ከቅኝ ግዛት ነፃ ያልወጡ አፍሪካውያንን ከቅኝ ተገዢነት ለማላቀቅ እንዲሁም የአፍሪካን የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ውህደት ለማሳካት የተመሠረተውን የቀድሞውን ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት››ን (Organization of African Unity – OAU) እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም ከተካው የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (African Union – AU) ዓላማዎች መካከል አንዱ በምጣኔ ሀብት ያደገችና የበለጸገች አፍሪካን እውን ማድረግ ነው።
በእርግጥ የምጣኔ ሀብት ዘርፍን ጨምሮ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዘመን የነበረችው አፍሪካ፣ በአፍሪካ ኅብረት ዘመን ካለችው አፍሪካ በብዙ መልኩ የተለየችና የተሻለች እንደሆነ አይካድም። አፍሪካ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚዋ እያደገች፣ ትናንት ከነበራት የምጣኔ ሀብት ትስስር የተሻለ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች። የአፍሪካ ኅብረትም በአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲያድግ የወሰዳቸው ተቋማዊ እርምጃዎች አዎንታዊ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አፍሪካ ካላት እምቅ አቅም እና ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር አህጉሪቱ የምትገኝበት የምጣኔ ሀብት ደረጃ ዝቅተኛ ነው።ይህም የአፍሪካ ኅብረት አህጉሪቱን በምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ያስቀመጠው ዓላማው በሚጠበቅበት ልክ እየተጓዘ ላለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ቢጠቀስ ስህተት አይሆንም።
ዛሬም በከፋ ድህነት የሚማቅቀው የአህጉሪቱ ሕዝብ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ሥራ አጥ ከሆነው የአህጉሪቱ ሕዝብ መካከል ወጣቱ 60 በመቶውን ይሸፍናል።ኢ- ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ከአህጉሪቱ ራስ ምታቶች መካከል አንዱ ነው።ግዙፍ ሀብትና አቅም ያላት አፍሪካ፣ ከዓለም ምጣኔ ሀብት ያላት ድርሻ ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑ አስደንጋጭ ነው፡፡
የአህጉሪቱ አገራት መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦችን ጭምር የሚያቀርቡት ከውጭ አገራት ገዝተው እንጂ ራሳቸው አምርተው አይደለም። አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ፣ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ይረዳቸው ዘንድ ከውጭ አገራት የሚያስገቧቸውን ሸቀጦች በራሳቸው ምርቶች ለመተካት ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ሞክረው ነበር። የአገራቱ መንግሥታትም በዚህ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ምክረ ሃሳቦች ቀርበውላቸው ነበር። ይህ አሠራር መጠነኛ ለውጦች እንዲመዘገቡ ቢያስችልም የሚጠበቅበትን ያህል መጓዝ ግን አልቻለም።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ሲበሰር በዕለቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በሙሉ ታላቅና ታሪካዊ ቀን ነው … በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚና በሶሻል እድገት ካልተደገፈ ከፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል …›› ብለው ነበር።
በምጣኔ ሀብት እድገት ያልተደገፈ የፖለቲካ ነፃነት፣ በወረቀት ላይ የሰፈረና በወሬ የሚነገር ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም ምጣኔ ሀብታቸውን በፍጥነት ማሳደግ ባለመቻላቸው ከእጅ አዙር ቅኝ ተገዢነት ነፃ ሊወጡ አልቻሉም።
የአፍሪካውያን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች (በተለይ እንግሊዝና ፈረንሳይ) እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ስልት በአፍሪካውያን ጉዳይ ባለቤትና አድራጊ የመሆናቸው ነገር ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።ከዚህ በተጨማሪም የኅብረቱ አባል አገራትም አፍሪካዊ አቋምና እሳቤ ከመያዝ ይልቅ በየፊናቸው የምሥራቁና የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለሞች ደጋፊ ሆነው ይታያሉ።
ከኅብረቱ አባል አገራት መካከል አብዛኞቹ ለኅብረቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በተገቢው ሁኔታ የሚከፍሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ኅብረቱ ለመደበኛ ወጪዎቹ ጭምር ባለፀጋዎቹን የምዕራብና የምሥራቅ አገራትን ደጅ ለመጥናት ይገደዳል።ይህ ለእጅ አዙር ቅኝ ተገዢነት የመጋለጥም ሆነ ወደተፃራሪ ጎራዎች አማትሮ የመለጠፍ አባዜ የመጣው በአፍሪካውያን ደካማ የኢኮኖሚ አቅም ምክንያት ነው።
‹‹የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ጣልቃ ገብነትን መከላከል ዓላማዬ ነው›› የሚለው የአፍሪካ ኅብረት ግን ይህን ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ወኔ አጥሮታል።‹‹የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ጣልቃ ገብነትን መከላከል›› የተባለው የኅብረቱ ዓላማም በወረቀት ላይ የሰፈረ ምኞት ሆኖ ሲቀር በተደጋጋሚ ታይቷል።
በተጨማሪም ኅብረቱ አፍሪካውያን ከውጫዊ የአስተሳሰብ ጥገኝነት ተላቅቀው አፍሪካዊ እሳቤ መያዝ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የሠራው ሥራም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።እንግዲህ ይህ ሁሉ ተጋላጭነትና ጫና የሚመነጨው በኢኮኖሚ ራስን ካለመቻል ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ዓላማዬ ነው ብሎ የያዘውን የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት የማሳደግና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የመፍጠር ግቡን ለማሳካት እስካሁን ድረስ ያደረጋቸውን ጥረቶች ማጠናከር፣ ማሻሻልና በአዳዲስ አሠራሮች መቃኘት ይጠበቅበታል።ለዚህ ሁነኛው መፍትሄ ደግሞ የአህጉሪቱን እምቅ አቅም ለመጠቀም ለሚያስችለው የእርስ በእርስ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ልዩ ትኩረት መስጠት ነው።አህጉራዊው የምጣኔ ሀብት ትስስር አፍሪካውያን ሀብታቸውን ተጠቅመው በጋራ ለማደግ የሚያስችል ዕድል ይሰጣቸዋል፤ በዓለም ኢኮኖሚ የላቀ ድርሻ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።
የአህጉሩን የምጣኔ ሀብት ትስስር እውን ለማድረግ ከሚያግዙ ግብዓቶች መካከል አንዱ ‹‹የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት›› (African Continental Free Trade Area Agreement – AfCFTA) ነው።ስምምነቱ በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን ለማቀላጠፍና የግብይት መሰናክሎችን ለማስቀረት እንደሚያስችል ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ አብዛኞቹን የንግድ ታሪፎች በማስቀረት የአፍሪካውያንን የርስ በርስ ንግድ እስከ 2034 ዓ.ም. (እ.አ.አ) 60 በመቶ በማሳደግ የሦስት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር ገበያ የመፍጠር እቅድ አለው።
ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ከሆነ፣ በዓለም ባንክ ስሌት መሠረት፣ 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ከከፋ ድሕነት፤ 70 ሚሊዮን የአህጉሪቱን ዜጎች ደግሞ ከመካከለኛ ድሕነት ያወጣል። ስምምነቱ በአህጉሪቱ የሚታየውን የተዛባና ያልተመጣጠነ የንግድ ሥርዓትን በማረም ሂደት ላይ የጎላ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፤ ለሚሊዮኖች የአህጉሪቱ ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል።
አፍሪካ ለምታስበው አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ውህደትም በር ይከፍታል ተብሎ ይታሰባል። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ እድገት ባሻገር፣ በተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመቀነስ የሚደረገን ጥረት አጋዥ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።
በምጣኔ ሀብት እድገት ያልተደገፈ የፖለቲካ ነፃነት፣ ከወሬ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም የምጣኔ ሀብት ነፃነትን ማሳካት ባለመቻላቸው አሁንም ከእጅ አዙር ቅኝ ተገዢነትና ስውር ቅኝ ግዛት ለፈጠራቸው ችግሮች ተዳርገዋል። ስለሆነም የአህገሪቱን የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠንከር ሰላምን ማስፈን፣ ከውጭ ተፅዕኖ መላቀቅ፣ ከድህነት መውጣት በአጠቃላይ የአፍሪካ ኅብረት ያስቀመጠውን ሰላሟና ፀጥታዋ የተጠበቀ፣ በምጣኔ ሀብት ያደገችና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደት ያላት አፍሪካን እውን የማድረግ ግብን ማሳካት ይገባል።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015