የዲጂታል ዘመኑን የዋጁ የዓለም ሀገራት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተራቀቀ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህም ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመራመድ የዲጂታሉን ዓለም መቀላቀል አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል። በዲጂታል አብዮት ወደ ኋላ የቀሩ ሀገራት በእዚህ ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል፤ እነዚህ ሀገሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂው ወደፊት ከገሰገሱ የዓለም ሀገራት ጋር ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ መቀየስም ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችላትን ዲጂታል ኢኮኖሚ በመከተል ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ››ን አጽድቃ ወደ ሥራ ገብታለች። በሀገሪቱ ቀደም ሲል የዲጂታል ዘርፉ ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ ብዙ አልተሰራበትም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለዲጂታል ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የቴክኖሎጂ መሠረት ለመጣል የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን እንደ አበረታች ጀምር መውሰድ ይቻላል።
በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› የተሰኘ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ ቢዝነሶችና ባለሙያዎች የሚበረታቱበት መርሐ ግብር ማስጀመሩም የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ አድርጎ መውሰድም ይቻላል።
ፕሮግራሙን አስመልክተው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዳሉት፤ ይህ ፕሮግራም ጀማሪ ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረጉ ቢዝነሶችና ባለሙያዎች የሚበረታቱበት ሲሆን፤ በጀማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሰማሩ ተቋማትን የሚያበረታታና የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት የራሱን ሚና ይጫወታል። ፕሮግራሙ ለ250 ጀማሪ ኩባንያዎች ዕድል ይሰጣል።
የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ በንግድ ስራ የተሰማሩ ናቸው። ከሚያካሂዱት የንግድ ስራ ጎን ለጎን ዘመናዊ ንግድን ማዘመን የሚችሉበትን መንገድ ከመወጠን ባለፈ ጥናቶችን አድርገዋል፤ ከዚያም አሸዋ ቴክኖሎጂ የሚል ኩባንያ በማቋቋም በኦንላይን ግብይት ውስጥ ገብተው እየሰሩ ይገኛሉ።
አቶ ዳንኤል በቀለ እንደሚሉት፤ ‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› የተሰኘ ፕሮግራም መጀመሩ የኢንኩቤሽን ማዕከል መፍጠር ወይም የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች በስልጠና፣ በትምህርት እና በፋይናንስ በማበረታታት በዘርፉ ያላቸውን ብዙ ልምድ እንዲጠቀሙበት የሚያደርግ ነው። ይህም ወደ መሬት የሚወርድ ሥራ እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። የፈጠራ ባለሙያዎች ሀሳባቸው እውን እንዲሆንም ያግዛል። ለሀገርም ሆነ የፈጠራ ሀሳብ ላላቸው ባለራዕዮች ትልቅ እድል የሚሰጥና ከፍተኛ ፋይዳ ያለውም ነው።
‹‹ብዙ ሀሳብ እና ራዕይ ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ‹‹የፈጠራ ሀሳቦችን በማበረታታት ሰዎች ከህልማቸው ጋር እንዲገናኙ ወይም ሃሳባቸው እንዲሳካላቸው በፋይናንስም ሆነ በስልጠና ድጋፍ በማድረግ ማገዝ ይገባል። ›› ሲሉ ይገልጻሉ። በሀገሪቱ የፈጠራ ሀሳቦች በማበረታታት ላይ ብዙ እንዳልተሰራም ተናግረው፣ ተደራሽነታቸው ሰፊ ባይሆንም እንደ ‹‹ብሉሙን›› አይነት ጥቂት ተቋማት ኢንኩቬሽን ማዕከልን በመፍጠር የፈጠራ ሀሳቦችን በማበረታታት ረገድ እየሰሩበት እንደሚገኙም ነው የጠቀሱት።
‹‹ከአሜሪካ እና ህንድ ጋር ሲነጻጸር በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የዲጂታል ዘርፉ እንቅስቃሴ ደካማ ነው። ህንድን ብንመለከት በዲጂታል ዘርፉ ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ በቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝላት ነው። ›› ያሉት አቶ ዳንኤል፣ የአሜሪካውን አፕልን የመሳሰሉ በአለም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያመጡ ተቋማት ብዙ ትሪሊየን ዶላር በዚህ ቴክኖሎጂ እንደሚያፉሱም ይጠቅሳሉ። ቻይናም እንዲሁ 95 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆኑን ያብራራሉ።
ይህ የሚያመላክተው የየሀገራቱ መንግሥታት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው በደንብ መሥራት መቻላቸውን ጠቅሰው፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ መንግሥት ለዘርፉ ሲሰጥ የነበረው ትኩረት በጣም አናሳ መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹እኛ እንደ ሀገር የምንነቃው ሌሎች የዓለም ሀገራት ጥለው ብዙ ርቀት ከተጓዙ በኋላ ነው። ለአብነት የግብርናውን ዘርፍ ብንመለከት በመንግሥት ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ ያለው ገና አሁን ነው። ዓለም አሁን ያለችበት ሁኔታና እኛ ያለንበት ሁኔታ ሲነጻጸር ብዙ ወደኋላ የቀረንበት ሁኔታ ስለመኖሩ መገንዘብ እንችላለን›› ይላሉ።
አቶ ዳንኤል እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉ አዲስና እንግዳ ከመሆኑ አንጻር ወደ ዘርፉ ሊሰማራ ያሰበ ሥራ ፈጣሪ፣ ንግድ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ግብር መክፈል ድረስ ብዙ ወጣ ውረድ ያለው ሂደት ለማለፍ ሊገደድ ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ የሀገሪቱ ህዝብ ጊዜውን የሚያውለውም ሆነ ገንዘቡን ወጪ የሚያደርገው የውጪ ሀገር ሶፍት ዌር ወይም ቴክኖሎጂ በመጠቀም ላይ ነው። በሀገር ውስጥ በልጽገው የሀገርን ችግር የሚፈቱና የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያገለግሉ ምርቶች ለገበያ እንዲወጡ ለማድረግ መንግሥት በትኩረት መሥራት አለበት።
‹‹ለአብነት በዲጂታል ዘርፍ የሚሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎች ለተወሰኑ ዓመታት ከታክስ ውጪ ቢደረጉ ይበረታታሉ፤ ጎልተው የሚታዩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። የፖሊሲ እገዛ ቢደረግ፤ ይበልጥ የሚሳለጥበት ሁኔታ በመፍጠር የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል›› የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ‹‹አሁን እየወጡ ባሉ ፖሊሲዎች እኛንም በማሳተፍ ለፖሊሲ ግብዓት የሆኑ መረጃዎችን በመውሰድ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል የማድረግ ሁኔታ መኖሩ የሚያበረታታና ትልቅ ለውጥ ያመጣል›› ብለዋል።
ቴክኖሎጂ የሕዝብን ሕይወት ቀላልና ምቹ፣ ዘመናዊና የተሻለ እንዲሆን እንደሚረዳ ጠቁመው፣ ስርአተ ትምህርት ተቀርጾለት በትምህርት መሰጠት አለበት ብለው እንደሚያምኑም ያመለክታሉ። ወደ ዘርፉ የሚገባ ሰው ልምዱን ሲያወቀውና ጥቅሙን ሲረዳ ነው የተሻለ ለውጥ ማምጣት የሚችለው ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ይህ ሲሆን ባለሀብቱም ጉዳዩን በትኩረት መመልከት እንደሚችል ነው ያብራሩት።
አቶ ዳንኤል እንዳሉት፤ ብዙ ኩባንያዎች የተቋቋሙት በኢንኩቤሽን ማዕከል ነው። አንድ ሀሳብ ያለው አንድ ሥራ ፈጣሪ ህልም ይዞ ይመጣል። ይህ ህልም በደንብ ይገመገማል፤ችግር ካለበት እዚያው ጋ ብዙ ሳይለፋበት ገንዘብ፣ ጊዜ እና ጉልበት ሳይወጣበት ይቀራል። ቀጣይነት ያለውና ዘላቂ ከሆነ ደግሞ በደንብ መውጣት ይችላል። በዚህ ሂደት የጠሩ ሀሳቦችና ቢዝነሶች የተሻለ ተዕጽኖ በመፍጠር ለማህበረሰቡ የሚደርሱበት እድል ይፈጠራል።
እነዚህ ሥራዎች አንደኛ እንደ ቢዝነስ ብዙ ገንዘብ የሚያመጡ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ እንደ ሀገር ከሥራ ፈጠራ አንጻር የተሻለ እድል በመፍጠር ሰፊ የሥራ እድል እንዲኖር ያደርጋሉ። በአጠቃላይ በዲጂታል ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ያስችላሉ።
‹‹ሁሉም ነገር የጀመረው ከሀሳብ ነው፤ ዓለምን የቀየራት ፈጠራ /ኢኖቬሽን/ ነው። አለም አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ለመድረሷ መነሻው ሀሳብ ነው። ስለዚህ ሀሳብ በደንብ መደገፍና መደነቅም አለበት›› ይላሉ። ምክንያቱም ለአዳዲስ ነገሮች ትኩረት አልሰጠንም ማለት በድሮ በሬ በማረስ የመቀጠል ህልም ይዘን የምንጓዝበት ሁኔታ መኖሩን ነው የሚያሳየው። አዲስ ሀሳብ እንደሀገር ኢኮኖሚ የሚቀይርልንና የተሻለ ተዕጽኖ እንድንፈጥር የሚረዳን በመሆኑ መንግሥት የተጀመሩ ሥራዎችን ቶሎ ሥራ ላይ ማዋል አለበት›› ሲሉም ያብራራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ግንዛቤ ላይ ብዙ ክፍተት ያለ በመሆኑ በደንብ ቢሰራ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በሀገሪቱ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። በዚህ እየተጠቀሙ ያሉት ውጪ ያሉ ኩባንያዎች ናቸው። በሀገር ውስጥ የበለጸጉት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ መንግሥትና ሥራ ፈጣሪው በጋራ የሚሰሩበት የተሻለ የሚያሻግር ነገር መፍጠር የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ሀገር የሚገነባው በጋራ ነውና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ግንኙነት በጣም ጠንካራ መሆን አለበት።
‹‹እኔ ወደ ዘርፉ ስቀላቀል ያጠራቀምኩትን ብር ይዤ ነው የተነሳሁት። ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገባሁት ለማስፋፊያ ነው›› የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ እንደ ሥራ ፈጣሪ ወደ ሥራ ሲገቡ ወደ ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሟቸውም ያስታውሳሉ። ሥራ ፈጣሪዎች እንደዚህ አይነት ኢንኩቤሽን ማዕከል ላይ ተቀላቀለው የገንዘብ ሆነ የእውቀት ድጋፍ አድርገው ህልምና ዓላማ ተጋርተው ሀሳባቸው ወደ ሕዝቡ እንዲመጣ እገዛ ማግኘታቸው ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ሸክም በመቀነስ የተሻለ ደረጃ የሚደርሱበት ሁኔታ የሚፈጥርና ከውጭ ሀገራት ጋርም የልምድ ልውውጥ ስለሚኖር የተሻለ እድል እንዳለው ይገልጻሉ።
አቶ መርዕድ በቀለ የአይ ኢ ኔትዎርክ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተሰማርተው ወደ ሥራ ከገቡ 14 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ለተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ትላልቅ የዳታ ማዕከላትን ከመገንባት ጀምሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትን ያቋቋሙ ሲሆን አገልግሎቱን የሚሰጡትም አገር በቀል በሆኑ ባለሙያዎች ነው። አቶ መርዕድ የፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታት ለኛ ሀገር አዲስ ነው ይላሉ።
በሌላው ዓለም በተለይ በፋይናንስ የሚረዳና እንዴት መሥራት እንዳለባቸው የሚያግዙ ብዙ አሠራሮች እንዳሉም ይናገራሉ። ‹‹የፈጠራ ሀሳብ ይዘው ለሚመጡ ባለሙያዎች ገንዘብ ይሰጣቸዋል። ያንን ሀሳብ እንዴት አድርገው ወደ መሬት በማወረድ ውጤት እንደሚያመጡ ደግሞ የማኔጅመንት፣ የማርኬቲንግ፣ አሠራሮችን የሚመለከቱ የሙያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ሲሉ ገልጸው፣ ይሄ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ መሆኑን ይገልጻሉ።
አሁን ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ፕሮግራም መጀመሩ በጣም የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶለት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም አቶ መርዕድ ይጠቁማሉ። አንድ ፈጠራ ውጤት እስከሚያመጣ ድረስ ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም አስገንዝበው፣ ልክ እንደ ኢትዮቴሌኮም ሌሎች ድርጅቶችም የፈጠራ ሀሳቦችን ማገዝ ቢችሉ ጥሩ ነው ይላሉ። ብዙ ሀሳብ ያላቸው፣ ብዙ ችግር መፍታት የሚችሉ ሰዎች ሀሳባቸው ከግብ ሳይደርስ ተወሰነው የሚቀመጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ እነዚህን አካላት በማገዝ ለሀገር ከፍተኛ ሚና መወጣት ይገባል ብለዋል።
ዘመኑ የዲጂታል መሆኑን በመጥቀስ፣ ብዙ ፈጠራዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አቶ መርዕድ ይናገራሉ፤ ብዙ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር፣ ፍጥነትና ቅልጥፍናቸውን ለማሻሻል የሚሰሩ የሶፍትዌር፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የሚያበለፅጉ ወጣቶችን መርዳት በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ይናገራሉ።
አቶ መርዕድ እንደሚሉት፤ የፈጠራ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ባንክ መሄድ የለባቸውም። በግሉ ሴክተር ያሉ ሰዎች የፈጠራ ባለሙያዎችን መርዳትና ማገዝ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው። የፈጠራው ውጤት መሬት ላይ ወርዶ ውጤት ሲያመጣ ደግሞ ከትርፉ ይካፈላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ በሀገራችን አንድና ሁለት የውጭ ኩባንያዎች አሉ እንጂ ዘርፉ ይህንን ሥራ የሚሰሩ ድርጅቶችን በመፍጠር ረገድ ብዙ ስራ ይቀረዋል። የፈጠራ ባለሙያዎች በታገዙ ቁጥር ብዙ ችግሮች ይፈታሉ። በገንዘብም፣ በፖሊሲም፣ በሕግም እና በሌሎች ማበረታቻዎች ሊታገዙ ይገባል። በሌላ በኩል የፈጠራ ባለሙያዎች የታክስ ማበረታቻ እንዲያገኙ ማገዝ እንዲሁም ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታም ማመቻቸት ያስፈልጋል።
‹‹እኔ ወደዚህ ሙያ ስገባ በራሴ ጥረት ከማድረግ በዘለለ በፋይናንስም ሆነ በማኔጀመንት ምንም የሚያግዝ አሠራር አልነበረም›› ያሉት አቶ መርዕድ፤ አሁን የተሻሉ ጅምሮች እንዳሉም ይገልጻሉ። በዚህ ዘመን በፈጠራ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች የተሻለ እድል እንዳላቸውም ገልጸው፣ ‹‹ሀገራችን በእድገት ወደኋላ ቀርታለች፤ በፍጥነት መሻገር የምንችለው በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመሆኑ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ማበረታታት ይገባል›› ይላሉ።
ዲጂታል ኢኮኖሚ በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በአገልግሎትና በሌሎች መስኮች በሀገር እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ ‹‹መንግሥትና የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ አተኩሮ ዘርፉ የሚያድግበትን ዘዴ በመቀየስ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችን ማደግ በምትፈልገው ፍጥነት ማድግ ትችላለች›› ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም