ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ እምብርትና የስበት ማዕከል ናት። አገሪቱ ሁሉንም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በማዕከልነት በማስተባበር አካባቢያዊ ጥምረት እንዲፈጠር የበኩሏን አስተዋጽኦ ማበርከት ከጀመረች ውላ አድራለች። በተለይም በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የዓባይን ግድብ በመገንባት በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እያደረገች ካለችው ጥረት ጎን ለጎን ሰሞኑን በዓለም ላይ ከነዳጅ ቀጥሎ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የስንዴ ምርት ወደ ወደ ጎረቤት አገራት ኤክስፖርት በማድረግ ቀጣናዊ ትስስሩ ተጨባጭ እንዲሆን አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሮሽ በሚፈጥሩ የጋራ በሆኑ የባቡር፣ የመንገድና የወደብ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት ዋና ምንጭ በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑም የአደባባይ ሀቅ ነው።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው አገሮች ዘላቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል ከማቅረብም በተጨማሪ፣ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ ጭምር ለቀጣናዊ ትስስሮሹ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑንም ብዙዎች በስኬት ያወሱታል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ቀጣናውን በማስተሳሰር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት መፍጠር ከቻሉ፣ ሰላምም ሆነ ዳቦ ችግር ለሆነበት ክፍለ አኅጉር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።
እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2019 የተጀመረውን የቀጣናው አገሮችን ‹‹Horn of Africa Initiative›› (የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር) ፕሮጀክትን በመተግበርም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው። በዓባይ ግድብ የኃይል አቅርቦትና በስንዴ ረገድ የታዩ አበረታች ለውጦችም ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በፊት የጀመረችው ታላቁ የዓባይ ግድብ ከ84 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ግድቡ ከወዲሁ ለጎረቤት አገራት ጭምር የኃይል ምንጭ በመሆን ምሥራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር ላይ ይገኛል። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የምሥራቅ አፍሪካ አገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የቀጣናውን አገራት በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ በር ይከፍታል።
እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ ኢትዮጵያ በግብርናው ረገድም ቀጣናዊ ትስስሩን የማጠናከር ሥራ በስኬታማነት በማከናወን ላይ ትገኛለች። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ስንዴ ምርት ነው። ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት ራሷን በመለወጥ ታሪክ ሠርታለች፤ ለቀጣናው አገራትም ኩራት ሆናለች።
በተያዘው ዓመት ኢትዮጵያ 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት ታመርታለች። ከዚህ ውስጥ 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ሲሆን 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ወደ ውጭ ተልኮ ዶላር የሚያስገኝ ነው። ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ካላቸው ስድስት አገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል። የረድኤትና ሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን ስንዴ በአገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ መሆናቸው ተነግሯል። በዚህም ኢትዮጵያ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደም ታገኝ ይገመታል።
ይህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር የጎረቤት አገራት ከአውሮፓ፤ ከአሜሪካና ካናዳ ደጅ ጠንተው የሚገዙትን ስንዴ ከደጃቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የምሥራቅ አፍሪካን አካባቢም ከግጭትና ሁከት ነፃ በማውጣት አገራቱን በልማት እንዲተሳሰሩ በር ይከፍታል።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ሚና በአግባቡ ለመወጣትም ነፃ የንግድ ቀጣና በድሬዳዋ መስርታለች። ይህ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ጎረቤት አገራት ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር ተግባር በውጤታማነት እየተወጣች የምትገኝ አገር ነች። በተለይም በኃይል አቅርቦት፤ በግብርና ምርት በተለይ ስንዴን ከራሷ አልፎ ወደ ጎረቤት አገራት መላክ መቻሏ ተጠቃሽ ያደርጋታል። በሌላም በኩል ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወተውን የድሬዳዋን ነፃ የንግድ ቀጣናን በማቋቋም ሚናዋን እየተወጣች ያለች አገር መሆኗን አስመስክራለች
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም