‹‹ዛሬ ከሰባት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረኝ ጉልበት ደክሟል። አልጋ ላይ ከዋልኩ ዓመታት ተቆጥረዋል። የሚያነሳ የሚያስቀምጠኝም ሰው ነው። ቢሆንም ወኔዬ አልሞተም። የትኛውም የአገሬ ጥቃት ይሰማኛል። የማንኛውም የሰው ዘር በደል በሙሉ ይመለከተኛል›› ይሄን የሚሉት አባት አርበኛና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል እንዲሁም የቃኘው ሻለቃ ጦር አባል ባሻ አስፋው አበበ ናቸው።
ባሻ አስፋው አበበ የዛሬን አያድርገውና አልጋ ላይ ከመዋላቸው በፊት አንበሳ ነበሩ። በ1943 ዓ∙ም ኮርያ ዘምተው ሲመለሱ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ላገራቸው ባቀረበው ጥሪ መሠረት በድጋሚ ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ አቅንተው ተዋግተዋል። ባሻ ከኮርያም ከኮንጎም በድል ነው የተመለሱት። ቁጥራቸውን በውል ባያስታውሱትም እሳቸው በተሳተፉበት በኮንጎ ውጊያ የተሳፉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር እንደ ኮርያው ብዙ አይደለም። ጥቂት ነው። አንዳንዶቹ እንደሳቸው ከኮርያ ጦርነትና ድል መልስ በድጋሚ በቀጥታ ኮንጎ ኪንሻሳ ጦርነት ላይ በመዝመት የተሳተፉ ናቸው።
በኮንጎ ጦርነት ውጊያ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን እሳቸው እንደነገሩን አብዛኞቹ በሕይወት የሉም። በዕድሜም አስተዋሽ በማጣትም እየተዳከሙ አልቀዋል። የ105 ዓመቱ ዕድሜ ባለፀጋ ባሻ አስፋው አበበ ስለ ኮንጎ ዘመቻ ብዙ የሚያውቁት ታሪክ ቢኖርም ከዚህ በላይ ሊያወጉን አልቻሉም። አብረዋቸው ወደ ኮንጎ የዘመቱት ጓዶቻቸውን ስም እንኳን ለማስታወስ ቢሞክሩ አልቻሉም። በጨዋታችን መካከል ድካም ከዕድሜ ጋር ተጋግዞ እንደ እንቅልፍ ሽልብ እያደረገ ይወስዳቸዋል።
እኛ እንዳስተዋልነው የኮንጎ ኪንሻሳ ዘማቾች የአገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ባለውለታ ቢሆኑም እንደ ኮርያው ዘማቾች ብዙ አልተዘመረላቸውም። ለእነሱ ተብሎ የተመሠረተ ማህበርና የቆመ ሐውልት ቀርቶ በሕይወት ከነመኖራቸውም የሚታወቅ አይመስልም። በተለይ የኮንጎው ጦርነት ከኮርያ ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ በ1952 ለአገራችን በተደረገ ጥሪ የተካሄደ በመሆኑ የኮርያ ዘማቾች በሕይወት እያሉ የኮርያዎቹ በዕድሜ ብዛት ሞተው አልቀዋል። ያሉትም ቢሆን አስተዋሽ በማጣት በየጓዳው ተቸግረው ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል።
ተተኪ አርበኛ በቀለ ዳባ እንደሚናገሩት አፍንጮ በር ናይጄሪያ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘውን ፓርክ፤ «የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ» ተብሎ ተሰይሟል። በፓርኩም ውስጥ ለደቡብ ኮርያ ነፃነት ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ሲተናነቁ ለወደቁ 122 የቃኘው ሻለቃ ጀግኖች የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል። በፓርኩ በተገነባው ሙዚየም ውስጥም ጦርነቱን የሚገልጹ የፎቶግራፎች፣ በጦርነቱ ወቅት የነበሩ ታሪካዊ የጦር መሣሪያዎችና ሌሎች አሻራዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም የኮርያ መንግሥት ለባለውለታዎቹ አርበኞች ያሠራላቸውና አፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኝና የሚከራይ ሕንፃም እንዳለ ያውቃሉ። የዚህ ሕንፃ ገቢ ለማኅበሩ አባላት ይከፋፈላል፤ ጃንሜዳና የቀድሞ ክብር ዘበኛ ካምፕ አካባቢ የሚገኘው አደባባይም በቃኘው ሻለቃ ጦር ስም ተሰይሟል ባይ ናቸው።
ሆኖም ለኮንጎ ዘማቾች እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አልተደረገላቸውም። እንዲያውም አስተዋሽ ያላቸው አይመስልም። እንደ ባሻ አስፋው አበበ ያሉት ደግሞ በኮርያና በኮንጎ በመዝመት ጥምር ጀግንነት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ጀግኖች መታወስ የሚያስችላቸው አሻራ መኖር እንዳለበት ያምናሉ። መዘንጋት የለባቸውም ባይ ናቸው።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ሻረው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያውያን በማይጨውም ሆነ አደዋ በየትኛውም የአገር ወረራ ዘመን እንደ አንድ ሰው ሆነው ተዋግተዋል፤ አዋግተዋል። ብዙ መስዕዋትነት ከፍለውም አገርን ነፃ በማድረግ አሁን ላለነው ትውልዶች አስረክበዋል። የአሁኑም ትውልድ ለራሱ ለአገሩም ሆነ ለዓለም ሕዝቦች ሰላም በየአውደ ውጊው በመሳተፍ ውድ ሕይወቱን ጨምሮ ብዙ መስዕዋትነት እየከፈለ ይገኛል።
ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ እያሰኘ ያለው ከቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን ተሞክሮ በመነሳት ነው። ጀግኖች አባቶች ከአገር አልፈው በኮርያና ኮንጎ አውደ ውጊዎች ተሳትፈዋል። በተለይ ከኮርያ ጦርነት መልስ በ1952 ዓ.ም ኮንጎ ለኢትዮጵያ ባደረገችው ተመሳሳይ የወታደራዊ ድጋፍ ጥሪ መሠረት ዳግመኛም ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ ዘምተው የተዋጉና በድል የተመለሱ ጀግኖች አሉ። እንዲሁም መስዕዋትነት ከፍለው እዚያው የቀሩም ይገኙበታል። ከነዚህ ጀግኖች ብዙዎቹና በሕይወት ያሉት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል ሆነው ሲያገለግሉ ነበሩ። በሕይወት የሌሉትም እንደ ማይጨውም ሆነ አደዋ በማህበሩ ይታወሳሉ። ይታሰባሉ።
ሆኖም ኮርያ ዘማቾች የራሳቸው ማህበር አላቸው። ማህበሩ የሚደገፉበትና የሚታወሱበት ነው። ማህበሩ ባለው አቅም ከመንግሥት በሚመደብለት አነስተኛ በጀት ድጎማ በመስጠት በምክር ቤት አባልነት እንዲመረጡ በማድረግ ሲደግፋቸው ቆይቷል። አሁንም በዚሁ መንገድ ውለታቸውን በማሰብ የሚደገፍበት አሠራር አለ። እኛም ሁሉም ጀግኖች የአገር ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካና የዓለም ባለውለታዎች ናቸውና መደገፍ ይገባቸዋል።
በተለይም የኮንጎ ዘማቾች የተዘነጉ ይመስላል። ስለዚህም የሀገር ባለውለታ የሆኑትን እነዚህ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ማስታወስ ቢቻል ማቋቋምና እንደ ባሻ አስፋው አበበ ያሉትን አልጋ ላይ የወደቁትን መታደግ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አይገባም።
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም