በሀገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ሲወስድ ይታያል:: ገበያን ለማረጋጋት መንግሥት ከወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ከሚገኙ እርምጃዎች መካከል የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው::
አምራችንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር የባዛርና የኤግዚቢሽን ገበያ ወሳኝ እንደመሆኑ የባዛርና የኤግዚቢሽን ገበያ በተለያየ ጊዜ ይዘጋጃል:: በገበያውም ሸማቹ ከአምራች አርሶ አደሮችና ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት ሰፊ ዕድል ይፈጠራል:: ይህም ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ያስችለዋል:: በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በተለያየ ጊዜ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች የሚዘጋጁት በዚሁ ምክንያት ነው::
እነዚህ ማኅበራት በተለይ በከተሞች ገበያን በማረጋጋት በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው:: በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን የምርት እጥረትና የሸቀጦች ዋጋ ንረት ለማረጋጋት ሚናቸው የጎላ ነው:: ማኅበራቱ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዲቻልና ገበያውን ለማረጋጋት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ::
በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከየካቲት 2 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደው ሁለተኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም ገበያን ለማረጋጋት ከተዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች አንዱ ነው:: ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየሙ ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአገር እድገት መሠረት ናቸው›› በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው::
እኛም በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ተገኝተን ገበያውን ቃኝተናል:: በሁለተኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ በርካታ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለገበያ ቀርበዋል:: ገበያው እንዳለፉት ተመሳሳይ ገበያዎች ሞቅ ደመቅ ያለ ባይሆንም፣ ሸማቹ በኤግዚቢሽን ባዛሩ ያገኘውን ምርት ከየዓይነቱ ሲሸምት አስተውለናል:: ሸማቹንና አምራቹን በማነጋገርም ሀሳባቸውን ተጋርተናል::
በኤግዚቢሽንና ባዛር ገበያው ሲሸምቱ ካገኘናቸው ሸማቾች መካከል ወይዘሮ መሠረት አሳዬ አንዷ ናቸው:: ከሃና ማርያም አካባቢ መምጣታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ መሠረት፣ እንዲህ ዓይነት ገበያ ለሸማቹ ማኅበረሰብ እጅግ በጣም ጥሩ እንደሆነና ገበያውን የማረጋጋት ዕድል እንደሚፈጥርም ይገልጻሉ::
እሳቸውም በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ የተለያየ ዓይነት ምርቶች ቀርበዋል ይላሉ:: ምርቶቹ ግን በሚፈለገው መጠን በስፋት አልገቡም ነው የሚሉት:: ያም ቢሆን ታዲያ እርሳቸው ከሚኖሩበት አካባቢና በአጠቃላይ ውጭ ካለው ገበያ አንጻር ገበያው የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመትም ችለዋል::
እሳቸው እንዳሉት አንድ ኪሎ ጤፍ በአካባቢያቸው ከ70 እስከ 75 ብር የሚሸጥ ሲሆን በኤግዚቢሽን ባዛሩ በ51 ብር መግዛት ችለዋል:: በዚህም በአንድ ኩንታል ከ800 እስከ 900 ብር ድረስ ቅናሽ ማግኘት እንደቻሉ ነው ያስረዱት::
ከጤፍ በተጨማሪ ገብስ እና የሽሮ እህል የሆነውን አተርና ሽንብራ ጭምር መግዛታቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ መሠረት፤ ዋጋውም ውጭ ካለው ቅናሽ መሆኑን ተናግረዋል:: ለአብነትም አንድ ኪሎ ገብስ ውጭ ባለው ገበያ ከ50 ብር በላይ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በኤግዚቢሽን ባዛሩ ግን አንድ ኪሎ ገብስ በ35 ብር መሸመት ችለዋል:: የሽሮ አተርን በተመለከተም ውጭ ላይ 100 ብር እና ከ100 ብር በላይ የሚሸጠውን እርሳቸው በ80 ብር መግዛት እንደቻሉ ነው የገለጹት::
ሸማቹ እንዲህ አይነት የገበያ አማራጮች ሲቀርቡለት ከየአካባቢው መጥቶ መግዛት ቢችል ተጠቃሚ ይሆናል ይላሉ:: ‹‹እንዲህ አይነት ገበያ በቀጣይም ተጠናክሮ ቢቀጥል ጥሩ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ መሠረት፤ ከተለያየ አካባቢ ለሚመጣው ሸማች ቦታው ርቀት ቢኖረውም ካለው የዋጋ ልዩነት አንጻር አዋጭ መሆኑን ይገልጻሉ:: ገበያን በማረጋጋትና የኑሮ ጫናውን በማቃለል በጎ ተጽዕኖ ያላቸው እንዲህ አይነት የገበያ አማራጮችን በማስፋት አምራቹ ከሸማቹ ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ መሸመት ቢችል መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል::
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታምራት መንገሻ እንዳሉት፤ ገበያው ብዙም አጥጋቢ አይደለም:: ለዚህም ምክንያቱ በኤግዚቢሽን ባዛሩ በስፋት የሚታዩት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተቋቋሙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሆናቸው ነው:: እነሱ ደግሞ በመኖሪያ አካባቢዎች በየቀበሌው የሚገኙ ናቸው:: ዋጋቸውም ተመሳሳይ ነው ይላሉ::
ከዚህ ቀደም እንዲህ ባለ ኤግዚቢሽንና ባዛር በሀገሪቷ ከሚገኙ የተለያዩ ክልሎች የሚመጡ አምራቾች ይሳተፉ እንደነበር በማስታወስ፤ ከጎጃም፣ ከደብረብርሃን፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከሌሎች አካባቢዎችም ይመጡ እንደነበር ያስታውሳሉ:: አሁን ግን ከየረርና በቾ ብቻ የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ገበያው እንደዚህ ቀደሙ ሞቅ ያለ አይደለም ብለዋል:: በዚህ የተነሳም ውጭ ካለው ገበያ ብዙም የተለየ ነገር እንዳላገኙም ነው የተናገሩት::
ከዚህ ቀደም በዚሁ ኤግዚቢሽንና ባዛር የከፋ ጫካ ቡና፣ የሐረርና ሌሎች ምርቶችም በቀጥታ ገበሬው ይዞ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታምራት፤ በዚሀ ገበያ ግን ብዙም እንዳልተደሰቱ ተናግረዋል:: አምስት ሊትር ዘይት በ880 ብር እንደገዙና በአካባቢያቸው በሚገኝ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆችም በ880 ብር አምስት ሊትር ዘይት እንደሚሸጥ ተናግረዋል::
አቶ ታምራት በርካታ ምርቶች ከየክልሉ እንዳልመጡ ጠቅሰው፣ በጤፍ ምርት አቅርቦትና ዋጋ ላይ ግን የተሻለ ነገር እንዳለ ነው የተናገሩት:: አንድ ኪሎ ጤፍ ውጭ ላይ እስከ 70 ብር እየተሸጠ ባለበት በዚህ ወቅት በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከ51 ብር እስከ 57 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም ገበያውን ማረጋጋት እንደሚችል በመግለጽ የወይዘሮ መሠረት ሃሳብን ደግፈው ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ከነጋዴው በተሻለ ዋጋ የሚያቀርቡ ቢሆንም እንዲህ አይነት ገበያ ላይ አምራቾች ከክልሎች መምጣት እንደነበረባቸው ያመለክታሉ:: ከዚህ ቀደም የዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመታት በርካታ አምራች አርሶ አደሮች ከየክልሎቹ ይመጡ እንደነበርም አስታውሰው፣ አርሶ አደሮቹ በዚህ ላይ መጥተው ቢሆን በተሻለ መጠን እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ይቻል እንደነበር ነው ያስረዱት::
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የግብርና ምርቶችን ይዘው ከቀረቡት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች መካከል የደቡብ ክልል መሊቅ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን እንዱ ነው:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው የሁለተኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ መገኘታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የዩኒየኑ የግብይት ባለሙያ አቶ ዲንሰፋ ሽኩር ይናገራሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒየኑ የተለያዩ ጥራጥሬዎችንና የእህል ምርቶችን ይዞ መቅረቡን ገልጸው፤ ለአብነትም በቆሎ፣ ባቄላ፣ አተር ገብስና የገብስ ቅንጬ እንዲሁም በቆሎና የበቆሎ ቅንጬ ለገበያ ማቅረቡን ያብራራሉ:: ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ከማቅረብ ባለፈ እንዲህ ባሉ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች መሳተፍ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል:: ለአብነትም ዩኒየናቸው ከተለያዩ ዩኒየኖች እና ሸማቾች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል::
ወደ ገበያው ይዞ የቀረባቸውን ምርቶችም በስፋት መሸጥና እነሱ ካሉበት ቦታ ድረስ ሄደው ሊገዙ የሚችሉ የተለያዩ ተቋማትን ማግኘት እንደቻሉና የገበያ ትስስር የመፍጠር ዕድል እንዳገኙም ተናግረዋል:: አምራቾች እርስ በእርስ የመተዋወቅ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ዲንሰፋ፤ የትኛው ምርት ማን ጋ እንዳለና እንደሌለ የመለየት ሰፊ ሥራ የተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል::
እንዲህ ዓይነት ኤግዚቢሽንና ባዛር ገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነቱን ማቃለል ዋንኛ ዓላማው ነው ያሉት አቶ ዲንሰፋ፤ ገበያን ለማረጋጋት ከዚህ የተሻለ አማራጭ እንደሌለም ነው የሚገልጹት:: ይህን አይነቱ ባዛርና ኤግዚቢሽን ዋጋና ገበያን ማረጋጋት ዓላማ አድርጎ እንደሚዘጋጅ ጠቅሰው፣ በቀረበው ምርት ሸማቹ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይገልጻሉ:: ለአንድና ለሁለት ወራት ቢሆንም ለሸማቹ አስቤዛ መሸመት የሚችልበትን ዕድል ለሸማቹ ፈጥሮለታል ይላሉ:: በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ አምራቹ በስፋት ባይገባም፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መገኘታቸውን ግን ገልጸዋል::
ዩኒየኑ 192 አባል ማኅበራትና 105 ሺ የተናጠል አባል አርሶ አደሮች ያሉትና ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዲንሰፋ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ያቀርባል ብለዋል:: በዚህም ጥራት ያላቸውን የግብርና ምርቶች ተቀብሎ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ያቀርባል:: በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለማምረት በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራም ይናገራሉ:: በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአርሶ አደሩ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሠራል ብለዋል::
ሌላው በኤግዚቢሽን ባዛር ያገኘነው የኦሮሚያ የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌዴሬሽን ነው:: ፌዴሬሽኑ የፋብሪካ ውጤት ምርቶችን ይዞ ነው የቀረበው:: የፌዴሬሽኑ የገበያ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ፈይው እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ የግብርና እንዲሁም የፋብሪካ ውጤቶችን ያመርታል:: በአሁኑ ወቅትም የፋብሪካ ምርቶች የሆኑ የበቆሎ ዱቄት፣ የበቆሎ ቅንጬ፣ ለከብቶች መኖ የሚሆን የበቆሎ ተረፈ ምርት ይዞ ቀርቧል:: ምርቶቹም በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሱቆች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ በእሁድ ገበያ ላይም ተሳታፊ በመሆን ተደራሽ ናቸው::
ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ናሙናዎችን ይዘው መቅረባቸውን ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ ሽንብራ፣ ማሾ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ ነጭ ቦሎቄና ዥንጉርጉር ቦለቄን ለማሳያነት ይዘው መቅረባቸውን ነው የተናገሩት:: እነዚህ ምርቶች ከአርሶ አደሩ የሚሰበሰቡና ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ እንደሆኑም ተናግረዋል::
አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችል የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉለታል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ እገዛ የሚደረግላቸው መሆኑን አመላክተዋል:: ለአብነትም ፀረ-ተባይ ምርቶችን ከውጭ በማስመጣት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ይከፋፈላል:: ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ቁሳቁስን ከውጭ በማስመጣት አባል ለሆኑ አርሶ አደር ቤተሰቦች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል::
በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፤ ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማጠናከር ኅብረተሰብን መደገፍ ነው›› በማለት የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በሀገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል:: በተለይም ማኅበራቱ ሰው ሠራሽ የሆነውን የኑሮ ውድነት በማቃለል የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ተናግረዋል::
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ከ170 በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መገኘታቸውንና ከ10 ሺ በላይ ኩንታል የሰብል እህል መቅረቡን መረጃዎች ያሳያሉ:: ማኅበራቱ አምራቾችን እና ሸማቾችን በማገናኘት ካላቸው የላቀ ሚና ባሻገር የኑሮ ጫናውን ከማቃለል አንጻር ጉልህ ድርሻ አላቸውም ተብሏል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም