የአፍሪካ ሀገሮች ባደረጉት ዘመናትን የወሰደና ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፈለ ተጋድሎ ከቅኝ ገዥዎቻቸው መዳፍ ነጻ መውጣት ችለዋል። ይህን ድል በመቀዳጀትም በሀገራቸውና በአህጉራቸው እጣ ፈንታ ላይም መወሰን በሚያስችላቸው ማማ ላይ ተቀምጠዋል።
እነዚህ ሀገሮች ከነጻነት በኋላም ነገሮች አልጋ ባልጋ አልሆኑላቸውም። ዛሬም ከቅኝ ገዥዎቻቸው ጣልቃ ገብነት ያልተላቀቁበት ሁኔታ በስፋት ይታያል። እጣ ፈንታቸውን ራሳቸው መወሰን ሲገባቸው ምዕራቡ ዓለም ካልወሰንኩላቸው እያላቸው ነው የኖረው። ከነጻነት በኋላ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በእጅጉ ተፈትነዋል።
አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በአፍሪካውያን የውስጥ ጉዳይ ጭምር ጣልቃ በመግባት ብዙ አሲረዋል፤ የአህጉሪቱን ሀብት ለመቀራመት ያልጫሩት ግጭት፣ ያላቀጣጠሉት ግጭትና ጦርነት የለም። እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን አሻፈረኝ ያሉ አፍሪካውያን እጣ ፈንታቸው በመፈንቅለ መንግስት መነሳት ሆኖ ኖሯል፤ በመሪዎቻቸው ላይ ተቃዋሚ በማደራጀትና የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ በማድረግ በኃይል ሰብረዋቸዋል። በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ የውስጥ ጉዳዮቻቸው እንዲከፉ ተደርገዋል።
የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዙ አፍሪካውያን በራሳቸው እንዳይቆሙ፣ ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዳይፈቱ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ አፍሪካ ብዙ ፈተናዎች ደርሰውባታል፤ በዚህም አያሌ አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው እንዲጫረሱ ተደርገዋል፤ ተሰደዋል፤ ከሞቀ ቤታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጎም ለተረጂነት ተዳርገዋል።
አንዳንዶቹ ችግሮች እግርና እግርም ይጋጫል አይነት ሆነው ሳለ ነው የአህጉሪቱ ጠላቶች ችግሮቹን በማራገብና በማባባስ በቀላሉ ሊፈቱ እንደማይችሉ አድርገው በማሳየት፤ ለመፍትሄው ከእነሱ መላ ውጪ አፍሪካውያን መፍትሄ እንደሌላቸው አድርገው በማሰብ ፈተናቸውን አባብሰውት ኖረዋል።
ነገሮችን በማጦዝም ለመፍትሄዎቹ ብዙ ርቀቶችን በመጓዝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በአረብ ሊግ፣ ሌሎች ሃያላን ሃገራት በኩል እንዲፈቱ ለማድረግ ብዙ ደክመዋል።
ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን ሊፈቱ የሚችሉባቸው መንገዶች እንደሌሏቸው አድርገው በማሳየት ነው። ይህ ሁኔታ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቀይሯል። ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ታሪክ ሰርታለች።
ኢትዮጵያ የታላቁ የዓባይ ግድብ ጉዳይ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ እንዲታይ በታችኛው የተፈሰሱ ሀገሮች በኩል ጥያቄ ቢቀርብም፣ ጉዳዩ አፍሪካዊ መፍትሄ ነው የሚያስፈልገው ብላ ወደ ቤቱ እንዲመለስ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ለእነዚህ ተቋማት በተደጋጋሚ ከሰዋታል። ሀገሪቱ ግን ችግሩ አፍሪካዊ ነው፤ መፍትሄውም አፍሪካዊ ነው በማለት ጉዳዩ በአፍሪካውያን እንዲታይ አድርጋለች። በእዚህ ጽኑ አቋሟም መንግስት ከሕወሓት ጋር ሲደረግ የነበረውን ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ የሰላም ውይይት ስምምነት መፍትሄ እንዲያገኝ አድርጓል። በሰላም ስምምነቱ መሰረትም መፈጸም ያለባቸው ተግባሮች አንድበአንድ እየተፈጸሙ ይገኛሉ።
ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚቻል አጥብቃ ስታስገነዝብ የቆየችው ኢትዮጵያ፤ በዚህ የሰላም ስምምነት ለአህጉሪቱ ችግር አህጉራዊ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚቻል በሚገባ አሳይታለች። አፍሪካም ይህን የኢትዮጵያን ሃሳብ በመጋራት ባደረገችው ስኬታማ የማስማማት ተግባር ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን የኢትዮጵያን ጽኑ አቋምና ስኬት ተቋድሳለች።
የአፍሪካ ኅብረት ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ሀገሮችም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በእዚህ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ወቅት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።
በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ‹‹ስምምነት›› በሚል ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ብዙ እልቂትን፣ የሀብት ውድመትን፣ የልማት መስተጓጎልን፣ የገጽታ መጠልሸትን ፣ በጠላትነት መፈራረጅን ያስቀረ ታላቅ ስኬት የተገኘበት የሰላም ስምምነት ነው። በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ስራ እንዲጀምሩ ያስቻለ፣ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን እንደገና ያስመለሰ፣ ምግብና መድሃኒትን የመሳሰሉ ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ በየአቅጣጫው እንዲገቡ ያስቻለ፣ የአውሮፕላን በራራን ወዲያውኑ በዚህ በጦርነቱ የተራራቁ ቤተሰቦችን ያገናኘ ታላቅ ድል ነው።
በአፍሪካ ከሚደረጉ ስምምነቶች አኳያም ሲታይ በእጅጉ የተለየ ሊባል የሚችል ነው። በአፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይቆይ የሚጣስበት ሁኔታ ብዙ ነው። ይህ የሰላም ስምምነት ግን በጥሩ ሁኔታ እየተተገበረ የሚገኝ እንደመሆኑ የተለየ ሊባል የሚችልም ነው። ይህም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ ከመፍታትም በዘለለ ለአፍሪካ ችግሮች በእጅጉ ውጤታማ አህጉራዊ መፍትሔ የሰጠ ቢባልም ያስኬዳል።
በዚህም ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ሆናለች። ስኬቱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኅብረትም እንደመሆኑ አፍሪካ ኅብረትንም ትምህርት ቤት ማድረግ ችላለች። ከእንግዲህ ወዲህ የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዝ የሚፈልጉትንም የአህጉሪቱን ሀገሮች ማስቀረት መቻል አለበት። ኢትዮጵያ ውጤታማ የአህጉሪቱን ችግሮች መፍቻ አድርጋ የተጠቀመችበት ሰላማዊ አማራጭ ላይ የተመሰረተውን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ እንደ እርሾ በመጠቀም የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታት መስራት ይኖርበታል።
በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤም ለዚህ የኢትዮጵያ ስጦታ ለሆነው የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ ታላቅ ሀሳብ ትልቅ ስፍራ ሰጥቶ በመመልከት ለአህጉሪቱ ችግሮች መፍቻ ሊያውለው ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም