የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማትን ለማፋጠን እና ለማጠናከር ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ውህደት አስፈላጊነት በአፍሪካ ውሳኔ ሰጪዎች ዘንድ ትኩረት ካገኘ ውሎ አድሯል። አንድነት፣ ትብብር እና ውህደት የብዙ አፍሪካዊያን ልህቃን የረጅም ጊዜ ምኞት ነበር። ማርከስ ጋርቬይ፣ ዱቦይስ የመሳሰሉ ልህቃን እና አንቂዎች እንዲሁም እንደ ክዋሜ ንክሩማህ እና አጼ ሀይለ ስላሴ የመሳሰሉ መሪዎች አፍሪካን አንድ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን መዋለድ ችለዋል።
ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት በአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.አ.አ. በ1963 ሲያቋቁሙ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ውህደት እውን የሚሆንበትን ተቋማዊ ማዕቀፍ አስቀምጠዋል። የአህጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና ከተጠነሰሰበት 1979 የሞንሮቪያ ስትራቴጂ ጀምሮ በ1980 የሌጎስ የድርጊት መርሀ-ግብርና ከ1991ዱ የአቡጃ ስምምነት አንስቶ ተግባራዊነቱ በኢኮኖሚያዊ ትስስር ረገድ የአፍሪካውያን መሰረታዊ ጉዳይ ሆኗል።
እ.አ.አ በ2018 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የህብረቱ አባል ሀገራት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፋቸው የሚታወስ ሲሆን በ2021 ደግሞ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ንግድ ተጀምሯል። ይህም አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ረጅም ጉዞ ተምሳሌታዊ ክንውን ሆኖ ተመዝግቧል።
ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተምሳሌታዊ ክንውን መሆኑን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመር ውሳኔ በተላለፈበት ጥር 2021 የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ “የአፍሪካ አህጉርን አዲስ ዘመን ማምጣት የምንችልበት ወቅት ላይ እንገኛለን” በማለት ነበር የገለጹት። በአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናው የንግድ እንቅስቃሴ መጀመሩ የአፍሪካን የንግድ ሂደት እንደሚያሻሽል፣ የኢንዱስትሪ አብዮትን እንደሚያበረታታ፣ የስራ ዕድል እንደሚፈጥርና ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለትን እንደሚያቀላጥፍ ጠቅሰዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣናው ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የሚልቀውን የአፍሪካ ህዝብና ከ 3 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሆነውን አጠቃላይ አህጉራዊ ገቢ ያቀናጀ ግዙፍ የገበያ ዕድል የመፍጠር ዓላማ አለው።
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አምና ያወጠው ሪፖርት እንዳመላከተው፤ ቅልጥፍናን በሚገቱ እና የኢኮኖሚ እድገትን በሚገድቡ በተበታተኑ ገበያዎች የተያዘው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዓለም ኢኮኖሚ ግርጌ ላይ የሚገኝ ሲሆን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት የአፍሪካን የተበታተነ ገበያን ለመሰብሰብ እና የኢኮኖሚ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ከፍተኛ ሚና ይጨወታል። አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እ.ኤ.አ.በ1994 ከተመሰረተው የአለም ንግድ ድርጅት (WTO) ቀጥሎ በአለም ትልቁ አዲስ ነፃ የንግድ ቀጣና ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያወጠው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ እ.አ.አ በ2040 በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ከ15 እስከ 25 በመቶ ወይም ከ50 ቢሊዮን ዶላር ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳድግ ተንብዮአል። በ2019 የአለም ባንክ ባስቀመጠው ትንበያ መሰረት ደግሞ ስምምነቱ 30 ሚሊዮን የአፍሪካ ህዝብን ከአስከፊ ድህነት ያወጣል። ከድህነት ወለል ትንሽ ፈቅ ያለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 68 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውጥን በ2035 ለአህጉሪቱ 450 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል።
ስምምነቱ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የአህጉሪቱን እምቅ የኢኮኖሚ አቅም አሟጦ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እንዲሁም ውጤታማ የሀብት ድልድልን እውን በማድረግ በዓለም ገበያ የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ ተስፋ የተጣለበት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ስምምነቱ ለንግድ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በዓለም አቀፍ ገበያ የአህጉሪቱን የተወዳዳሪነት ኢንዴክስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ( አይ ኤም ኤፍ) ሪፖርት ያስቀመጠው ትንበያ ያሳያል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የሚመጣው የገበያ ተደራሽነት የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ልማትን፣ ቱሪዝምን፣ የኢኮኖሚ ሽግግርን፣ እና በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም መካከል ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው። ለዓለም የቢዝነስ ለሰዎች እና ንግድ ልዩ እድል ይፈጥራል። ለዓለም ሀገራት ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አዲስ ትልቅ ገበያ የመሆን እድል አለው።
በመጪው ቅዳሜና እሁድ “የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ትግበራ ማፋጠን’’ በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሚወያይባቸው አጀንዳዎች አንዱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት አተገባበር ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
በአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙታንጋ ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ አፍሪካን ለማስተሳሰርና አንድ ለማድረግ እንዲሁም አህጉራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከነዚህ ስራዎች መካከል አፍሪካን በትራንስፖርት ማስተሳሰር አንዱ ነው። አፍሪካን በትራንስፖርት ለማስተሳሰር እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የጠቆሙት አልበርት ሙታንጋ ተጨማሪ ትስስሮችን በመፍጠር የአፍሪካዊያንን ግንኙነት የበለጠ ለማደርጀት የአየር፣ የየብስ እንዲሁም የውሃ ላይ ትስስሮችን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት አፍሪካ አንድ መገበያያ እንዲኖራት፣ ያለ ቪዛ ከሀገር ሀገር መጓጓዝ እንዲቻል በአጠቃላይ የጋራ ገበያ እንዲኖር በተለያዩ ዘርፎች የማስተሳሰር ነው። እነዚህን ለመስራት ግን አሁንም መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች አሉ። ምርታማነትን ማሳደግ ከነዚህ ስራዎች መካከል ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። በኢንዱስትሪ እና በግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። ምርትን ማሳደግ ሳይቻል የገበያ ትስስርን መፍጠር ፋይዳ ቢስ ነው። ምክንያቱም ምርት ከሌለ ገበያ ቢኖር እንኳ የሚፈለገውን አህጉራዊ እድገት እውን ማድረግ አይታሰብም።
በአህጉሪቱ ውስጥ በሚገኙ አምራቾች መካከል ውድድርን ማበረታታትም እንዲሁ ወሳኝ ነው። በአህጉሪቱ አምራቾች መካከል ጤናማ ውድድርን ማበረታታት ወሳኝ ነው። ጤናማ ውድድር ባለበት የተሻለ ምርትና አገልግሎት ይኖራል። የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ የአንድ ማዕከላዊ ባንክ እና የአንድ መገበያያ ገንዘብ ወሳኝ ነው። ለዚህም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። የአፍሪካ ልማት ባንክን ማጠናከርና ማደርጀት ያስፈልጋል።
የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራው በተፈለገው ፍጥነት ሳይተገበር ሀገራቱ አሁንም በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ይገኛሉ። ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ሀገራት እንደ ኢኮዋስ ባሉ ቀጣናዊ የንግድ ቀጣና ትስስር ማዕከላት ጥሩ የሚባል ልምምድ ማዳበር የቻሉ ቢሆንም አንዳንድ ሀገራት ዛሬም ፈራ ተባ እያሉ ነው። በኢትዮጵያ በኩልም ጅምር እንቅስቃሴዎች ይታያሉ። ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ በነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ የመሳተፍ ልምዷ እምብዛም ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሀገር በቀል ኩባንያዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር ልማዳቸው ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ነው፡፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ከአሁኑ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ገበያዋን በማስፋት በነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ የሚኖራትን ሚና ከፍ እያደረገች መቀጠል አለባት።
ሀገሪቱ ለማይቀረው ውድድር ራሷን ማዘጋጀትና ወደ ውድድሩ መግባት አለባት። ይህ ማለት ግን ነጻ የንግድ ቀጣና በሚል በአንድ ጊዜ ገበያውን በመበርገድ የተወዳዳሪነት ልምድ የሌላቸውን የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍን ለአደጋ ማጋለጥ ማለት አይደለም። ከነጻ የንግድ ቀጣና ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ስምምነቶች እና ውይይቶች የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅምን የሚጎዳ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
በነጻ የንግድ ቀጣና የሚደረጉ ድርድሮች አሁንም የቀጠሉ ሲሆን፤ በነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውስጥ የሚካተቱ ምርቶች የኢትዮጵያን የቀረጥ ገቢ፣ የስራ እድል እና ሌሎች ሁኔታዎችን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ከህዝብ ኑሮ፣ ከስራ እድል፣ የኤክስፖርት አቅም ምን ያህል ነው የሚለውን ከአሁኑ መለየት ያስፈልጋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም