በኢትዮጵያ ጥሬ ስጋ መብላት ከባህል ጋር የተያያዘ ነው። በተለያየ ጊዜ ያጋጠሙን የውጭም ሆነ የውስጥ ጦርነት ጥሬ ስጋ የመብላት ትሩፋት ያመጡልንም ያመጡብንም ይመስላል። አለማየሁ ነሪ ..ኢትዮጵያ ሲሳይ.. በሚል ርዕስ በ1998 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት 29 ዓመት በፊት የሮማው ንጉሥ አውግስቶስ ቄሣር ኢትዮጵያን በሰሜን በኩል ወረረ። በጦርነቱ ወቅትም ዘማች ሠራዊት ምግቡን ለማብሰል እሳት በሚያነድበት ስፍራ የሚወጣውን ጭስ በመመልከት የጠላት ሠራዊት አስከፊ አደጋ እያደረሰ በወገን ላይ ጉዳት ማመዘኑ፣ የወቅቱ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች ደረሱበት። በጭሱ ሳቢያ የሚደርሰው ሽንፈትም እጅግ ስለበዛ ሥጋ ለማብሰያ እሳት እንዳይቀጣጠል፣ ጭስ እንዲቀር፣ የኢትዮጵያ ጦርም ጥሬ ሥጋ እንዲበላ እንደታዘዘ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥሬ ሥጋ መብላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ባህል ሆኖ መለመዱን.. የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ ሲሉ ጽፈዋል።
በኢትዮጵያ የዐውደ ዓመትን ዐውድ የሚያሰማምረው እርድ ነው። ማለትም የበግ፣ የፍየል፣ የበሬ፤ የዶሮ እርድ። የሙስሊሙም ሆነ የክርስቲያኑ ዐበይት በዓላት ድምቀቱ የከብቶች እርድ ነው። የሙስሊሞች ዒድ ሲከበር እርድ የግድ ነው። በተለይ ዒድ አልፈጥር (ረመዳን) እና ዒድ አል አድሃ (አረፋ) የበዐላቱ ውበቱና ድምቀቱ እርድ ነው። ዐውድ ዓመትን የሚያደምቁት የሚዘጋጁት የበዓል ምግቦች ናቸው። እነዚህም ቁርጥ ስጋ፣ ክትፎ ፣ድፎ በከተሞች ደግሞ ኬኩ፣ ለስላሳና አልኮል መጠጡ የማይቀሩ ናቸው። ጀበናው በከሰል ተጥዶ፣ ሲኒው ከነረከቦቱ ቀርቦ፣ የጭሳጭሱ እና እጣኑ መጫጫስ፣የፈንዲሻው እና የቄጠማው ጉዝጓዝ የበዓሉን ድባብ በተጨማሪ የሚያሞቁና የሚያደምቁ ናቸው።
በከተሞች ለገና፤ለፋሲካ ለአረፋ እና ለመሳሰሉት በአላት ሰዎች ተሰባስበው ገንዘብ አዋጥተው ወይፈን አርደው በቅርጫ ይከፋፈላሉ። በእነዚህ በዓላት በከተሞች ያለው በግሉ በግም ሆነ ፍየል አርዶ ያከብራል። የሌለው ደግሞ ከብት ገዝቶ አርዶ በቅርጫ መልክ ይከፋፈላል። ዐቅም የሌለው ደግሞ ልኳንዳ አንድ ኪሎም ለመግዛት ይሰለፋል።
አሁን አሁን የሁዳዴን ጾም መያዣ በመሳሰሉት ቀናት ተሰባስቦ ጥሬ ስጋ መቁረጥና ጾሙን በደስታ መቀበል የተለመደ እየሆነ መጥቷል።በተለይም እንደአሁኑ የሁዳዴ ጾም ሰኞ የሚገባ ሲሆን ቅዳሜና እሁዱን ጥሬ ስጋ በስፋት ይበላል።የስጋቤቶች ገበያም ይደራል።ወዳጅ ዘመድ መጪውን የጾም ወቅት ሰላም የሚገኝበት የምህረት ወቅት እንዲሆን ምኞቱን ይገላለጻል።
በተለይ እንደ ገና እና ፋሲካ ያሉ ዓውደ ዓመቶች የሚመጡት ረዥም የጾም ወቅትን ተከትለው በመሆኑ ዐቅም በፈቀደ እርድ ይከናወናል። የከብት እርድ ተፈጽሞ ቅርጫውን የሚጋሩ ሰዎች ስጋቸውን ተከፋፍለው ቤት ከማስገባታቸው በፊት ጥሬ ጉበቱን ቆራርጠው በአዋዜ አድርጎ መብላት የተለመደ ነው። የከብት ጥሬ ስጋው ሲበላ ዳቢት( የበሬ የትከሻ ስጋ የጎድን ዘርፍ ) ከሻኛ መቁረጥ፣ ቁርጥ፣ ከክትፎ ማመራረጥ በመጠጥ ማወራረድ የተለመዱ የዐውደ ዓመት ትሩፋቶች ናቸው።ጥሬ ስጋ መቁረጥ፣ ቁርጥ ማመራረጥ ሀገርኛ ነባር ልምድ ነው።
መስቀል ከአዲስ ዓመት ቀጥሎ የሚመጣ ስለሆነ ሰዎች አዲስ ዓመትንም ደርበው በድምቀት ያከብሩታል። ለዚህ ደግሞ የከብት እርድ የግድ ተብሎ የሚከወንባቸው ቦታዎች አሉ። በደቡብ በጉራጌ፣ በሀዲያ፣ በጋሞ በዓሉን የሚያደምቁት ከብት አርደው በቅርጫ ተከፋፍለው፤ ቁርጥ ስጋውን፣ ጎረድ ጎረዱን፣ ክትፎውን እየበሉ ነው።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር 1868 Narrative of a Journey to Shoa,” ወደ ሸዋ ጉዞ ትርክት በሚል ካፒቴን ባርከር በጻፈው መጻፍ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ጥሬ ስጋ የሚወድ ሕዝብ ያለባት ሀገር ናት ሲል በኢትዮጵያ ተዘዋውሮ በወቅቱ የጎበኘውን ይጠቅሳል።
አሚስቱ ኩማ እና ሌሎች ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሎጅ Consumer Preference of Raw Beef (“Kurt”) በሚል ርዕስ በ2017 በወላይታ ሶዶ ከተማ ዙሪያ ባወጡት ጥናት ልኳንዳ ቤቶች እና ደንበኞቻቸውን ለናሙና መርጠው ነበር።
ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል 80 በመቶዎቹ ጥሬ ስጋን ለቁርጥ ፣ 4ነጥብ 8 በመቶው ለወጥ ፣12 ነጥብ 9 በመቶ ለጥብስ እና 3ነጥብ 3 በመቶው ቅቅል ለመሥራት እና ሌሎቹ ለጣምራ አገልግሎት እንደሚጠቀሙበት ጥናታቸው ያስረዳል። በዚህም ጥሬ ስጋ ወይም ቁርጥ በአካባቢው ነዋሪዎች እጅግ ተወዳጅ ምግብ እንደሆነ በጥናታዊ ጽሁፋቸው ጠቅሰዋል።በኢትዮጵያ የከብት እርባታ ለሥጋ ምርት ዓመታዊ አስተዋፅኦ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ ሲገመት ይህም 72 በመቶ ጠቅላላ የስጋ ምርት ነው። ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ጥሬ ስጋ ተወዳጅ ምግብ ቢሆንም በኢትዮጵያ መደበኛ ዓመታዊ የስጋ የነፍስ ወከፍ አጠቃቀም 8ኪሎ ግራም መሆኑን ጥናታዊ ጽሑፉ ያስረዳል።
በዓለም ሥጋን የመመገብ ልምድ ከሀብት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው። በብዙዎቹ ምዕራብ አውሮፓ ሀገራት አንድ ሰው ከ80 እስከ 90 ኪሎ ሥጋ በዓመት እንደሚመገብ ሰነዶች ያሳያሉ። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን በጣም ሥጋ የምንመገብ ይመስለናል። እርግጥ ስጋ በባህላችን ተወዳጅ ምግብ ነው።አብዛኛው የሀገራችን ገጠሬው በከተሞች እንደምናየው ስጋ በላተኛ አይደለም። ገጠሬው ስጋ የሚበላው በዓላት በሚሆኑ ጊዜ ፣ ሠርግ የመሳሰሉ ነገሮች ሲያጋጥሙት ነው።
ገበሬው በከብቶቹ ከማረስ ውጭ እምብዛም አርዶ ስጋውን ለመብላት ወኔውም ፍላጎቱም የለውም። የተወሰነ በዓላት ሲኖሩ በግና ፍየል አርዶ ስጋውን ለምግብ ፍጆታ ይጠቀማል። ቢሆንም የተወሰኑት የበሬ ስጋ የፍየል የበግና የዶሮ ስጋ ይመገባሉ። አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከብት አርደው ስጋ ከመብላት ከብቱን ሸጠው ገንዘብ ማግኘትን ይመርጣሉ። ስጋ የሚበሉት በዐላትን ተከትሎ ነው። እናም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ስጋ ተመጋቢ ያለባት ሀገር እንደሆነች ጥናቶች ያሳያሉ።
የከተሜነት መስፋፋትን ተከትሎ በከተሞች በአንድ ገበታ በጋራ የመመገብ ልምድ እየቀነሰ ቢመጣም፤ ቁርጥ ሥጋን ግን ለብቻ መመገብ እምብዛም አይታሰብም። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየጨመረ የመጣው የቁርጥ ሥጋ ፍቅርም፣ በአንድ ገበታ ከቦ የመመገብ ልምድን አጠናክሮ መቀጠሉን በሥራው ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ።
በምግብ ቤቶች ጥሬ ስጋ መብላት ያማረው ከወዳጆቹ ጋር ብር በማዋጣት ጥሬ ስጋው በጋራ ሲበላ በየልኳንዳ ቤቶች የምናየው እውነታ ነው። ሰዎች ጥሬ ስጋቸውን እየበሉ ‹ጥሬ በሉት የበሰለ› ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች እና ሌሎችም ነገሮች እያነሱ ጭውውት ያደረጋሉ። እናም ጥሬ ሥጋ የሚመገቡ ሰዎች ማኅበራዊ ትስስራቸውን እግረ መንገዳቸውን ያጠናክራሉ። ይህም ሰብሰብ ብለው ልኳንዳ ቤት በመሄድ ጥሬ ስጋ በመብላት ብቻ ሳይሆን፣ በዓውድ ዓመት እንደ ገቢ አቅማቸው በጋራ በመሆን ቅርጫ በመግባት አንድ በሬን በቡድን በመካፈል አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው። ከታች ያለው አንቀፅም ይህንኑ ሃሳብ ያስረግጣል።
ከሁለት ዓመት በፊት ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ በአንድ ስጋ ቤት በኢትዮጵያ ባላንጣ የሚባሉ ፖለቲከኞች ስጋ ቤት ሲገናኙ ቂማቸውን ሁሉ እርግፍ አድረገው ትተው ጥላቻቸውን ወደ ፍቅር እንደሚቀይሩ ዘጋቢው የታዘበውን ጽፏል። ቁርጥ ቤት ሲገናኙ አሳዳጅ እና ተሳዳጅ የነበሩ ፖለቲከኞች የእግዜር ሰላምታ ተለዋውጠው እና ተቀላልደው ይመገቡበታል። ሁኔታውን የታዘቡ አንድ የስጋ ቤት ደንበኛም ‹‹ምናለ ሥጋ ላይ እንደምንቻቻል ፖለቲካው ላይ እንዲህ ቢንቻቻል ›› ማለታቸውን የስጋ ቤቱ አስተዳዳሪን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
የቁም ከብት ልማት ዘርፍ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ሁነኛ ሚና ይጫወታል። እርሻውን የሚያርሰው በሬ ሰብሉን እንዲዘራ እየረዳ ገበሬው ምርታማነት የጎላ ሚና ያበረክታል። ሸማቹ እየሸመተ የሚበላው በሬውና ገበሬው ያረሱትን ነው። በሬ በጉልበቱ ሰብል እንዲመረት እየረዳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ገበሬዎች ቀልበው፣ አደልበው ወደ ከተሞች ይሸጡታል። በከተማ ቄራዎች እየታረደ ስጋው ለምግብነት ቆዳው ለልብስና ለጫማ አገልግሎት ይውላል። ከላይ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ላይ ሁነኛ ሚና አለው ያልነውም ይህንኑ ነው።
በምግብ ቤቶች እና በልኳንዳ ቤቶች ጥሬ ስጋ በቁርጥ፣ በጎረድ ጎረድ መብላት የተለመደ ነው። ክትፎ፣ ናሽፍ እና ዱለት በጥሬና በለብለብ ሲበላም በብዛት በምግብ ቤቶች እና በልኳንዳ ቤቶች የምናየው ነው። እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች ምግብ ቤቶች ዱለት አዛችሁ ምግቡ ሲመጣላችሁ ዱለት የሚባለውን ፈጽሞ አታገኙትም። ክትፎ መሆን የተሳነው ቀይ ስጋ ፤በጥሬ፣ በለብለብና በጥብስ መልክ ይቀርብላችኋል። ዱለትን ደግሞ የምታገኙት ለብቻው ምላስ ሰንበር በሚል አዛችሁ ተጠብሶ ሲመጣላችሁ ነው።
በዓላት ብቻ ሳይሆን ለትዳር ሽማግሌ ሲላክ፣ ሠርግ ሲሠረግ፣ ተዝካር ሲወጣ፣ ዝክር ሲዘከር፤ እርድ ማዘጋጀትና ጥሬ ስጋውንም አክሎ የመብላት ልምድና ባህል በሠፊው የሚታይ ሀገርኛ ባህላችን ነው። ጥሬ ስጋ በብዛት የመብላት ልምዱም ሆነ ባህሉ ያለው በከብት ማለት በበሬ እና ባረጠች ላም እርድ ላይ ነው። የምግብ ማቀዝቀዣ በሌለባቸው ቦታዎች ስጋን ለተወሰነ ቀን ማቆየት የሚችሉት ስጋውን ዘልዝሎ በማድረቅ ነው። ይህም ቋንጣ የምንለው ነው።በዚህም ሰዎች ቋንጣውን ከሰቀሉበት አውርደው ለቅምሻ ያህል መብላት የተለመደ ነው። በተዘዋዋሪ ቋንጣ ሲበሉ ጥሬ ስጋ እንደመብላት ነው።
በከተሞች ደግሞ አሁን አሁን ጥሬ ስጋ የመብላት ባህሉና ልምዱ ወደ ፍየልም እየተሸጋገረ ይመስላል። ለዚህም በልኳንዳ ቤቶች በብዛት የሚታዩት ‹‹የፍየል ቁርጥ አለ›› የሚሉ ማስታወቂያዎችም ምስክር ናቸው። በአንድ ወቅት በአዋሳ ከተማ ጥሬ ዐሳ ተበልቶ ስጋውን ከሐይቁ ብዙም ሳይርቁ በብዛት የሚበሉ ሰዎች ዐይቼ ተደምሜ ነበር። ስለዚህ ጥሬ ስጋ የመብላት ባህላችን ከበሬ፣ ፍየል፣ ዐሳ እያለ አድጎም በሉት ወርዶ ወደ ዶሮም ሊሸጋገር እንደሚችል ብገምት የሚቃወመኝ አይኖርም።
በመድኃኒት ከደለበ በሬ ይልቅ በተፈጥሮ ሳር እየጋጠ እና እያረሰ ያደገ በሬ ለስጋው ጤንነት ተመራጭ መሆኑን አንዳንድ የምግብ ሳይንስ ምሁራን ያስረዳሉ። ጥሬ ስጋ የሚደምቀው ከማባያው ጋር ሲቀርብ ነው። አዋዜ፣ ስናፍጭ፣ ዳጣ እና ሚጥሚጣ ጥሬ ሥጋን መልከ ብዙ ለማድረግ ያጅቡታል። አንዳንዶች ሚጥሚጣ ከሀሞት ጋር ቀላቅለው ለጥሬ ስጋው እንደማባያ ይጠቀሙበታል። የአልኮል መጠጥ የሚጠቀሙም ሰዎች ጥሬ ስጋ ሲበሉ ማወራረጃ መውሰዳቸው አይቀርም። ጠላ፣ ጠጅ፣ አረቄ፣ ወይን አልያም ቢራም አብረው የሚቀርቡ መጠጦች ናቸው።
ከጥሬ ሥጋ መብላት ጋር ተያይዞ የኮሶ ትል፣ ሳልሞኔላ እና አንትራክስ የተሰኙ በሽታዎች ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል። ቀድሞ ሰዎች ጥሬ ስጋ ሲበሉ በብዛት ኮሶ ይጣባቸው ነበር። አሁን ኮሶ ስሙ የጠፋ ይመስላል።በአንዳንድ ቦታ ከብቶች ስለሚከተቡ እና ብዙ ገበሬዎች ጉድጓድ አዘጋጅተው ለመጸዳጃ መጠቀማቸውም ኮሶ ድራሹ እንዲጠፋ ጠቀሜታ ያለው ይመስላል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015