ኢትዮጵያ የብዙ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች እንዲሁም የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ የሚታወቅ ሐቅ ነው። ብዙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ የሀገሪቱ ቅርሶች መኖራቸውም የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የባሕል እና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግበው ይገኛሉ። ይህም በዓለም መድረክ ሀገሪቱን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተመራጭ ሊያደርጋት እንደሚችል አያጠያይቅም። ነገር ግን ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታገኘው ገቢ ልታገኝ ትችል ከነበረው እጅግ ጥቂቱን መሆኑን የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጭራሽ ዘርፉ በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅተኛ አፈፃፀም እያሳየ መምጣቱ እየተዘገበ ይገኛል። ይህንኑ ዝቅተኛ አፈፃፀም በቅርቡ የኢትዮጵያ ፌደራለዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ ይፋ አድርጎል። ይህ ለምን ሆነ? ስንል ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች የሚሉት አላቸው።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ እንደሚናገሩት፤ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ከሚባሉት ከግብርና እና ኢንዱስትሪ ቀጥሎ የሚመጣው የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፍ ዋነኛው ነው። ሦስቱ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ዋናውን ድርሻ እንዲይዙ የሚፈለግ ሲሆን፤ አገልግሎት ደግሞ በዋናነት ቱሪዝምን ያካትታል። ከአገልግሎት ዘርፍ በላይ እንዲመራ የሚፈለገው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው።
ነገር ግን የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር ደግሞ የአገልግሎት ዘርፉ በተለይም ቱሪዝም ማደግ እንዳለበት አያጠያይቅም ይላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላላ ምርት ትልቁን ድርሻ የያዘው የአገልግሎት ዘርፉ ነው የሚሉት ባለሙያው ቀጥሎ ግብርና፣ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ ኢንዱስትሪ ሲሉ ያስረዳሉ። በእርግጥም አገልግሎት ውስጥ ካሉት ከዋንኞቹ አንዱ ቱሪዝም ነው። ይህ ዘርፍ ራሱን የቻለ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኖሮት የሚመራ ነው ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ ይናገራሉ።
ቱሪዝምን የሀገር ውስጥ እና የውጭ በሚል በሁለት መክፈል ይቻላል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው ከውጭ የሚመጣው ቱሪዝም ነው ይላሉ። አሁን የቱሪዝም ዘርፉ ለምን ወደቀ? ከተባለ ቱሪዝም በዋንኝነት የሚያድገው ምንም እንኳ ሊጎበኝ የሚችል ሰፊ ሃብት ቢኖርም የሀገር ውስጥ ደህንነት እና መረጋጋት ካልተረጋገጠ ዘርፉ ስኬት ማስመዝገብ አይችልም ሲሉ ይገልጻሉ። ስለዚህ መረጋጋት በሀገሪቱ ውስጥ የማይኖር ከሆነ በምንም ዓይነት ተዓምር ከቱሪዝም የሚገኘው ገንዘብ ከፍ ሊል እንደማይችል በመጠቆም፤ ሰላም ከቱሪዝም የማይለይ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሌላው በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስቶች ወይም የሰው የመጎብኘት ፍላጎት የሚኖረው የዓለም ኢኮኖሚ በራሱ የተረጋጋ ሲሆን ነው። የሚሉት አቶ ወሰንሰገድ የእርስ በእርስ ጦርነቶች እያሉ እና ሀገራት ከሀገራት ጋር እየተጋጩ ከሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ስለሚኖር ቱሪዝም የሚጎዳበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ያብራራሉ። በተለምዶ ለመዝናናት ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች ያላቸው የመክፈል አቅም የተዳከመ እየሆነ ከመጣ እና የውጭ የተለያዩ ምክንያቶች እንደ ኮቪድ ያሉ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ከፍ እያሉ በሚመጡበት ጊዜ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር የሚመጡ የቱሪስቶች ቁጥሩ በሚታይ መልኩ መቀነሱ የሚያስገርም አለመሆኑን ያስረዳሉ ።
አቶ ወሰንሰገድ እንደሚናገሩት፤ቱሪዝም ላይ ምንም ያህል የሚጎበኝ ሰዎችን ሁሉ ሊስብ የሚችል ሥራ ቢሠራም የሚጎበኛው ሰው ከሌላ ሄዶ ሄዶ ገቢ አይኖረውም። ፣ ስለዚህ ቱሪስት ወደ ሀገር ውስጥ እንደይመጣ ከላይ የተጠቀሱ ዓለም አቀፍ ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ዋናው ግን ዓለም አቀፍ ከሆኑ ጉዳዮች በላይ በሀገር ውስጥ ያለው ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ነው።
ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተስተዋሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ለዘርፉ ማዳከም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ጎብኚው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እንዲሁም በአጠቃላይ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚንቀሳቀስበት ወቅት እና ጊዜ ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ የሚያስብ ከሆነ ተንቀሳቅሶ የመጎብኘት ፍላጎት አይኖርም። ስለዚህ ክልሎችም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምርላቸው ከፈለጉ በክልላቸው ውስጥ ሰላምን ማስከበር መቻል እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የሰላም መረጋገጥ ለቱሪዝም ዘርፍ ለነገ የማይባል ሥራ ነው የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤ ከዚህ ውጪ ቱሪስቶች ሲመጡ የሚጠቀሟቸው ሆቴሎች፣ የሎጀስቲክ አገልግሎት፣ የመኪና አቅርቦት፣ የአየር ትራንስፖርት እንዲሁም በቱር እና ትራቭል ወይም በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚሰጡዋቸው አገልግሎቶችን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል። እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ እና ቶሎ ቶሎ የሚቀያይሩ ባንኮች መኖራቸውም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።
አቶ ወሰንሰገድ በማብራሪያቸው፣በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ እና መንግሥት ተናበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በመግለፅ በዋናነት ግን የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ዋነኛው የቤት ሥራ እንደሆነ አንስተዋል።
የቱሪዝም ባለሙያው ዶክተር አያሌው ሲሳይ በበኩላቸው፤ ለኢንዱስትሪው መዳከም የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ ያብራራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መልኩ የተከሰቱ በሽታዎች እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው ጦርነት ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል ካሉ በኋላ፤ ተዘግቶ እንዲቆይም አድርጎታል ይላሉ። በተጨማሪነት ቱሪዝም እና ሰላም አብረው የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች በመሆናቸው፤ ሰላምም ወሳኝ እንደሆነ በመግለፅ፤ ከምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ እንዳላቸው ያስረዳሉ።
የቱሪዝም ባለሙያው ዶክተር አያሌው፤ ሀገሪቱ የሚጎበኝ ሃብት አላት፤ መስሕብ አላት፤ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቱሪስት ለመሳብ ዝግጁ የሆኑ እና ቱሪስቱም የሚወዳቸው መስሕቦች አሉ። ሀገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን ቱሪስቶች ይወዱዋቸዋል። ነገር ግን በተለይ በውጭ ቱሪስቶች ሃብቶቹ እንዳይጎበኙ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ሆኖዋል። ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች የሚወዱትን መስሕብ፣ የሚወዱትን ሕዝብ፣ የሚወዱትን ቅርሶች እንዳይጎበኙ አድርጓቸዋል። ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ተዘግቷል ይላሉ።
ከዛ ውጭ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ለቱሪስቶች እንዴት ብለው ሀገራትን መጎብኘት እንዳለባቸው፤ ከጤናቸው አኳያ የተለያዩ መመሪያዎችን ስለሰጧቸው፤ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶቹ ስለሁሉም ነገር ያውቃሉ። በሀገር ደረጃ ደግሞ ምንም እንኳ ኮቪዱ እየተቃለለ ቢመጣም አሁንም ለጥንቃቄ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማድረግ የግድ ነው። በሌላ በኩል የተጠናከረ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ቅስቀሳ ያስፈልጋል፤ ሰላም ተፈጥሯል፤ ሀገሪቱን መጎብኘት ትችላላችሁ መባል አለበት። ራሱን ችሎ የተቋቋመ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የክልል የቱሪዝም ቢሮዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥረት ማድረግ እና ማስታወቂያዎችን መሥራት አለባቸው ይላሉ።
‹‹ይህ ማለት አሁን ዝም ብለው ተቀምጠዋል ማለት አይደለም›› የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያው ዶክተር አያሌው፤ አዲስ ስትራቴጂ ነድፈው ዘርፉ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ሁሉ ቀይሰው ወደ ዓለም የቱሪዝም ገበያ መሄድ እና አጠናክረው መሥራት አለባቸው ለማለት ነው። ከድሮው በበለጠ ሥራዬ ብለው በኢትዮጵያ ሰላም እንደተፈጠረ ማስተዋወቅ አለባቸው ብለዋል።
‹‹ዛሬ ብትመጡ ምንም ዓይነት ችግር አይገጥማችሁም። ›› የሚለውን በሙሉ በገበያው ላይ በተጠናከረ መልኩ መሥራት አለባቸው ሲባል፤ የቱሪዝም ቤተሰብ የሚባሉት ሌሎችም ሆቴሎች ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ወዘተ ሁሉ ግንባር ፈጥረው ወደ ዓለም ቱሪዝም ገበያ መዝመት እና በተዓማኒነት ቱሪስቱን የመቀስቀስ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።
ሰላምን ማረጋጋጥ ከተቻለ የኮቪዱ ሁኔታ እየተቃለለ ከሄደ፣ ሀገሪቱን ቱሪስቶች የሚወዷት በመሆኑ ይመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ይገልፃሉ። ዶክተር አያሌው በተጨማሪ ሲናገሩ፤ በየአካባቢው ከዚህም ከዛም ትንኮሳ ወይም ሀገሪቱ ሰለላሟን እንዳታገኝ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማስተካከል መንግሥት ኃላፊነቱን ከተወጣ እና ሕዝቡም ተገቢውን ሚና ከተጫወተ ቱሪዝም የዚህች ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ለቱሪዝም ምቹ የሆኑ ግብዓቶች እየተገኙ ለዓለም አቀፍ ቱሪስት የሚሆኑ ለአብነት በክልሎች ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ኮይሻ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥም የወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እነኚህ ሁሉ ተጨማሪ ለቱሪስቱ የተዘጋጁ ስለሆኑ እነኚህንም ጨምሮ የነበሩትንም አጠናክሮ ማሠራት ከተቸለ ለወደፊቱ ኢትዮጵያ የቱሪስቶች መናኸሪያ ትሆናለች ብለው እንደሚያምኑም አብራርተዋል።
የወደፊቱን በተመለከተም የሚናገሩት አቶ ወሰንሰገድ፤ በዋናነት መንግሥት ሰላምን ከማስጠበቅ አንፃር ትክክለኛ ሥራ የማይሠራ ከሆነ የቱሪዝም ዘርፉ ብቻ ሳይሆን፤ ማንኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ በትክክል ውጤታማ መሆን እንደማይችልም ተናግረዋል። ስለዚህ መንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ሁሉም ነገር ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መቀየር እንዲችል መሥራት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም የቱሪዝም ሚኒስቴር ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል ያሉት የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ፤ የቱሪዝም አይነቶች በጣም ብዙ ስለሆኑ ኢትዮጵያውያንም የራሳቸውን ሀገር የመጎብኘት ልምምድ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተዋል። በተለይ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅት ሠራተኞች በዓመት አንድ ጊዜ የጉብኝት ፕሮግራም እንዲኖራቸው በማድረግ የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች እንዲጎበኙ ማበረታታት እንደሚገባ ያነሳሉ። ይህም የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም በምሳሌነት አንስተዋል።
ባለሙያዎቹ እንደገለፁት፤ በቀጣይ በተለይም መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ኃላፊነቱን በሚገባ ከተወጣ እና ሰላም መስፈኑን በተመለከተ በሰፊው የማስተዋወቅ ሥራ ከተሠራ የቱሪዝም ሃብት ሰፊ በመሆኑ ትልቅ ውጤት መምጣቱም የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም