርገው፡፡ በሽታ ክፉ ነው ፤በሰው እጅ መውደቅ ደግሞ ሞት ፡፡ እኛ ጠንካራና ቆፍጣና በርካታ አገራዊ ኃላፊነቶች ላይ ግንባር ቀደም የነበሩት ሰው ዛሬ ተንቀሳቃሽ ወንበራቸው (ዌልቸራቸው) ላይ ቁጭ ብለው የልጆቻቸውን በተለይም የካሊድን ድጋፍ መፈለግ የእለት ተዕለት የኑሮ ሂደታቸው ከሆነ 13 ዓመታት እንደዋዛ ተቆጥረዋል፡፡ ዲያሌሲስ እያደረጉ ጭምር መንግስትን የማማከር ስራቸውን አላቋረጡም፡፡
ዛሬ አቶ ዱባለ በሳምንት ሶስት ጊዜ እንዲያደርጉ ለሚጠበቅባቸው ዲያሊሲስ እጅ ሰጥተዋል፡፡ ለህክምናው እጅ ቢሰጡም ከፍሎ መታከሚያው ደግሞ የሞት ያህል ገዝፏል፤ እጃቸው አጥሯል፡፡አስራ ሶስት ዓመት ሙሉ በተለያዩ ህመሞች ሲሰቃዩ የቆዩት አቶ ዱባለ ዛሬም ድረስ አብሯቸው ለቀጠሉት ህመሞች የሚሆን መታከሚያ ገንዘብ የላቸውም፡፡ ዛሬ ቤተሰቦቻቸው የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንዲደረግላቸው ቢያስቡም (ቢመኙም) ለእሱ የሚሆን ገንዘብ ግን የላቸውም፡፡ እኚህን የአገር ባለውለታ ዞር ብሎ ያያቸውም የለም ቀፍድዶ ከያዛቸው ህመም ጋር ተደምሮ ችግር አቅም አሳጥቷቸዋል ፡፡
አቶ ዱባለ በወጣትነታቸው ሀገራቸውንና ቤተሰባቸውን መደገፍ ነበር የቀን ተሌት ህልማቸው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው በ 2ሺ 5 መቶ ብር ደመወዝ ይስሩ እንጂ ከደመወዛቸው ውጪ አንዲትም ነገር ለመጠቀም አስበው አያውቁም ፡፡ በወቅቱ ደመወዛቸውን ቆጥበው የሰሩትን ቤትም በኩላሊት ህመማቸው ምክንያት ለመታከሚያ ይሆን ዘንድ ሸጠውታል፡፡ ከዛም በመንግስት አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ቤተሰባቸውን ይዘው ለመኖር ተገደውም ነበር ፡፡ አንዳንዴ ስራ ዋጋ ይከፍላልና ዛሬ ላይ አብረዋቸው በሰሩ ስለ ጉብዝናቸው ስለአገልግሎታቸው እንዲሁም ታማኝነታቸው የሚያውቁ የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው አቶ አባዱላ ገመዳ ባደረጉላቸው ከፍ ያለ ጥረት የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ማረፊያ ይሆናቸው ዘንድ አንድ ቤት ሰጥቷቸዋል፡፡
ይህንን ላደረጉላቸው አካላትም ላቅ ያለ ምስጋናን ያቀርባሉ፤ ግን ደግሞ አሁን የአቶ ዱባለ ችግር የህክምና ወጪያቸው ነው፡፡በጡረታ የሚያገኟት ገንዘብ እሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ህክምና መድኃኒት ለመሸፈን ቀርቶ ቀለብ ለመሸመት አትበቃም፡፡ እራሱን ችሎ እሳቸውን ለመደገፍ አቅም ያለውም ልጅ የላቸውም፤ ብቻ ሁኔታቸው ልብ ይነካል። ተገቢውን ህክምና ቢያገኙ በቀላሉ የሚያገግሙ መሆናቸው ሲታይ ደግሞ ቁጭት ፈጥራል፡፡ 35 ዓመታት አብረዋቸው ከኖሩት ባለቤታቸው አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አቶ ዱባለ ባለቤቴ በዚህ ሁኔታዬ ውስጥ ከጎኔ ቆማለች፡፡ ልብሴን አጥባ ምግቤን ሰርታ አቅርባ እንዳይሰማኝ አበረታታኝ “አመመኝ “ እንኳን ስል “ አንተ ብቻ ነህ እንዴ የምትታመመው በል በርታ “ ብላ ዛሬ ላይ እንድደርስ አቅም ሆናኛለች ይላሉ ፡፡
የእኔ አባት የሚሉት ልጃቸው ካሊድ ዱባለ ከጎናቸው አይለይም፤ ይህንን ቃለ ምልልስ እያደረግን እንኳን ደጋግመው ይጠሩታል፡፡ እሱም ለእሳቸው ሲል ስራና ኑሮውን ትቶ አባቱ ስር ነው ያለው፤ “….አባቴ አገሩን በታማኝነት ያገለገለ ነው፤ ዛሬ ግን ጤናው ተዛብቶ የሰው እጅ ላይ ወድቋል “ ይላል ካሊድ ፡፡ ካሊድ አባቱ የዲያሊሲስ ህክምናቸውን በገንዘብ ችግር ምክንያት እንዳያስተጓጉሉ ብዙ ጥረት ያደርጋል፤ ቀድሞ የሰሩባቸው መስሪያ ቤቶች እየሄደ እርዳታ ይጠይቃል፤ የሚያውቁትን እሳቸውን የሚያውቋቸውን ሰዎች ሁሉ አስቸግሯል፤ ግን ደግሞ ዘላቂ መፍትሔን ማግኘት አልቻለም፡፡
“….አባቴ ታሞ አልጋ ከያዘ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በእነዚህ ዓመታት ቤታችንን ሸጠናል፤የብዙ ሰዎችን እጅ አይተናል፤ የሚያውቁንም የማያውቁንም ብዙ አድርገውልናል፤ አሁንም አባቴ የሚያስፈልገው የኩላሊት ንቅለ ተከላው በመሆኑ እሱን የሚያደርግልን ኢትዮጵያዊ እንፈልጋለን” በማለት እያሳለፉ ያሉትን ከባድ ጊዜ ይናገራል፡፡ ‹‹በዚህ ዘመን ሙስና ገነገነ አስቸገረ ትልቁም ትንሹም ሙሰኛ ሆነ አገር ተበዘበዘች እየተባለ ኮሚቴ እስከማዋቀር የደረሰ ዘመቻ ላይ ነን፡፡ እንደዚህ ደግሞ አገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉ ለእኔ ሳይሉ የኖሩ በዚህ መልኩ ችግር ሲገጥማቸው እንደ አገርም ሆነ ህዝብ ውለታቸውን በአለሁ ባይነት ማሰብ ይገባል›› ይላል ካሊድ ፡፡
አዎ! ለመልካም ስራ መሽቶም ፤ረፍዶም አያውቅምና አቶ ዱባለ የሚያስፈልጋቸውን የህክምና እርዳታ ያገኙ ዘንድ ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ አለብን፡፡ ይህ ትውልድም የሀገር ባለውለታዎችን የመደገፍ ሀገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ አለበትና የሀገር ባለውለታ የሆኑትን የአቶ ዱባለን ህይወት መታደግ የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015