በ32 መስራች አገራት ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ለአገራችን እንግዳ የነበረው ኢቴቪ ይህንኑ ጉባኤ በማስተላለፍ ነበር ስራውን የጀመረው) እና በ1995 ዓ.ም ወደ አሁኑ ይዞታው የተሸጋገረው፤ የአፍሪካ ህብረት 36ኛ መደበኛ ጉባኤውን (ordinary Session) በመጪዎቹ ሁለት ቀናት (አርብ እና ቅዳሜ (18 – 19 ፌብሯሪ 2023)) እዚህ፣ አስተናጋጅ አገር በሆነችው ኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ያካሂዳል።
የመሪዎቹ ጉባኤ ከጉባኤው አስቀድመው ሁለት (16 – 27 January 2023: 45th Ordinary Session of the PRC (Ambassadors) እና 15 – 16 February 2023 42nd Ordinary Session of the Executive Council (Ministerial Session) ስብሰባዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ በእነዚህ ሁለት ስብሰባዎች ተቀርፀው፣ ለውይይት ቀርበውና ተጨምቀው ለመሪዎቹ ጉባኤ በሚቀርቡት አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
ይህ (ትርጉም የጸሐፊው) “የአየር ንብረት ለውጥ እና የአለም ምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ – የሰብአዊ ፍላጎቶች ቁልፍ ጉዳዮች” (Climate change and global food insecurity – key drivers of humanitarian needs) በሚል መሪ ሀሳብ (Theme) የሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እንደ ተለመደው ሁሉ በቁልፍ የአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ ይወያያል።
እንደሚታወቀው አፍሪካ በተለያዩ ችግሮች የተያዘች ናት ። “ሁሉም አጥኚዎች” በሚባል ደረጃ የሚስማሙባቸው አፍሪካን የፊጥኝ አስረው ከያዟት ችግሮች መካከል ስር የሰደደ ሙስና፣ የማህበራዊ አገልግሎት እጦት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ድርቅ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ የቴክኖሎጂ አለመስፋፋትና ስራ አጥነት፤ በተለይ የሰላም እና ፀጥታ አለመኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ይህ የሚያሳየን አቢይ ጉዳይ ቢኖር የአፍሪካ መሪዎችም ሆኑ ጃንጥላ ድርጅታቸው /አፍሪካ ህብረት በእነዚህ የአፍሪካ የከፉ ችግሮች ላይ አንድ ሆነው፣ አብረውና ተባብረው መስራት ያለባቸው መሆኑን ነው።
በርግጥ እነዚህ በስራቸው በርካታ የችግር አይነቶችን የያዙ አንኳር አንኳር ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱ ብዙ ርቀቶችን ሄዷል። የተለያዩ ደንብና መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በማፀደቅ ስራ ላይ እንዲውል መመሪያ ሰጥቷል። ተግባራዊ ተደርጓል አልተደረገም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፤ ዋና ዋናዎቹን መጥቀስ ይቻላል።
በሩዋንዳዋ ዋና ከተማ ኪጋሊ (በ2018) የተሰባሰቡ 44 የአፍሪካ ሃገራት (ኢትዮጵያን ጨምሮ) መሪዎችና የሃገራት ተወካዮች ደርሰውበት የነበረውን ስምምነት መጥቀስ ይቻላል። “በዚህ ስምምነት 80 በመቶ በሚሆነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት እንዲሁም 70 በመቶ መደበኛ ያልሆነ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እና ወጣቶች ዋነኛ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ” ይላል። በአፍሪካ ሃገራት መካከል ድንበር የማያግዳቸው የንግድ ልውውጦች እንዲካሄዱ እንደሚያግዝ፤ አልፎም ግብር እና አስመጭዎች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ በማስቀረት በአህጉሪቱ ሃገራት መካከል ያለውን ነፃ ዝውውር እንደሚያበረታታ ብዙ የተባለለትን በአህጉሪቱ ነፃ የንግድ ዝውውር እንዲኖር ያስችላል የተባለለትን ስምምነት ማንሳት ይቻላል።
“አንድ ማዕከላዊ ገበያ፣ ነፃ ቪዛ (አህጉራዊ ፓስፖርት ተግባራዊ ማድረግ)፣ ማርሻል ፕላን የሆነው አጀንዳ 2023፣ አፍሪካን ከጠብ መንጃ (ተኩስ) ነፃ የማድረግ ውሳኔ፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት፣ የወጣት አፍሪካዊያን ትስስር (ዮዝ ኮኔክት አፍሪካ)፣ አፍሪካ እንደ አህጉር በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት (ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ውስጥ የራሷ የሆነ ድምፅ እንዲኖራት የማድረግ እንቅስቃሴ።
“በአህጉሪቱ የሚገኙ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሰዎችን የሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊ መብቶች ተጠቃሚ የማድረግና አንድ የተባበረ አፍሪካ መንግስት የመፍጠር (ይህ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የፈጀና የፓን አፍሪካኒስቶቹ አጀንዳ ነበር) ራእይ ነድፏል። ተግባራዊ ተደርጓል አልተደረገም የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው።
ምንም እንኳን ተቺዎች ከፈረሱ ጋሪው ቢሉም (ድህነትን ማስወገድ ላይ መስራት የሚገባው መሆኑን በመግለፅ)፣ በኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዙማ (Dlamini- Zum) አስተዳደር ዘመን ህብረቱ፣ እኤአ በ2028 አህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክን፣ አህጉራዊ ፓርላማን እና አንድ የጋራ መገበያያ ገንዘብን ለማስተዋወቅ ማቀዱም ከዚሁ ጋር ማስታወሱ የግድ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የወቅቱ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በ2018 በአፍሪካ ህብረት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ አገራት “ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት የተለያዩ የጋራ እቅዶችን ቢያወጣም “አህጉሪቱ ግን አሁንም ውህደትን አስቸጋሪ በሚያደርጉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ውስብስብ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተተብትባለች” የሚለው ትችት ጎልቶ የሚሰማ ነው፤ የአህጉሪቱ አገራት መሪዎች ለህብረቱ ደንብና ህግጋት ተገዥ ያለመሆን ችግር ለውሳኔና ስምምነቶቹ ገቢራዊነት እንቅፋቶች ሆነዋል የሚለውም ሌላኛው ነው።
“አፍሪካ አንድ መንግስት ሆና አፍሪካዊያን ከኬፕታውን እስከ ካይሮ፣ ከዳካር እስከ ዳሬሰላም በቀላሉ መዘዋወር (በነገራችን ላይ፣ አንድም አፍሪካዊ ያላገኘውን እድል በማግኘት፣ አሜሪካዊያን ያለ ምንም አይነት ቪዛ ከሃያ በላይ የአፍሪካ ሀገራት መጓጓዝ እንደሚችሉ ያውቃሉን?)፣ ሰርቶ መኖር ወይም ያለገደብ መነገድ የሚችሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚል ጥያቄን የሚያነሱ የመኖራቸውን ያህል “አዎ ይመጣል” የሚሉ ባለ ብርቱ ተስፋዎችም አሉ።
ለሁሉም ግን፣ የአህጉሪቱ መፃኢ እድል የጃንጥላ ድርጅቱ (አፍሪካ ህብረት) ጠንክሮ መስራትና ስትራቴጂካሊ ማሰብ፤ የአባል አገራት መሪዎችም እቅዱን (በተለይም ሁሉን አቀፍ መሆኑ የሚነገርለትን አጀንዳ 2063) ወደ ተግባር መቀየር ላይ የተንጠለጠለ ነውና እሱ ላይ መበርታት የግድ ይሆናል። ይህ ከሆነ መጪው ዘመን ለአፍሪካ ብሩህ ነው።
መልካም የጉባኤ ቀናት፤ መልካም የአዲስ አበባ ቆይታ ለታዳሚ መሪዎቹ!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም