የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ማግስት ጀምሮ በተጠናና በተቀናጀ መንገድ ሀገርን
ከነበረችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ለመታደግ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎችን
ሠርቷል ፤እየሠራም ነው። በዚህም እየተገኘ ያለው ውጤት ከፍ ያለ ፣ እንደ ሀገር የጀመርነው የለውጥ/
የብልጽግና ጎዳና ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ያመላከተ ነው።
በተለይም ለውጡ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ኃይሎች የተናበበ ተግዳሮት/ፈተና እየተናጠ
ባለበት ሁኔታ፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከነበረበት ችግር ታድጎ ወደ አዲስ የስኬት ምዕራፍ እንዲሻገር እያሳየ
ያለው ቁርጠኝነትና ከዚህ የሚመነጨው ውጤታማነቱ፤ ሃገርን በመታደግ ሂደት ትልቅ አቅም እየሆነ
ነው።
በተለይም ቀደም ሲል የተጀመሩ ሃገር አቀፍ ትላልቅ ፕሮጀክቶች /እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ/ አጋጥሟቸው
የነበሩ ችግሮችን በማጥናት፤ በቂ በጀት በመመደብ ፤ጠንካራ ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቶቹ ነፍስ
ዘርተው በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ማበርከት እንዲችሉ እየተሠራና ውጤት እየተገኘበት
ነው። አንዳንዶቹም ፍጹም ከመዘረፍ አደጋ ወጥተው በአዲስ አደረጃጀትና ተልዕኮ ሃገርንና ሕዝብን
በሚጠቅሙበት ቁመና ላይ እንዲገኙ አድርጓል።
አዳዲስ ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን/ የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ፓርክ ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የአንድነት
ፓርክ /በአጭር ጊዜ አቅዶ በማጠናቀቅ ፤በፕሮጀክት አፈጻጸም አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል። ለለውጥ
ራሱን እንዳስገዛ መንግሥትም ለሕዝብ በአደባባይ የገባቸውን ቃሎች በመተግበር፤ ለቃሉና ለሕዝብ
ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ አሳይቷል።
በከፍተኛ የመንግሥት ክትትል እየተገነቡ ያሉ የኮይሻ፣ የወንጪ እና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች ሀገሪቱ
ያላትን የተፈጥሮ መስሕቦች በማልማት ተጨማሪ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የሚደረጉ
ጥረቶች፤ በአንድም ይሁን በሌላ ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሻገር በመንግሥት የሚደረጉ ጥረቶች እርሾ
ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።
ከዚህም ባለፈ ሃገሪቱ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ፤ ምርቱን ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሪ
እንድታገኝ ከፍ ባለ ትኩረት ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ስኬታማ በመሆን ከትናንት በስቲያ ሃገሪቱ ስንዴ
ወደ ውጪ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምራለች። ይህ ታሪካዊ እውነታ በሃገሪቱ የተጀመረው ለውጥ በብዙ
ፈተናዎች ውስጥም ቢሆን እያስመዘገበ ያለው ውጤት ከችግሮች በላይ የመብረር አቅም እየጎለበተ
መምጣቱን ያመላከተ ሆኗል።
የለውጥ ኃይሉ ለሕዝብ ቃል በገባባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የቱን ያህል በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ፤ ይህ
ትጋቱ ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች በላይ አድርጎ አፉን ሞልቶ በድፍረት በአደባባይ እንዲናገር ፤በሀገራዊ
የታሪክ መዝገብም የአዲስ ታሪክ ባለቤት እያደረገው እንደመጣ በተጨባጭ ያሳየ ነው። ለሃገራዊ ነገዎች
ብሩህነትም እንደ አንድ ማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር
ገጻቸው፤የስንዴ ኤክስፖርት መጀመሩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “እኛ የምናልም፣
ያለምነውን የምንናገር፣ የተናገርነውን ሌት ከቀን የምንሠራ፣ የሠራነውን ደግሞ አጠናቅቀን የምናሳይ
ስለመሆናችን ማረጋገጫ ነው” ማለታቸውም ለዚህ ነው። ለቃላቸው ከሁሉም በላይ ምስክር ሊሆን
የሚችለውም የተሠራው/ የሚታየው ሥራ ብቻ ነው።
የለውጥ ኃይሉን በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ፋታ በመንሳት ለሕዝብ
የገባቸው ቃሎቹ እውን እንዳይሆኑ የሚደረጉ ጥረቶች ቀን ተቀን መልካቸውን እየቀየሩ ሃገራዊ ፈተና
እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ይህ የመንግሥት ሀገራዊ ጥረት ከዚህ ከፍ ባለ ደረጃ ተግባራዊ ሆኖ ለማየት መላው
ሕዝባችን፤ከእያንዳንዱ ሀገራዊ የብጥብጥ አጀንዳ በስተጀርባ ያለውን ስውር አጀንዳ/ለውጡን ተስፋ
አልባ ማድረግና ማደናቀፍ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝቦ ዓይኖቹን ከለውጡ አጁንዳዎች ላይ ሳያነሳ
ከለውጡ ኃይል ጋር በቁርጠኝነት ሊሰለፍ ይገባል። በዚህም ለከራሱ አልፎ መጪውን ትውልድ የተሻለ
ሀገር ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ይችላል!
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም