መነሻ ሃሳብ፤
የአፍሪካ መሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ በሚካሄድበት ሣምንት ውስጥ ከአህጉሪቱ የተሰባሰቡ በርካታ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ በአገራቸው አንቱታን ያተረፉ ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የሚመክሩበት ታላቅ ሊባል የሚችል ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል።የዚህ ታላቅ ጉባዔ የየዓመቱ መሪ ቃል «አፍሪካ ተነሽ – Africa Arise” የሚል ሲሆን፤ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚያስተባብረውም «ቤዛ ኢንተርናሽናል ቤተክርስቲያን» የተባለ አገራዊ ቤተ እምነት ነው፡፡
በጉባኤው ላይ ከአፍሪካም ውጪ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን የተጎናጸፉ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች ለአንድ ሣምንት ያህል በአፍሪካ ዘርፈ ብዙ አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ፣ ያስተምራሉ፣ አንድነትና ኅብረት ላይ ትኩረት በመስጠትም የአህጉሪቱ ሕዝቦች እውቀታቸውን፣ ሀብታቸውንና ጊዜያቸውን አስተባብረው ለአፍሪካ ትንሣኤ እንዲተጉ ይመክራሉ፣ ያነቃቃሉ፣ የመቀራረብን ትሩፋትም አጉልተው ያመላክታሉ።
የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔያቸውን በሚጀምሩበት የመጀመሪያው ዕለት ማለዳ ላይም በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ጉባዔተኞቹ በአንድነት ተሰባስበውና እጅ ለእጅ ተያይዘው አፍሪካን ይባርካሉ፣ ለሕዝቦቿ ሰላምና ልማት ይጸልያሉ፣ ለመሪዎቿም ጥበብና ማስተዋል ፈጣሪን ይማጸናሉ።ይህ የማለዳ የጥሞናና የጸሎት ጉባዔ በየዓመቱ የሚከፈተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ቡራኬ ነው።በዚህ ዓመት በዛሬው ዕለትም የተከናወነው መርሃ ግብር ይሄው ነው፡፡
በአለፉት ዓመታትም ሆነ በዚህ ዓመት በተካሄደው ጉባዔ ላይ ተጋባዥ ተናጋሪዎች፣ አስተማሪዎችና የሴሚናሩ አስተባባሪዎችና መሪዎቹ ሲናገሩ የነበረውና ባለፉት ቀናት ውስጥም ተደጋግሞ ሲተላለፍ የሰነበተው መልዕክት «ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የወደፊት ዕድል ተቀዳሚና ወሳኝ ነች።ኢትዮጵያ ተዳከመች ማለት አፍሪካም ሸብረክ አለች ማለት ነው።የኢትዮጵያ ራእይ በራሷ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንም ጭምር ትርፋቱና በረከቱ ስለሚተርፍ ይህንን ታላቅ አደራዋን በታላቅ ጥንቃቄ ልትወጣ ይገባል፤ ሕዝቧም እውነታውን ተረድቶ ከራስ ባለፈ ዝግጅት አፍሪካን አማክሎ መፍትሔ አመንጪ ሊሆን ይገባል» የሚል ነበር።
እነዚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አገራችንንና ሕዝባችንን ባስቀመጡበት ልክ እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን እያዘጋጀን ነው ወይ? ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ልንሞገትበት የሚገባ መሠረታዊና ተገዳዳሪ ጥያቄ ይመስለኛል።እንዴታውን በተወሰኑ ምሳሌዎች ለማብራራት ልሞክር፡፡
ያልታየንን እናስተውል፤
ለዚህ ጽሑፍ የተሰጠው ዋና ርዕስ ጥያቄ ማጫሩ የሚቀር አይመስለኝም።«ኢትዮጵያ ቀድሞንስ አፍሪካዊት አገር አይደለችም ወይ!? አፍሪካዊነቷስ የሚረጋገጠው ዛሬ ነው? ርዕሱ ግልጽነት የጎደለው አይመስልም? ወዘተ.» የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚዥጎደጎዱ አልጠፋኝም።እውነት ነው፤ ርዕሱ የተመረጠበት ዋናው ዓላማ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ለውይይት ክፍት እንዲሆኑ በማሰብ መሆኑን ሳልጠቁም አላልፍም፡፡
የአፍሪካ አገራት በሙሉ በአንድ አህጉር ውስጥ የተጠቃለሉ የቤተሰብ አባላት ይምሰሉ እንጂ የሥነ ልቦናና የአስተሳሰብ ልዩነት የላቸውም ማለት ግን አይደለም። ይህን መሰሉ የአመለካከት መዥጎርጎር ሊፈጠር የቻለው አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ተክለው ያለፉት ዘር ፍሬ ከማፍራቱ ጋር ብቻ ተያይዞ መታሰብ የለበትም።ከእኛ ከኢትዮጵያውያን አንጻርስ መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች አይኖሩም ይሆን? ምክንያቴን በውሱን ምሳሌዎች ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
አፍሪካውያን ለእኛ ያላቸውን ተስፋና በጎ አመለካከት የሚቃረን ከሚመስል መሠረታዊ ሃሳብ ልንደርደር።ይህ ጸሐፊ በተለያዩ የአፍሪካ አገራትና «በሥልጡን» ተብዬ የዓለም አገራት በተገኘባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ተደጋግሞ ከተጠየቃቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤ «እኛ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እጅግ በጎ ግምትና ፍቅር አለን።በአህጉሪቱ ውስጥም የተለየ ሞገስ ያገኛችሁ ሕዝቦች እንደሆናችሁ የየአገራችን ታሪክ ሳይቀር ይመሰክርላችኋል።እናንተ ኢትዮጵያውያን ግን በርግጡ የአፍሪካና የአፍሪካውያን ጉዳይ ግድ ይላችኋል?» እነዚህን የመሰሉ ጥያቄዎች የተጠየቀው ይህ አምደኛ ብቻ ሳይሆን ብዙዎችም ሳይጠየቁ እንዳልቀሩ ይገመታል፡፡
አፍሪካውያኑ ወንድም እህቶቻችን ለሚጠይቁን ለዚህን መሰሉ ጥያቄ «ስለ ምን ተሞገትን!?» ብለን ሊከፋን ወይንም ሊያበሳጨን የሚገባ አይመስለኝም።ለምን ቢሉ በሌላው ዐይን ላይ ያለን ጉድፍ እያየን ከመሳለቅ ይልቅ በራሳችን ዐይን ላይ የተጋደመውን ምሰሶ ቀድሞ ማስወገዱ ብልህነት ስለሆነ ነው፡፡
ደፈር ብለን ራሳችንን መሄሱ ለጋራ ፈውሳችን ስለሚበጅ አፍሪካዊነትን በተመለከተ አንዳንድ ታሪካዊ እውነታዎችን ስንዘክር ወደ አልተፈለገ ጫፍ እንዳይወስደን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉ ጠቀሜታው የላቀ ነው። ሳናስተውል የፈጸምናቸውን መተላለፎቻችንንም ላለመድገም በአመለካከታችንና በድርጊታችን ላይ ተሃድሶ ማድረግ ይገባ ይመስለኛል፡፡
ብዙም ትኩረት ከማይሰጠው ነገር ግን አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን ደጋግመው ከሚያነሱት ቅሬታ ልጀምር።በዕለት ተዕለቱ ንግግራችን ውስጥ የአህጉራችንን የቤተሰብ አባላት የምንጠቅሳቸው እንደ ቅርብ ወንድምና እህት እየቆጥርን ሳይሆን «እነርሱ አፍሪካውያን» እያልን በማራቅ ነው።
መልካቸው የቀላውንና ቆዳቸው የነጣውን ደግሞ በጅምላ የምንፈርጃቸውና ስንፈርጃቸው የኖርነው «ፈረንጅ» እያልን ነው።«አሜሪካውያን፣ አውሮፓውያን፣ እስያውያን ወዘተ.» እያልን የእኛን አህጉር ወንድም እህቶች በምንጠራበት በአህጉራቸው ስም ስለመበየናችን እርገግጠኛ አይደለሁም።
በብዙ ንግግራችን ውስጥም «እናንተ አፍሪካውያን» የሚል ገለጻ መጠቀም የተለመደ ነው።ይሄ ጉዳይ በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባል።እነርሱን «እነዚያ አፍሪካውያን» ስንል እኛን ራሳችንን ሌላ አህጉር ውስጥ እንዳለን ማስመሰሉን ልብ ያልን አይመስልም።«እናንተስ አፍሪካውያን አይደላችሁም?» ተብለን የተጠየቅን እንደማንጠፋ ጸሐፊው ተስፋ ያደርጋል።
ሁለተኛ ማሳያ ላክል፡- በኢጣሊያኖች የተከፈተብንንና ድል በድል የተጎናጸፍንባቸውን የዓድዋን ጦርነት ወይንም የፋሽስትን ወረራ በጽሑፍም ሆነ በቃል ንግግር ስንዘክር የኖርነውና ዛሬም እያደረግነው ያለው «የአፍሪካ አገራት በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ወድቀው በነበሩባቸው ዘመናት ‹እኛ ኢትዮጵያን ግን›…» እንላለን ።
ይህን መሰሉን የቋንቋ አጠቃቀም ብዙ እህት ወንድሞቻችን እንደማይወዱት ለዚህ ጸሐፊ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው ገልጸውለታል። ነገሩ እውነት ቢሆንም እንኳን በንግግራችንና በገለጻችን ጥንቃቄ ሊጓደል አይገባም። በቅኝ ግዛት መኖራቸው ባይካድም «ባርነትን» አጉልቶ በማሳየት ሥነ ልቦናቸውን መጉዳቱን ልብ ብለን ያጤንን አይመስልም።«ካቆሰለኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ» እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡
ሦስተኛ ምሳሌ ልጥቀስ፡- እኛ ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ሰጥተን በመደበኛ የትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ልጆቻችን እንዲማሩ የምንፈልገውና ቅድሚያ ቢሰጣቸው የማንጠላቸው ቋንቋዎች በአብዛኛው የየትኞቹ አገራት ቋንቋዎች እንደሆኑ «ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ» ካልሆነ በስተቀር ለሁላችንም እውነቱ አይጠፋንም።
ከ200 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪ ያለውንና በባህል፣ በደምና በታሪክ የተቆራኘንበትን፣ ከፍ ሲልም የአፍሪካዊነትን ዋጋ የሚያልቀውን የአህጉራችንን የስዋህሊ ቋንቋ ቢማሩልን እንመርጣለን ወይንስ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጫና እንደምንገደድባቸው እንደ የቻይናው የማንደሪን ቋንቋ?
በቤተሰባዊነት ብቻ ሳይሆን ከጂኦ ፖለቲካው አንጻርም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የሚታመነውና በታሪካዊ መስተጋብራችን ለዘመናት አብረን የኖርነውን፣ የሰሜን አፍሪካ አብዛኞቹ አገራት የሚናገሩትንና ሰፋ ብሎም የሩቅ፣ የቅርብና የመካከለኞቹ የአረብ አገራት የሚናገሩትን የአረብኛ ቋንቋ ወይንስ ወደ አውሮፓ በርቀት ተሻግረን በአግባቡ ሳይገቡን ሌሎች ትምህርቶችን ሳይቀር በምንማርባቸው የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ቋንቋዎች? ዜጎች የትኛውንም ተጨማሪ ቋንቋ መማር ቢችሉ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ጸሐፊው የሚያረጋግጠው በቋንቋ ትምህርት የሰለጠነበትን የእውቀት ዘርፍ ዋቢ በማድረግ ጭምር ነው።
«ብቸኛ የአፍሪካዊ ፊደል ባለቤት» እያልን በኩራት ልባችንን የምናሞቅበትን የእኛንስ ቋንቋ ሌሎች የአህጉራችን ቤተሰቦች እንዲማሩት ምን ያህል ጥረት ተድርጓል።በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የምርምርና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመጠናትን ያህል ዕድል ያህል ቋንቋችንን እንዲማሩ አመቻችተንላቸዋል? በዚህ ጉዳይ የሚከፉ አፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን «ኩሩነታችንን» እያጣቀሱ እንደ አንድ ቤተሰብ በመቆራኘታችን ጉዳይ ላይ «እናንት ኢትዮጵያውያን የአፍሪካዊነት ስሜት በእርግጡ አላችሁ?» ብለው ቢሞግቱን ተገቢነት አይኖረውምን?
በአገራችን የልብስ መደብሮች ውስጥ ሞልተው የተትረፈረፉት የአልባሳት ዓይነቶችስ የአፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን ናቸው ወይንስ የአውሮፓዎቹ ሙሉ የወንዶች ሱፍ፣ ከረቫት፣ ለሴቶችም ሚኒስከርት? እንደ እውነቱ ከሆነ የጋናው ኬንቴና ዳሺክ (የአሼንቴና ኤዌ ጎሳዎች ወንድ ከሴት ሳይለዩ የሚለብሷቸውት ድንቅና ውብ አልባሳት)፣ የናይጄሪያው ኢሮ አቲ ቡባ፣ የጾታ ልዩነት ሳይደረግ ሴኔጋሎች የሚለብሱት ቦቡ፣ የኬንያዎቹ የማሳይ ጎሳዎች የሚለብሱት ዝነኛ ሹካ፣ የዙሉ ቆነጃጅት የሚዋቡበት ኢስዱዋባ፣ የካሜሮኖቹ ቶጉ ወይንም አቶጉ የተሰኙት በጠቢባን የእጅ ጥልፎች የተሠሩ የወግ ልብሶች ምርጫችን እንዲሆኑ ፈቅደን እናውቃለን? ምን ያህሉስ በአገራችን ተለምደዋል? ያውም የአፍሪካ መዲና እያልን በምናንቆለጳጵሳት በአዲስ አበባ የአልባሳት መደብር ውስጥ ምን ያህሎቹን ማግኘት ይቻላል?
የማዕድ ገበታችንም ቢሆን ለአፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን ባህላዊ ምግቦች ባዕድ መሆኑን ልንክድ አንችልም።አቆነጃጅተን በምንደረድራቸው የግብዣ ቢፌዎች ዝርዝር ውስጥም ሆነ በአዘቦት ቀን ምግባችን ውስጥ የጣሊያን ፓስታ፣ ማኮሮኒና ፓስታ ፉርኖ የሚከበሩትን ያህል አፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን የሚጠበቡበትን ምግብ ምርጫችን እናደርጋለን?
ስምና ዓይነታቸውንስ በአግባቡ እናውቀዋለን? የሞዛምቢክ ፒሪ ፒሪ፣ የደቡብ አፍሪካ በኒቾ፣ የአንጎላው ሙምባ ዴ. ጋሊና ወይንም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ማዕድ ላይ የሚከበሩት እነ ታጂኔ፣ ቦቦቲ፣ ባራኢ፣ ኡጋሌ፣ በኒ ቾው ወዘተ. የመሳሰሉትን አፍሪካዊ ምግቦች አንኳንስ መቅመስ በዐይናችንም አይተን ያለማወቃችን ለእኛ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አገር ሕዝቦች ምን ትርጉም እንደሚያሰጥ እንዴት ይጠፋናል?
ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን ከቋንቋ አጠቃቀም እስከ ተዘረዘሩት ዋና ዋና ማሳያዎች ራሳችንን አጥረን ካኖርነበት «ጌቶ» ነፃ አውጥተን እንደ አፍሪካ የፖለቲካ መናኸሪያና የአህጉሪቱ ሥልጣነ መንበር እንደተዘረጋባት አገር ራሳችንን ልንፈትሽ ይገባል።ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ አገራት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስም የተሰየሙ በርካታ ጎዳናዎች መኖራቸውን ይህ ጸሐፊ አረጋግጧል።
አልፎም ተርፎ በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ስም የተሰየመ ስቴዲዬም በሞሮኮ ካዛብላንካ መኖሩን የሚያውቁ በስፖርቱ ዘርፍ ያሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው።በጋናው የቀድሞ መሪ በንክሩሁማ የመታሰቢያ ሙዚዬም ዋናውን በር አልፎ የሚገባ ጎብኚ በመጀመሪያ ፊት ለፊቱ በግርማ ሞገስ ቆሞ የሚያስተውለው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን አስደናቂ ግዙፍ ሥዕል ነው።እኛስ? «ሆድ ይፍጀው!»
ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ሁለተኛ ቤት ነች እያልን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ከልባችን የምናምን ከሆነ «አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ» የአፍሪካዊነት ጠረኗ ጎልቶ እንዲገንን ተግተን ልንሠራ ይገባል።
ለንግግርም ሆነ ለአድራሻ ጠቋሚነት ወግ ባይበቁም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለይስሙላም ቢሆን በአፍሪካ አገራት ስም መሰየማቸው አልቀረም።ነገሩ «እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላ ግፋው» እንዲሉ ሆኖ ግን ከተሰጡት ስያሜዎች መካከል ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል የተሰጠውን የጎዳና ስያሜ ያህል በመለስተኛ ደረጃም ቢሆን በብዙኃን ዜጎች ዘንድ እነዚህ የአፍሪካውያን መንገዶች በስም ስለመታወቃቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።እንዲታወቁ ከልብ ስለመፈለጉም መጠርጠሩ አይከፋም።
በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅትና በኋላም በጉለሌው ጴጥሮስ ወጳውሎስ Cimitero Militare Italiano የዘላቂ ማረፊያ (መካነ መቃብር) ውስጥ አስከሬናቸው በክብር ያረፈው የወራሪው የኢጣሊያ ወታደሮች የሚታወሱትን ያህል በድሬዳዋ በሚገኘው “African War Cemetry, #1” መካነ መቃብር ውስጥ ከእንግሊዝ የቃል ኪዳን ወታደሮች ጋር ነፃነታችንን ለማረጋገጥ ገብተው የፋሽስት ወረራ ሰለባ በመሆን በድናቸው እዚያ ያረፈውን የአፍሪካውያን ወንድሞቻችንን የመቃብር ቦታ ምን ያህል ሰው እንደሚያውቀው ለመገመት ያዳግታል፡፡
እነዚህን መሰል ህፀፆችን ለዘመናት ተሸክመን መኖር ብቻም ሳይሆን ስህተቶቻችንን ለማረም እንኳን ጥረት ያለማድረጋችን እየታወቀ አፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን ግን ዛሬም ቢሆን ለአገራችንና ለሕዝባችን ያላቸው አክብሮትና ጽኑ ተስፋ ያለመሸርሸሩ ሊያባንነንና ሊያነቃን ይገባል።
የማጠቃለያ መልዕክታችንን የምንደመድመው «ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካዊነት ትመለስ!» በሚል አሟጋች ሃሳብ ነው።ከላይ የጠቀስነው የሰሞኑ የአፍሪካውያን ጉባዔ መሪ ሃሳብ «አፍሪካ ተነሽ! ‹Africa Arise›” የሚል መሆኑን ጠቅሻለሁ።በዚህ ጸሐፊ እምነት “Ethiopia Arise” የሚለው ዋና ሃሳብም መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም። ሰላም ለአፍሪካ፤ ለሕዝቦቿም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015