የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቱ ጉዳይ የሚመክርበት ጉባኤ በየአመቱ በፈረንጆቹ አዲስ አመት የመጀመሪያ ወራት በአዲስ አበባ ይካሄዳል::በዚህ ጉባኤ የአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳይ አጀንዳ በማድረግ መሪዎቹ ይወያያሉ::ውሳኔም ያሳልፋሉ::የኅብረቱ አባል ሃገራትም እንደየሃገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ውሳኔዎቹን ለመተግበር ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ኋላም ለአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ከፍተኛውን ሚና መጫወቷ በታሪክ ይታወቃል::አዲስ አበባም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ናት::ሃገራችን ከ50 ዓመታት በላይ እድሜ ላስቆጠረው አህጉራዊ ተቋም እና ለአፍሪካዊያን በተለያየ ስርዓተ መንግስት የማይለዋወጥ ድጋፍ አድርጋለች፤ አሁንም እያደረገች ትገኛለች፡፡ወደፊትም ታደርጋለች፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብም በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲካሄድ በኢትዮጵያዊ ስነምግባርና መስተንግዶ ባረፉባቸው ሆቴሎች ፣ በሚዘዋወሩባቸው የገበያ መደብሮችና መንገዶች በአክብሮት አስተናግዷቸዋል፡፡አሁንም ያስተናግዳቸዋል፡፡
ከመጪው የካቲት 10 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም 36ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል::ከመሪዎቹ ጉባኤ ቀደም ብሎ ደግሞ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2015 ዓ.ም 42ኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ይካሄዳል::እነዚህ ጉባኤዎች የተሳኩ እንዲሆኑ መንግስት እንዲሁም የፀጥታ ተቋማት እና ሆቴሎች በቂ ዝግጅት አድርገው እየተጠባበቁ ነው፡፡
የከተማዋን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እና ለእንግዶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲቻል የፀጥታ መዋቅሩ በቂ ዝግጅት አድርጓል::የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ያደረገውን የአጀብና የፀጥታ ሥራዎች የተግባር ልምምድ በስኬት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባዔዎችን በሰላም እንዲጠናቀቁ ሥራውን የሚመጥን ተግባራዊ ልምምድ አድርጓል::መጪውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ምክንያት በማድረግም የአጀብ እና የፀጥታ ስራዎችን መሰረት ያደረገ ልምምድ ያደረገው የእንግዶች ደህንነት እንዲጠበቅና አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ በከተማዋ እንዲኖር ለማስቻል ነው::የከተማዋ ነዋሪዎችም ከዚህ በፊት በኅብረቱ ጉባኤ ያደርጉት እንደነበረው ከፀጥታ አካላት ጋር በመናበብ የተለመደውን ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በመዲናይቱ የሚደረጉ አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ጉባኤዎችና ሁነቶች በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀሙ ሁሌም ተባባሪ ነው::የራሱ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ኅብረት የሚያካሂዳቸው ጉባኤዎች ደግሞ ይበልጥ በእኔነት ስሜት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በሰላም እንዲጠናቀቁ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በመዲናይቱ የሚካሄዱ ጉባኤዎች ለከተማዋ ገቢ ያስገኛሉ::ወደ ስብሰባ የሚመጡ ሰዎች በሚያርፉባቸው ሆቴሎች አካባቢ ብቻ ሳይሆን ታላላቅ የገበያ መደብሮች ግብይት ያካሂዳሉ::በዚህ ወቅት ሕዝቡ በተለይ ደግሞ አሽከርካሪዎች ለእንግዶች ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት በተግባር ማሳየት ይገባቸዋል፡፡
በከተማዋ ማንኛውም ዓይነት የፀጥታ ችግር ካጋጠመ የሃገር ገፅታ ነው የሚበላሸው፤ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የገነቡት የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ነው አደጋ ላይ የሚወድቀው፡፡ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ከተራ የስርቆት ወንጀል ጀምሮ አንድም የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥም ሕዝቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባባሪ ሆኖ መስራት አለበት፡፡
በከተማዋ ያሉ አሽከርካሪዎች ሆነ ተጠቃሚዎች ከፀጥታ አካላት የሚሰጣቸውን መመሪያና ተለዋጭ መንገድ በመጠቀም የትራፊክ ፍሰቱን ለእንግዶች የተመቸ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::ታጋሽና አስተዋይ ሆነው ለሃገራቸው የመልካም ስም አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል፡፡
እንግዶች በሚያርፉባቸው ሆቴሎችና መዝናኛ ቦታዎች፤ የገበያ ቦታዎች፣ ፓርኮችና ሙዚየሞች ለእንግዶች ምቾት መስራት አለባቸው::በእነዚህ ቦታዎች እንግዶቹ የሚፈልጓቸውን ከማቅረብ ጀምሮ በቋንቋ አለመግባባት ክፍተት እንዳይኖር የአፍሪካ ሃገራት በሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች በማስተናገድ ጥሩ መግባባት በመፍጠር ገቢም መልካም ገፅታም መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ 36ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ መላው የከተማዋ ህዝብ ከፀጥታ ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል እና ከፀጥታ ሰራተኞች የሚሰጡትን መመሪያዎችና ትእዛዞች መተግበር አለበት::ይህን መመሪያና ትእዛዝ መፈፀም ለከተማዋ ሕዝብ አዲስ አይደለም::ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ያደርገው የነበረ እና አፍሪካዊያንም የሚያውቁት ስለሆነ ይህንን አጠናክሮ በዚህ ጉባኤም ማሳየት ይቻላል፤ይገባልም!
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም