በዚህ በወርሃ የካቲት ብዙ የጀግንነት ታሪካዊ ድሎች አሉ። ከእነዚህ አንዱ የፊታችን እሁድ የካቲት 12 ቀን ታስቦ የሚውለው 86ኛው የሰማዕታት ቀን ነው። ይህ ቀን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ሲታገሉ የተሰዉበትን ለማስታወስ ነው።
ጀግንነት ለኢትዮጵያውያን ምን እንደሆነ ከሚያሳዩን ነገሮች አንዱ የስነ ቃል የኪነ ጥበብ ሥራዎች ናቸው። እነዚህ የስነ ቃል ውጤቶች የሕዝብ ናቸው። ሕዝብ ስሜቱን የሚገልጽበት ማለት ነው። ስለዚህ የአንዲትን አገር ሕዝብ ስነ ልቦናዊ ምንነት ይናገራሉ። እነዚህን የጥበብ ሥራዎች እስኪ በዚህ በየካቲት ወቅት እናስታውሳቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በክብሩ ለመጣበት ሁሉ የማይመለስ ጦረኛ መሆኑን እነዚህ የስነ ቃል የኪነ ጥበብ ውጤቶች ይመሰክራሉ። ጦርነት ሲባል ግን የግድ ከዋናው የውጭ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት ብቻ አይደለም፤ የውስጥን ገመና አሳልፈው የሚሰጡ ‹‹ባንዳዎች›› አሉ። እንዲያውም የአገር ውስጥ ከሃዲ ይከፋል፤ ምክንያቱም ለውጭ ጠላት አሳልፎ ይሰጣል። ለእንዲህ ዓይነቱ ከሃዲና ባንዳ እንዲህ ሲባል ተዘፍኗል።
ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው
‹‹አሾክሿኪ›› ማለት ወሬ አቀባባይ፣ ቧልተኛ፣ ነገር አመላላሽ… ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከግጥሚያው ውስጥ አይገባም። ‹‹እገሌ እንዲህ አለህ›› እያለ ነገር ነው የሚያቀባብል። ለሁለቱም ተጋጣሚዎች ወዳጅ መስሎ ነገር ያቀባብላል። በዘመነ መሳፍንት ዘመን የተባለ አንድ የአዝማሪ ታሪክ እናስታውስ።
ከ170 ዓመታት በፊት ኅዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም ጎርጎራ ላይ በደጃች ካሣ (በኋላ አጼ ቴዎድሮስ) እና በደጃች ጎሹ መካከል ጎርጎራ ላይ ወሳኝ ጦርነት እየተካሄደ ነው። የደጃች ካሳ ጦር የሚሸነፍ መስሎት አንድ ጣፋጭ የተባለ አዝማሪ ለደጃዝማች ጎሹ ወግኖ እንዲህ አለ።
እስኪ ተመልከቱት ይሄን የኛን እብድ
አምስት ጋሞች ይዞ ጉራምባ ሲወርድ
ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ
ወርደህ ጥመድበት ከሽምብራው ማሳ
አዝማሪው ይሄን ከማለቱ የደጃዝማች ጎሹ ጦር ተሸነፈ። ድል የአጼ ቴዎድሮስ ሆነች። ‹‹እንዲያው ምን እብድ ነኝ አጼ ቴዎድሮስ ይሸነፋል ብዬ አፌ ያመለጠኝ›› ሲል ተቆጨ። ወዲያውም ተይዞ አጼ ቴዎድሮስ ፊት ቀረበ። ይሉኝታውን ጥሎ፣ ሀሳቡን ቀይሮ ተገለበጠና ከአጼ ቴዎድሮስ ፊት እንዲህ አለ።
አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የእግዜር ቁጣ
አፍ ወዳጁን ያማል የሚሰራው ሲያጣ
ሽመል ይገባዋል ያዝማሪ ቀልማጣ
ብሎ በራሱ ላይ ፈረደ። አጼ ቴዎድሮስ እንዲህ ዓይነት አሽቃባጭ አይወዱም ነበርና አዝማሪውም በሽመል ተደብድቦ ተገደለ። እንግዲህ በጠብ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ነገር አቀባባይ ነው ‹‹አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው›› የተባለው። ከዚህም ከዚያም ወዳጅ ለመምሰል የአድርባይነት ሥራ ይሠራል። ዓላማው ማንም ያሸንፍ ማን ከአሸናፊው ወገን መሆን ብቻ ነው። በጣሊያን የአምስት ዓመቱ ቆይታ ወቅት እንዲህ ዓይነት ሥራ ሲሠሩ የነበሩ አሉ።
የኢትዮጵያውያን የጦርነት ስነ ልቦና እንዲህ ነው እንግዲህ! ይህ የሚያሳየን ግልጸኝነትን ነው። ‹‹ከአስመሳይ ወዳጅ ግልጽ ጠላት ይሻላል›› የሚባለው የኢትዮጵያውያን አባባልም ይህንኑ ግልጸኝነትና ደፋርነት ያሳያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ለክብሩ ሟች ነው። ክብሩን የነካበትን ሁሉ አይታገስም። አሁንም የጥንት ስነ ቃሎች ምስክር ይሆኑናል። እምቢ ብሎ ጠብ ፍለጋ የሚመጣን ሰው ልኩን ማሳየት ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ጠብ ጀማሪ እንደ ፈሪ ነው የሚታይ፤ እንደ ጀግና የሚታየው ጠቡን የሚጨርስ ነው። ጠብ ከጀመረ በኋላ ሲጨንቀው ‹‹እባካችሁ አስታርቁኝ›› የሚል ከሆነ እንዲህ ተብሎ ይሸለልበታል።
ረጅም ምንሽር ተኩሱም ረጅም ነው
ከተጣሉ ወዲያ ‹‹አስታርቁኝ›› ምንድነው!
ይሄ ማለት ግን ለሽምግልና ቦታ የላቸውም ማለት አይደለም። ጠቡ ከመጀመሩ በፊት ‹‹እባካችሁ እገሌን ተቆጡት›› እያሉ ለጓደኞቹ ይነግራሉ። ብዙ ጊዜ መታገስ የጀግንነት፤ ግልብነት ደግሞ የፈሪ ምልክት ተደርጎ ነው የሚታሰብ። ‹‹ጅል ሲያከብሩት የፈሩኝ ይመስለዋል›› የሚለው ምሳሌያዊ ንግግርም ተጨማሪ ማሳያ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ግልብ ድርድርን ሁሉ አሻፈረኝ ይልና ጠብ ይጀምራል፤ በኋላ ማጠፊያው ሲያጥረው ‹‹የሽማግሌ ያለህ!›› ይላል። ትዕግስተኛ ደግሞ ትዕግስቱን የጨረሰ ዕለት አይመለስም። የዳግማዊ አጼ ምኒልክና የጣሊያን ሁኔታም እንደዚያ ነበር። በአንቀጽ 17 እንዳልተስማሙ በትዕግስት እየተነገረው ነው ጣሊያን ወደ ጦርነት የገባው።
ጀግና በነብር ይመሰላል። ነብር የሚባለው እንስሳ ኃይለኛና አስፈሪ ነው። ደስ የሚለው ባህሪው ግን ካልነኩት አይነካም። ዋሽንት ከሚጫወት እረኛ ጋ ቁጭ ብሎ ሲያዳምጥ ቆይቶ ይሄዳል። ይሄን ባህሪውን የሚያውቁ እረኞች ነብር ሲያዩ ድንጋይ አያነሱም። ከተቻለ ቀስ ብለው ከአካባቢው ያመልጣሉ፤ ካልተቻለ ግን ወደ ነብሩ ምንም ነገር ሳይወረውሩ ዝም ማለት ነው። ምንም ነገር ሳያደርጋቸው ቀጥ ብሎ አልፎ ይሄዳል። ለዚህ ባህሪው ነው የጀግና ማነፃፀሪያ ሆኖ እንዲህ የተባለለት።
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው
ጠብ ጀማሪዎች እንደ ፈሪ ነው የሚታዩት። የፈሪ ምልክት ደግሞ አስቀድሞ ጉራ ያበዛል። የቃል ግጥሞች ባለቤት የገጠሩ ማህበረሰብ ነውና እዚያው ያየሁትን ነው ምሳሌ የማደርግ። ከሰው ለመጣላት አሥር ጊዜ ዱላ የሚያማርጡ ሰዎች ይሳቅባቸዋል። እንደ ፈሪ ነው የሚታዩት። ‹‹ዋናው ልብ ነው እንጂ ዱላ ብቻውን አይማታ!›› ይሏቸዋል። ጠብ ጀማሪው (ፈሪው) ዱላውን ያሻሸዋል፣ ይቀባባዋል፣ አሥር ጊዜ እያነሳ ያየዋል። እንዲህ ዓይነቱ ተጋጣሚ ጭንቀት ስለሚያበዛ ጠቡን አይወጣውም ተብሎ ነው የሚታመን። ለዚህም ነው በቀረርቶና ፉከራ ጊዜ እንዲህ ይባልበታል።
ምን ይተሻሻል እንደ ቅቤ ቅል
መመከትና መሸሽ ለየቅል!
እነዚህ የማህበረሰቡ የስነ ቃል ውጤቶች ከጥንት ጀምሮ ሲወርዱ ሲወራረዱ የመጡ ናቸው። በአንድ ጊዜ ሁኔታ ላይ ብቻ ተመስርተው የተባሉ አይደሉም።
በአገር ቤቱ ማህበረሰብ ዘንድ የአባቶች ምክርና ግሰጻ ትልቅ ቦታ አለው። ወጣቶች በደም ፍላት ወደ ጠብ ለመግባት ቢነሱ እንኳን አባቶችን ይፈራሉ። ይህኔ ተጋጣሚው የተፈራሁ ይመስለውና ወሰን አልፎ ይገባል። ነገሩ ከልክ ሲያልፍ ግን አባቶችም ‹‹በለው›› ሊሉ ይችላሉ። ወጣቶችም እንዲህ ሲሉ ትዕዛዝ ይጠብቃሉ።
‹‹በለው›› በለኝና ላሳጣው መድረሻ
የሰው ልክ አያውቅም ባለጌና ውሻ!
በነገራችን ላይ ውሻ ከሰውም በላይ ታማኝ ነው። የዚህ ቃል ግጥም ዓውድ ግን በገጠሩ አካባቢ ነው። ገጠር ውስጥ ውሻ ብዙም ትኩረት ስለማይሰጠውና በቂ ክትትል ስለማይደረግለት በከተማ አካባቢ የምናውቀውን የውሻ ባህሪ የላቸውም። ከቤት የመጣ እንግዳን ሁሉ ካልተናከስን ይላሉ።
ከላይ ያየናቸው የቃል ግጥሞች በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ለሚደረጉ ፍልሚያዎች ናቸው። እነዚህን ያመጣሁበት ምክንያት ደግሞ በትልልቅ ጦርነቶች ውስጥ ይባሉ የነበሩት በሰፊው ስለሚታወቁ ነው። በመጽሐፍና በታዋቂ ዘፋኞች ውስጥ ስለሚደጋገሙ ነው። ዳሩ ግን የእነዚህም መልዕክት ጥልቅ ነው። በግለሰብ ደረጃ የተነገረው ለቡድንም ይሆናል። ለምሳሌ ‹‹የሰው ልክ አያውቅም ባለጌና ውሻ›› የተባለው እንቶኔ ለተባለ አንድ ሰው ብቻ አይደለም። ለቡድንም ይሆናል፤ ለአገርም ይሆናል። ይሄንኑ ግጥም በጣሊያን ወረራ ጊዜ ተጠቅመውት ይሆናል።
ቀደም ሲልም እንዳልኩት ነገር አመላላሽና አስመሳይ ከዋናው ጠላት በላይ ትኩረት ይደረግበታል። ምክንያቱም ምሥጢር እያወጣ ለጠላት የሚሰጥ እሱ ነው። ሆኖም ግን አንዳንዱ ተጋጣሚ ደግሞ ዋናውን ጠላትም ነገር አመላላሹንም ሊንቃቸው ይችላል። ሁለታችሁም ምንም አታመጡም ለማለት ይመስላል እንዲህ ሲል ይሸልላል።
አንድ መልክ በሮች ከዳገት ጠምዳችሁ
ኋላ መመለሻው እንዳይቸግራችሁ
‹‹የማያድግ ጥጃ በማሰሪያው ያስታውቃል›› እንዲሉ አንዳንድ ጠብ ጀማሪዎች ገና ከጅምሩ ነው እንደማይወጡት የሚያስታውቅ። ደረጃቸው የማይገናኝ ሆኖ ያለ አቅሙ ግጥሚያ ለሚፈልግ ደግሞ እንዲህ ተብሏል።
ተንኮለኛ ጠቦት ልቡ ያበጠበት
‹‹እንገናኝ›› ብሎ ለነብር ላከበት
የፍየል እና የነብር ባህሪ ይታወቃል። ፍየል ነብርን የሚቋቋምበት አቅም የለውም። እነዚህ የቃል ግጥሞች ሁሉ የሚያሳዩን ጠብ ጀማሪ እንደሚፈረድበትና መጨረሻውም እንደማያምር ነው። ትዕግስት የጀግና ምልክት መሆኑን ነው። በሌላ በኩል ከዚያ እና ከዚህ ነገር የሚያቆሳቁስ አካልም ጠላት መሆኑን ነው።
የኪነ ጥበብ ጥሩ ነገሩ ይሄ ነው። ታሪክን እንዳይረሳ አድርጎ ያስቀምጣል። ኪነ ጥበብ በባህሪው ወደ ሰው አዕምሮ ውስጥ የመስረጽ ኃይል አለው። ይህ በጦርነት ወቅት ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ሥርዓት ሲቀያየርም የምናየው ነው። በንጉሡ ጊዜ እና በደርግ ጊዜ የጥበብ ሥራዎች ይዘት ወቅቱን የሚመስል ነበር። ኢህአዴግም ሲገባ ‹‹እንዳያልፉት የለም…›› በሚል ህብረ ዝማሬ እና በእነ ህላዬ ዮሴፍ ግጥም ነበር። ኪነ ጥበብ ስሜት ቀስቃሽ ስለሆነ የጦርነት ወይም የርዕዮተ ዓለም ስትራቴጂ ነው።
አስታውሳለሁ፤ ልጅ እያሁ፤ በኢትዮ ኤትርራ ጦርነት ጊዜ የአካባቢያችን ወጣቶች ወደ ገበያ እንዳይሄዱ ይጠበቁ ነበር። ምክንያቱም ገበያው ውስጥ ‹‹አስረስ ጎነበ›› የምትባለው የባህል ዘፋኝ የሽለላ ዘፈን ይከፈት ነበር። ሽለላው ወኔ ቀስቃሽ ነው። ወጣቶች ያንን ሲሰሙ ሄደው ይመዘገባሉ። እንዲያውም ለመመዝገብ ያልሄደ እንደ ፈሪ ይታይ ነበር። ሰፈር መጥተው ተመዝገቡ ቢባል ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ፤ በዚያ ቀረርቶና ፉከራ ግን ካልተመዘገብኩ ብለው ነበር የሚጣሉ። መንግሥት ያንን ዘዴ የተጠቀመ የኪነ ጥበብ ጉልበት ስለገባው ነው። በማይክራፎን እየዞረ ተመዝገቡ ማለት ይችል ነበር፤ ግን ስሜት ቀስቃሽ ሆኖ ያገኘው ኪነ ጥበብን ነው።
ሌላው የኪነ ጥበብ ሚና ደግሞ እንዲህ የሕዝብን ስነ ልቦና በስነ ቃል በኩል ሰንዶ ማስቀመጡ ነው። የቃል ግጥሞቹ በሕዝቡ ውስጥ በቃል የሚባሉ ናቸው። ስለዚህ የቃል ቅርስ ናቸው ማለት ነው።
ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም