በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው ጉልህ ሚና ያለው ቡና፣ በአሁኑ ወቅት በምርት መጠኑ፣ በጥራቱና በኤክስፖርት ድርሻው እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2014 በጀት አመት ኢትዮጵያ በቡና የወጪ ንግድ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገብ መቻሏም በዚሁ ምክንያት ነው። በዚህ የስኬት ጉዞ ውስጥ ቡናን ከሚያለማው አርሶ አደር ጀምሮ ሰብሳቢዎች፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበርም ጭምር ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ መያዙን የቀጠለው ቡና እያስመዘገበ ካለው ውጤት በተጨማሪ ቀጣይ በሚኖረው አበርክቶ ጉልህ ድርሻ ካላቸው አልሚዎችና ላኪዎች መካከል “ሞዬ ተጋና ጡላ ቡና አልሚና ላኪ ድርጅት” አንዱ ነው። ድርጅቱ በራሱ የእርሻ መሬት ላይ ያለማውን ቡና እንዲሁም የሌሎች አልሚዎችን ቡና ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ቡናን በጥሬው ከመላክ ባለፈ እሴት በመጨመር የተቆላ ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ በመሆን ለዘርፉ እድገት እየተጋ ይገኛል።
የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ አሀዱ ውብሸት ወርቃለማሁ ይባላሉ። የአንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ የክብር አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። የበኩር ልጅ በመሆናቸውም አሀዱ የሚለውን መጠሪያ አግኝተዋል። በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት አቶ አሀዱ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ወደ አገረ አሜሪካ አቀኑ። የአሜሪካ ጉዟቸውም በዋናነት ለትምህርት ነው።
በዚያው በአገረ አሜሪካ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ አሀዱ፤ በዚያው በአሜሪካ አገር በተለያዩ ባንኮች ሰርተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት አጋጣሚን ያገኙት የዛሬ 14 ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተመሰረተበት ወቅት ነው። በወቅቱ ለአገሪቱ አዲስ የሆነውን ምርት ገበያን ለማቋቋም ሲታሰብ በዘርፉ የተሰማራና የውጭ አገር ልምድ ያለው ሰው ማስፈለጉ የግድ ነበር። እናም በውጭ አገር የሠራና ሲስተሙን የተረዳ ሰው ሆነው የታጩት አቶ አሀዱ፤ ምርት ገበያን ካቋቋሙት ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
አቶ አሀዱ የምርት ገበያ ስርዓትን የመዘርጋቱ ስራ ከተመቻቸ በኋላ በአጭር ጊዜ ወደ አሜሪካ የመመለስ ዕቅድ ነበራቸው። ይሁንና በወቅቱ ቡናን የመተዋወቅ ሰፊ ዕድል በማግኘታቸው በቀላሉ ኢትዮጵያን ለቀው መሄድ አልቻሉም። በምርት ገበያ ቆይታቸውም ቡናን በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ውጭ እሴት ጨምሮ የመላክ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የመታዘብ ዕድል አጋጥሟቸዋል። ከዚህም ባለፈ ቡና ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ በሚገባ መረዳት የቻሉት አቶ አሀዱ፤ በዘርፉ ቢቀላቀሉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በማመን የአሜሪካ ጉዟቸውን ሰርዘው ቡናን ለማልማት ወደ ግብርናው ፊታቸውን አዞሩ።
‹‹ሁሉም የሚያምረው በአገር ነው›› በማለት የአሜሪካ ኑሯቸውን የተውት አቶ አሀዱ፤ በምርት ገበያ ውስጥ የነበራቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ለተተኪው አስረክበው ሙሉ ጊዜያቸውን ቡናን በማልማት ሥራ ውስጥ ማሳለፍ ውስጥ ገብተዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቡናን በጥሬው ከመሸጥ ባለፈ እሴት የመጨመር እሳቤ አልነበረም። ይሁን እንጂ መነሻው ቡናን ከማልማት ጀምሮ ነውና እሳቸውም በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ቡናን አልምተው በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ ሲልኩ ቆይተዋል።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ቡናን በጥሬው ብቻ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ ተመራጭና ውጤታማ መሆኑን በማመን ቡናን ቆልቶና አሽጎ ለውጭ ገበያ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ፈጥረው ወደ ሥራው ገብተዋል። ይህም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር አገርን የማስተዋወቅ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
በአሁኑ ወቅትም ሶስት ድርጅቶችን አቋቁመው እየመሩ ይገኛሉ። የመጀመሪያ ሥራቸው ቡናን ማልማት እንደመሆኑ በግል ከሚያለሙት በተጨማሪ 6000 ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ ቡና ያለማሉ። ሁለተኛው ቡናን በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለውን የቡና ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽን ተክለው መጋዘን ገንብተው ጥሬ ቡናን ለውጭ ገበያ ያዘጋጃሉ። ሶስተኛው ሞዬ ቡና በሚባለው ድርጅታቸው ስም እሴት ጨምረው ቡናን ቆልተውና አሽገው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ።
አቶ አሀዱ እንዳሉት፤ የቡና ልማቱን የሚያካሂዱትም በደቡብ ምዕራብ ክልል በከፋ፣ ሸካ ዞንና ከፋ ዞን ጌሻ በሚባሉ አካባቢዎች ነው። ከፋ ጊንቦ የሚባል አካባቢን ጨምሮ በአካባቢው በጥቅሉ አንድ ሺ 200 ሄክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ ቡናን እያለሙ ይገኛሉ። ለእርሻ ሥራው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ስፋት ባለው የእርሻ ቦታ ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ ይገኛሉ።
ለዘርፉ ዕድገት ዋናውና ወሳኙ ሥራ ቡናን በጥራትና በስፋት ማልማት መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም በግላቸው ከሚያለሙት ሰፊ የቡና ልማት በተጨማሪም በአካባቢው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ ይሰራሉ። አርሶ አደሮቹ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲያድግና ጥራት ያለው ምርት ማምረት እንዲችሉ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ ምርታማ እንዲሆኑ ያግዛሉ።
አርሶ አደሩም ድጋፉን ተጠቅሞ የሚያመርተው ምርት የተሻለ ጥራት ያለው በመሆኑ በጥሩ ዋጋ መሸጥ የሚያስችለው ይሆናል። ይህ ብቻም አይደለም፤ አርሶ አደሩ የገበያ ትስስር የተፈጠረለት በመሆኑ ምርቱን የሚሸጠው ለዚሁ ድጋፍና ክትትል ለሚያደርግለት ድርጅት ነው። በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ነው የሚሉት አቶ አሀዱ፤ ያለምንም ውጣ ውረድ በቀጥታ በተሻለ ዋጋ ምርቱን የሚገዙት መሆኑንም አስረድተዋል።
ከልማቱ ቀጥሎ ድርጅቱ በሚፈልገው የጥራት ደረጃ ያለማውንና ከአርሶ አደሩ የሚሰበስበውን ቡና አጥቦና አድርቆ ለውጭ ገበያ ማዘጋጀት ደግሞ ቀጣይ ሥራ ነው። ለዚህም በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሶስት ቡና ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽኖችን ተክለዋል። በዚሁ አካባቢም አርሶ አደሩን በማሳተፍ ድርጅቱ የሚያለማውን ጨምሮ ከአካባቢው አርሶ አደር ቡናን ይገዛሉ። ይህም ቡናን በማጠብና በማድረቅ እሴት ሳይጨመርበት የምርት ሂደቱ ተጠናቅቆ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ነው።
ሶስተኛው እህት ኩባንያ ሞዬ ቡና መሆኑን አቶ አሀዱ ጠቅሰው፣ ኩባንያው እሴት ጨምሮ የተቆላ ቡና ወደ ውጭ ገበያ እንደሚልክ ይናገራሉ። ሞዬ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ገበያው እየገባ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አገር እንድታድግ ከግብርናው ዘርፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ መሸጋገር የግድ ነው። ለዚህም ለገጣፎ አካባቢ 20 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ቡና መቁያና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁመዋል። በፋብሪካውም በግል ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚለሙ ቡናዎችንም ጭምር ቆልተውና ፈጭተው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ።
‹‹ተቆልቶ የተፈጨ ቡና የሚሸጠው ታሪኩ ነው›› የሚሉት አቶ አሀዱ፣ ገዢዎች የቡናውን መገኛ፣ ከየት እንደመጣና አጠቃላይ ታሪኩን ማወቅ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። ለዚህም ከመቁላትና ከመፍጨት በተጨማሪ በራሳቸው ማሸጊያ ቡናውን አሽገውና አስፈላጊውን ታሪክ በማሸጊያው አትመው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። ይህም በተለይም ለውጭ ገዢዎች ተዓማኒነትን የሚያተርፍ ነው ይላሉ።
የገበያ መዳረሻቸውን አስመልክቶም እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ትላልቅ ለተባሉ ኩባንያዎች ያለቀለት ቡና ማከፋፈል ጀምረዋል። ተደራሽነታቸው እየሰፋ በመሄዱ ከዚህ ቀደም በአውሮፕላን ይልኩ የነበረውን ቡና አሁን ላይ 80 በመቶ ያህሉ ያለቀለት ቡና በመርከብ እየተጓጓዘ ነው። ይህም የገበያ መዳረሻቸው እየሰፋ መሄዱን ያመለክታል። 66 በመቶ ያለቀለት ሞዬ ቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ ቀሪው 34 በመቶው ደግሞ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል።
ይህ ቡና በአገር ውስጥ ገበያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀምሮ በተለያዩ ኤምባሲዎችና ሱፐርማርኬቶች ይከፋፈላል። ከዚህ በተጨማሪም የካፌን ልምድ በማስፋት ቡናን አፍልቶ የማቅረብ ጅማሮን በተለይም በትላልቅ ሆቴሎች ሞዬ ቡናን እያስተዋወቀ ይገኛል። ከዚህ ባለፈም በአንዳንድ አካባቢዎች ለማገዶነት የሚውለው የቡና ገለባ በላብራቶሪ ሙከራ በማድረግ በባህላዊ መንገድ ለመጠጥነት እንዲውል የማስተዋወቅ ሥራም እየሠራ ይገኛል።
በዓመት አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኪሎ ያለቀለት ቡና ቆልቶ ወደ ውጭ ገበያ የሚልከው ሞዬ ቡና፣ ትልቁ ገበያው አውሮፓ ቢሆንም በተለያዩ የዓለም አገራት ተደራሽ ነው። ከእነዚህ ሀገሮች መካከልም ኔዘርላንድ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዱባይ፣ አሜሪካ ይገኙበታል።
ሞዬ ቡና በቅርቡም ከአንድ ትልቅ ኩባንያ ጋር ተፈራርሞ ወደ ሲውዲን ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አቶ አሀዱ ተናግረዋል። በምርት አቅርቦት መጠናቸውም ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላኩን ጠቅሰው፣ በዚህም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ እንደነበሩም አቶ አሀዱ አስታውሰዋል።
ቡናን ከእርሻው ጀምሮ በማልማት በጥሬውና እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩት አቶ አሀዱ፤ ለ366 ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቡናን በመልቀም፣ በማጠብና በማድረቅ 2000 ለሚደርሱ ሰራተኞች በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በቋሚነትና በጊዜያዊነት ከፈጠሩት የሥራ ዕድል በተጨማሪ ስድስት ሺ /6000/ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን በመደገፍና ምርታማ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ሰርተዋል። ለአብነትም ከፋ ጊንቦ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብተው አስረክበዋል። እዛው ከፋ ተጋና ጡላ በተባሉ አካባቢዎች መንገድና ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋም ገንብተው ለማህበረሰቡ ግልጋሎት እንዲሰጥ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነም አቶ አሀዱ ተናግረዋል።
በቀጣይም የቡና ምርትን በማሳደግ ጥራቱንም ከፍ በማድረግ በስፋት የመሥራት ዕቅድ ያላቸው አቶ አሀዱ፤ በተለይም ሞዬ ቡና የሚቆላ ድርጅት እንደመሆኑ የሌሎች አገራት ቡናን ጨምሮ እሴት በመጨመር ቆልቶና ፈጭቶ በኢትዮጵያ ስም ለውጭ ገበያ ተደራሽ በማድረግ ዘርፉን የማስፋት ዕቅድ አላቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና በዝቅተኛ መጠን እየተመረተ እንደሆነና በአንጻሩ ደግሞ የአገር ውስጥን ጨምሮ በዓለም አገራት የቡና ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑን ያነሱት አቶ አሀዱ፤ ምርትና ምርታማነት ላይ ሰፊ ሥራ መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ወደ ውጭ ገበያ እየተላከ ያለው የኢትዮጵያ ቡና መጠን እጅግ ዝቅተኛ ነው። በተመሳሳይ ቅርብ ጊዜ ቡናን ማምረት የጀመሩ እንደ ቬትናም ያሉ አገራት ደግሞ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ስድስትና ሰባት እጥፍ እያመረቱ ነው። ስለዚህ ጥናትን መሰረት በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ መሰራት አለበት።
ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ቻይና የቡና ፍላጎቷ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ቡና አብቃይ አገሮች ትልቅ የገበያ ዕድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን አመልክተዋል። ስለዚህ ምርታማነት ላይ መስራት የግድ ነው የሚሉት አቶ አሀዱ፤ እየመጣ ያለውን ሰፊ ገበያ ተደራሽ በማድረግ ከዘርፉ ተጠቃሚ የመሆን ዕድልን ማስፋት ይገባልም ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015