ወልዶ ለመሳም ያልታደሉ የመውለድን ፀጋ ለማግኘት የማይከፍሉት ዋጋ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጥሪታቸውን አሟጠው ሕክምናውን ከማግኘት የሚያግዳቸውንም አይቀበሉም። በአደጉት አገሮች ዕድሜ ለዘረመልና ለእንቁላል ለጋሾች መሀንነት ብዙም የማያስጨንቅ የሕይወት አጋጣሚ ሆኗል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግን ማህፀን ማከራየትም ሆነ አርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽን በሕግ የተከለከለ ስለሆነ ችግሩ አሁንም ችግር ሆኖ ቀጥሏል።
ሕክምናውም አገር ውስጥ የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አማራጮችን ለመከተልም ያለው ብቻ ነው የሚያገኘው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ለሚሊዮኖች ተስፋ የሚሰጥ ዜና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በኩል ተሰምቷል። ብዙዎችም ተስፋ አድርገው ዕድሉን ለመጠቀም እየተጠባበቁ ነው። ሆስፒታሉ በአገሪቱ ካለው የችግሩ ስፋት አንፃር በአገር ውስጥ የመካንነት ሕክምና መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተጀመረው የመካንነት ሕክምና ጽንስ ውጪ ላይ የሚፈጠርበት የኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን ዘዴን የሚከተል ነው። ይህ የሕክምና ሂደት በእኛ አገር ያልተለመደ ቢሆንም በቀሪው ዓለም በስፋት ይሠራበታል። ይኼን ዘዴ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው በ1970ዎቹ ሲሆን፤ ከጥንዶቹ እንቁላልና ዘረመል በመውሰድ ጽንስ እንዲፈጠር የማድረግ ሕክምና ነው።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ማዕከል በቀዶ ሕክምና፣ በሚዋጥ መድኃኒት የሚሰጡትን የመካንነት ሕክምና አገልግሎቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጥንዶች ሰጥቷል። በኢትዮጵያ ይህንን ሕክምና የሚሰጡ ሁለት የግል ተቋማት አሉ። በመንግሥት ደረጃ ሕክምናው ሲሰጥ ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመጀመሪያ ነው። በመጀመሪያው ዓመት 500 የሚሆኑ ጥንዶችን ለማከም ዕቅድ ይዞ ነበር የተነሳው፣ ቀጥሎ ግን በየዓመቱ 2ሺህ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ጥንዶችን እንደሚያክም አገልግሎቱ በተጀመረበት ወቅት መገለጹ ይታወሳል። እኛም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ከዶክተር ቶማስ መኩሪያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ መካንነት ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ቶማስ፦ መካንነት ማለት ከአንድ ዓመት በላይ ያለ መከላከያ በተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመፀነስ ያለመቻል ነው። ነገር ግን የሴት ዕድሜ 35 እና ከዚያ በላይ ከሆነ መካን ለመባል የሚያስፈልግበት ጊዜ እስከ ስድስት ወር ይሆናል። መካንነት 10 እስከ 15 በመቶ ጥንዶች (አንድ ከሰባት ጥንዶች ) የሚታይ ችግር ሲሆን፤ ይህ ማለት ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 45 ዓመት የሆኑት ጥንዶች ላይ በጣም የተለመደ ችግር ነው። ብዙዎቹ ጥንዶች የዕድሜም የጤናም ችግር ካልታየባቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አርግዘው የመውለድ ዕድል ይኖራቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ለመካንነት አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ቶማስ፦ የሴት ልጅ ዕድሜ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። በተለይ ወደ 30 እና 40ዎቹ ዕድሜ ላይ ስትደርስ ሁኔታው አስቸጋሪ ይሆናል። ለጤነኛ ሴት በ20ዎቹ ዕድሜ ወይም የ30 መጀመሪያዎቹ አካባቢ የማርገዝ ዕድሉ በየወሩ ከ25 እስከ 30 በመቶ ሲሆን፤ ነገር ግን በ40 ዎቹ ውስጥ ያለች ሴት ግን የማርገዝ ዕድሏ ከ10 በመቶ በታች ነው። ዕድሜዋ ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ሴት በወር ውስጥ አንዴም እንቁላል (የሴት ዘር) ካለቀቀች የማርገዝ ችግር ያጋጥማታል። ይህን ችግር ሊያመጡ ከሚችል ነገሮች የእንቅርት ህመም ሌላ የሆርሞን ችግሮች ናቸው። በተጨማሪ የወር አበባ በትክክል በየወሩ የማያዩ ሴቶች ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም ከመጠን በላይ ውፍረት መጨመር እና መቀነስ ይህን ችግር ሊያመጣ ይችላል።
የወንድ ዘር እና እንቁላል የሚገናኙበት ቦታ ማለትም የማህፀን ቱቦ መዘጋት ወይም መጎዳትም መካንነት ወይም ከማህጸን ውጪ እርግዝናን ያስከትላል። የማህጸን ጫፍ ካንሰር ችግርም እንዲሁ መካንነትን ከሚያመጡ ነገሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ነገር ግን ከስንት አንዱ ነው መካንነት የሚያመጣው። የማህፀን ጫፍ ካንሰር ከሚያስከትለው ችግር አንዱ ፅንስ ማህፀን ግድግዳ ላይ ተለጥፎ እድገቱን እንዳይጀምር የሚያደርግና መካንነትን የሚያስከትል ነው። ከተለመዱት የማህፀን ችግሮች መካከል የማህፀን ጠባሳ ፖሎፒስ ፤ ፋይብሮይድ ወይም ትክክለኛ ቅርጽ ያልያዘ ማህጸንን መጥቀስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ በአብዛኛው በባህላችንም ሆነ በእምነታችን መካንነት የሴቶች ችግር ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ይህ ትክክል ነው፤ የወንድ መካንነትስ አይከሰትም?
ዶክተር ቶማስ፦ ይከሰታል። መካንነት ወንድም ሴትም ላይ ሊገኝ የሚችል ችግር ነው። ነገር ግን በባህላችን የሚያረግዙት ሴቶች በመሆናቸው ምክንያት ካላረገዘች ችግሩ እሷ ጋር ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። ችግሩ እኩል በሴትም በወንድም ላይ የሚከሰት መሆኑን ነው ሳይንሱ የሚያረጋግጠው። በዚህም አንድ ሦስተኛው የሚሆነው የጥንዶች መካንነት ችግር በወንዶች ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፤ ሌላው አንድ ሦስተኛው የመካንነት ችግር ደግሞ በሁለቱም ጥንዶች በአንድ ላይ የሚከሰት ነው። እዚህ ላይ ወንዶች መካን የሚሆኑባቸው ምክንያቶች የወንድ ዘር አለመስራት እና የወንድ ዘር አለማመንጨት ናቸው።
ብዙ ጊዜ እንዲያውም በእኛ ሆስፒታል የሚያጋጥመን ችግር ጥንዶች አብረው ወደ ሕክምና ተቋም አለመምጣታቸው ነው። መጀመሪያ ሴቶች ናቸው የሚመጡት። ከዚያ በኋላ በብዙ ጥረት ግንዛቤውን መፍጠር ከቻልን በኋላ አብረው ይመጣሉ። በመሆኑም የመካንነት ችግር አጋጥሞናል ብለው የሚጠረጥሩ ጥንዶች በተቻለ መጠን ሕክምና ቦታ አብረው መጥተው ችግሩን አስረድተው ተገቢውን ድጋፍ ያገኛሉ። ስለዚህም ለውጤታማነቱ ጥሩ መንገድ የሚሆነው ይህ አካሂድ ነው። ችግሩ የማን እንደሆነ አልያም የሁለቱም መሆኑን አብሮ መረዳቱ በጣም አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መጀመሪያ ልጅ ወልደው መካከል ላይ የልጆች ቁጥር መጨመር ሲፈልጉ እምቢ የሚላቸው ሰዎችም አሉ።እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ጥንዶች ከዚህ ቀደም ልጆች ስለወለዱ ዳግም የመውለድ ዕድሉን ያገኛሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም በጤና ላይ የሚከሰቱ በርካታ ለውጦች ይኖራሉ። ልጅ አለ ማለት ወደፊት መካንነት አያጋጥምም ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ በአገራችን ያለው የሕክምና ሂደት ምን ይመስላል ?
ዶክተር ቶማስ፦ ጥንዶቹ አገልግሎቱን ፈልገው ሲመጡ መጀመሪያ በተለይም ሴቶች የሚደረግላቸው (የሚታዘዝላቸው) በማህጸን በኩል የሚታይ አልትራሳውንድ ነው፤ በዚህ ሕክምና በማህጸን ውስጥ እጢ ካለ፣ የእንቁላል መዛነፍ ተከስቶ ከሆነ፣ የእንቁላል መብዛት ወይም ማነስ ካለ ይታያል። የተለያዩ የሆርሞን ምርመራዎችም እዚህ ላይ ይካተታሉ። በወንዶች በኩል ደግሞ የወንድ ዘረመል ምርመራ ይደረጋል፤ የዘረመሉን ሁኔታ በአጉሊ መነጽር በሚገባ የማየት ሥራ ይሠራል። እዚህ ላይ ግን በተጨማሪነት ዕድሜያቸው በጋብቻ አልያም አብሮ በመሆን የቆዩበት ጊዜ ሁሉ ከግምት ገብቶ የምርመራው አካል ይሆናል።
ለሁሉም ሰው ግን አንድ ዓይነት ምርመራ ይደረጋል ማለት አይደለም።እነዚህ ሁሉ ምርመራዎች ከተደረጉና የሰዎቹ የኋላ ታሪክ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከተገናዘበ በኋላ ውጤቱ ያንን መሠረት ያደረገ ይሆናል።ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር ሰዎች ወልደው መሳም እንዲችሉ የሚያደርጉ ቀላልና ውስብስብ የሕክምና ዓይነቶች መኖራቸውን ነው።
ለትዳር መፍረስ ምክንያት የነበረው መካንነት በቀላሉ በሚዋጥ መድኃኒት ሊታከም ይችላል። ሕክምናው መካንነት እንደተከሰተበት ምክንያት የተለያየ ሲሆን፤ ለምሳሌ መካንነቱ የተከሰተው በእንቁላል ያለመመረት ችግር ከሆነ እንቁላሎች እንዲመረቱ የሚያደርጉ መድኃኒቶች በመስጠት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። ከዚህም ባሻገር አንዳንድ መካንነት የሚያስከትሉ እክሎች እጅግ ቀላል በሆነ ቀዶ ሕክምና መፍትሔ ያገኛሉ።
በቀዶ ሕክምናም ሆነ በመድኃኒት መስተካከል የማይችሉ ደግሞ አማራጭ ሕክምና አላቸው። ነገር ግን መካንነቱ የተከሰተው በሁለቱም በኩል በሚከሰት የቱቦ መዘጋት ከሆነ በመድኃኒትም በቀዶ ሕክምናም የመስተካከል ዕድሉ በጣም አናሳ ነው። እንዲህ ላለው ውስብስብ ችግር መፍትሔው ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን ነው። ኢንቪተሮ ፈርትላይዜሽን እንቁላል ከሴቷ፣ የወንዴ ዘር ፈሳሽን ከወንዱ በመውሰድ ጽንስ ውጭ ላይ እንዲፈጠር ማድረግና ወደ እናትየው ማህፀን መልሶ የመክተት ዘዴ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ሆስፒታሉ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ምን መልክ አለው ? የተገልጋዮች እርካታ ምን ይመስላል?
ዶክተር ቶማስ፦ ችግሩ በጣም ሰፊ ነው። በተለይም የእኛ አገርና ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካ አገራት ላይ ጎልቶ ይስተዋላል። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች በመኖር ሂደታቸው ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች መጋለጣቸው ሲሆን ይህ ኢንፌክሽን ደግሞ የመካንነት ችግርን ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ነገር ግን በአገራችን ሰፊና ወቅታዊ የዳሰሳ ጥናት ባይሠራም ያለው ችግር ሰፊ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በቂ ነው ለማለት ያስቸግራል።
ቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል ለየት የሚያደርገው በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ስለሚሰጥ ነው። በእርግጥ መካንነት ላለባቸው ጥንዶች ሌሎች ሕክምናዎችም ይሰጣል። ብዙ ሰዎች ለአገልግሎት ቢመጡም አሁን ላይ በእኛ አቅም ለማስተናገድ እየተቸገርን ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው አገልግሎቱን ለማግኘት እስከ አንድ ዓመት ድረስ የደረሰ ወረፋን ለመጠበቅ ይገደዳል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆርጣል። በመሆኑም ሆስፒታሉ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እንደ ጅምር ጥሩ ቢሆንም ተደራሽነቱ ላይ ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ። ካለው የተገልጋይ ብዛት አንጻርም ወደፊት ሌሎች ሴንተሮች ተከፍተው አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ካልተመቻቸ እርካታው በምንም መልኩ ሊመጣ አይችልም።
አዲስ ዘመን ፦ ሆስፒታሉ በመካንነት ሕክምና ዙሪያ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማጠናከር ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ቶማስ፦ በነገራችን ላይ ባለው ሁኔታ ራሱ ይህንን ብዙ ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ ሕክምና ሰዎች ሌላ አገር ሳይሄዱ ሳይንገላቱ እንዲያገኙ መደረጉ በራሱ ተስፋ ሰጪ ነው። መንግሥት ሌላው ቀርቶ በጤናው ዘርፍ ብቻ ብዙ የሚሠራቸው የሚያስተካክላቸው የሚያሟላቸው መሠረታዊ ችግር ያለባቸው ጉዳዮች አሉት። እናም አሁን ላይ በመንግሥት ይህ አልተሟላም፤ ያ ይቀራል ማለቱ ትንሽ ይከብዳል። ነገር ግን አቅም ያላቸው የግል ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ ያለውን ችግር በመረዳት ሕክምናውን ቢያሰፉት መልካም ነው።
ብዙ ሀብት የሚጠይቅ መሆኑን በማወቅ በሚችሉት ልክ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክሩም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ወጪ መጋራት ሲኖር ቅናሽና ውድድሮች ይሰፋሉ። እንደ እኛ ግን አሁን ላይ ማዕከሉ የግል ሕክምና መስጫ (ፕራይቬት ዊንግ ) በመክፈት በዚያ የሚገኘውን ገቢ ወደመደበኛው አገልግሎት ለማዞርና ሕክምናው ተደራሽና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማስቻል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም መንግሥት የፖሊሲ ክለሳዎችን በማድረግ የግል ሴክተሩ ላይ እንዲሰማራ ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡም ያለውን ልምድ ለሌሎች በማካፈል ሰዎች ጀምረው እንዳያቋርጡ በማድረጉ ሂደት ላይ መናገር ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ዶክተር ቶማለ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ