በአልባሳት የሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያውያን የሥልጣኔያቸውንና ማህበራዊ የእውቀት ደረጃቸውን ያሳዩባቸው የበርካታ እደ-ጥበብ ፈጠራ ባለቤቶች ናቸው። የቀድሞ እናት አባቶቻችን ምንም ዓይነት የቀለም ትምህርት ሳይቀስሙ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው እውቀትና የሕይወት ልምድ ብቻ የራሳቸውን ፋሽን በራሳቸው የባህል ይዘት ለዘመናት ሲያበጁና ሲያጌጡ ቆይተዋል።
እነዚህ ልዩ ልዩ አልባሳትም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ይገኛሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ በጭላጭል የመጥፋት ጎዳና በማዝገም ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንደኛው በርኖስ ነው። ለመሆኑ በርኖስ ምንድነው? ይህ ጥያቄ በአገራችን የሰሜን ሸዋ ክፍል ወደሚኖሩት የመንዞች መንደር ይወስደናል።
በርኖስ ማለት ከበግ ጸጉር ተሸልቶ የሚዘጋጅ በተለይ ድሮ ድሮ በሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎች እና በተወሰኑ የጎጃም ክፍሎች የሚለበስ ወፍራምና ጥቁር ካባ መሳይ ልብስ ነው። በርኖስ ዝም ተብሎ ለብርድ ወይም ለፋሽን ያህል ብቻ የሚለበስ አይደለም። የራሱ የሆኑ የአለባበስ ሥርዓትና ጊዜ ያለው የክብር ልብስ ነው። ቀደም ሲል በነገሥታቱና በመኳንንቱ ዘንድ የሚዘወተር የጀግንነትና የልዩነት ማሳያ ነበር። ከዚያም ማኅበረሰቡ በደስታና ክብረበአላት ወቅት በክብር ይለበሳል። በደስታ ብቻም ሳይሆን በኀዘን ጊዜም ይጠቀሙት ነበር።
የሚገርመው ነገር ደግሞ በርኖስ ለሁለት ተቃራኒ ማለትም ለደስታና ኀዘን እንዲያገለግል ተደርጎ በልዩ ዲዛይንና የፈጠራ ሃሳብ የሚሠራ መሆኑ ነው። ከትከሻ እስከ ጉልበት፣ ቁርጭምጭሚት የሚደርሰው ይህ በርኖስ ከላይ ወደታች፣ አሊያም ከተፈለገ ዘቅዝቆ መልብስ እንዲቻል ተደርጎ ነው የሚሠራው። አንድ በርኖስ ሁለት ዓይነት አለባበስና ሁለት ትርጉም አለው። ተዘቅዝቆ የሚለበሰው በኀዘን ወቅት ብቻ ነው። ሌላኛው ልዩ የዲዛይን ፈጠራ ደግሞ በበርኖሱ በአንደኛው የትከሻ ትይዩ በቀንድ ቅርጽ የተሠራ ወደላይ ሾጠጥ ያለ የጌጥ ክፍል መኖሩ ነው። ይህ ቦታ ጠመንጃን ሸጎጥ አድርጎ ለመያዝ የሚያገለግል ምስጢራዊ ክፍል ነው። በዚህ መልኩ በርኖስን የሚለብሱ ሰዎች መሣሪያ ይያዙ አይያዙ ማንም ሰው አያውቅም። በተለያዩ ሙግቶችና በዳኝነት ሥርዓት ጊዜ በርኖስ የሚለበስ ሲሆን በዚህ ወቅት ሾጠጥ ያለው የጌጥ ክፍል በትከሻ ትይዩ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ይደረጋል። አንዳንዴም ከነጭ እጀ ጠባብ አቡጀዲ ጨርቅ እንዲሁም ከጠባብ ሱሪ እና ጭራ ጋር አብሮ የሚለበስበት ሥርዓት አለው፡፡
የበርኖስ አሠራር ከመጀመሪያው ጀምሮ ትልቅ እውቀትና ጥበብ ከጊዜ ጋር የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በቀላሉ የሚሠራ አይደለም። የሚሠራው ከበግ ጸጉር ቢሆንም ነገር ግን የሁሉም በጎች ጸጉር አያገለግልም። ለዚህ የሚያገለግለው የጥቁር በግ ሪዝ ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም በርኖሱ ለስላሳና ለሰውነት ምቾትን የማይነሳ እንዲሆን ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ግን የነጭ በግ ሪዝ ለማስጌጫነት መጠቀም ይቻላል። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገው የበግ ጸጉር የሚሰበሰበው በጎቹ በሕይወት እንዳሉ ጸጉራቸውን ብቻ በመሸለት ሲሆን እስከ አንድ አመት ድረስም በጎቹ መልሰው ጸጉሩን ያበቅላሉ። አንድ በርኖስ ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሰባት ኪሎ ያህል የበግ ጸጉር ያስፈልጋል፤ ይህ ማለት ደግሞ ቢያንስ የሰላሳ በጎች ጸጉር ይፈተላል ማለት ነው።
በጎቹ ከተሸለቱ ወይም ጸጉራቸው ከተገፈፈ በኋላ በዚህ ጥበብ የተካኑት የመንዝ እናቶች የተሰበሰበውን የበግ ጸጉር ነጣጥለው በመበተን እንዲደርቅ ያደርጉታል። በእነርሱ የሙያ ቋንቋ ደግሞ ‘ፍቶ’ ያደርጉታል ማለት ነው። ከዚያም በደጋን እየነደፉ በማድበልበል አመልማሎ ይሠራሉ። የተድበለበለውንም ጸጉር በእንዝርት እያሾሩ ይፈትሉታል። በመቀጥልም በኳስ መልክ የፈተሉትን ፈትል እየተረተሩ የማድራት ሥራ ያከናውናሉ። እያንዳንዱን ሥራ በጥንቃቄ የከወኑት እናቶችም ከዚህ ደረጃ ላይ በማድረስ ቀጣዩን ሥራ ለሸማኔ ያስረክባሉ። የሽመና ሥራው ሲጠናቀቅም ወደ በርኖስነት ለመቀየር ጥቂት ሂደቶች የሚቀሩትን ይህንን አምሳለ በርኖስ ከንጹህ ውሃ ላይ ጋቢ እንደማጠብ በደንብ እየተረገጠ ሪዙ ጥቅጥቅ እንዲል ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ጥቁሩን ከጥቁሩ ጋር፣ ነጩንም ከነጩ ጋር ለይተን ካልረገጥነው በርኖሱ ወደ ነጭነት የሚቀየር በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። በስተመጨረሻም የባህልና ፋሽን ጠበብቶቹ ዲዛይነሮች በዚህ ሁሉ ሂደት አልፎ የመጣውን በርኖስ በማሳመር ወደ ልብስነት ይቀይሩታል።
በመንዞች ዘንድ በርኖስ የሚዘወተረው በወንዶች ሲሆን በተመሳሳይ የአሠራር ሂደት፣ በቀሚስ መልክ የሚዘጋጀው የሴቶቹ ልብስ ደግሞ መላወሻ ይባላል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህ ልብስ የመንዞች ዋነኛ የባህል መገለጫቸው ነበር። በጣም የሚወዱት የክብር ልብሳቸውም ጭምር የነበረ በመሆኑ በተለይ በገና በዓል የገና ጨዋታ ላይ የሚያጌጡት በዚሁ ልብስ ነው። በአሁኑ ወቅትም ይህ ባህል ሙሉ ለሙሉ ባይደበዝዝም እንደ ሻማ እየቀለጠ ሄዶ ለመጥፋት የቀረው ትንሽ ብልጭታ ብቻ ነው። የዚህ ጥበብ ባለቤቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተመናመነ በጣት የሚቆጠሩ ያህል ብቻ ቀርተዋል። ታዲያ ይሄኛው ትውልድ ምን ይጠብቃል? ሙያዊ ጥበብ እንደ ወራጅ ወንዝ ነው፤ አንዴ ካለፈ ዳግም መልሰን አናገኘውም። አባቶቻችን ያለምንም ቴክኖሎጂ ከቆሙ በጎች ጸጉራቸውን ሸልተው በርኖስና ባና በሠሩበት አገር ውስጥ ቴክኖሎጂውን ታቅፈን ለቆዳና ሌዘር ምርቶች የምንጠቀመውን፣ የቆዳ ተረፈ ምርት የሆነውን የበጎችን ጸጉር የሚያህል ሀብት እንደዋዛ አውጥተን ስንጥል ቢያዩን ኖሮ እንዴት በሳቁብን ነበር።
እነዚያ ጥበበኛ አባቶቻችን፣ ያለንን ሀብት በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንኮራባቸው የራሳችን የሆኑ የፈጠራ ምርቶች ባለቤት መሆን የሚያስችሉንን በርካታ ጥበቦችን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አስቀምጠውልናል። እነዚህን ውብ የሆኑ የባህላዊ የፋሽን ፈጠራዎችን ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ ብለን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በባህላዊ የፋሽን አልባሳት ዘርፍ የሚሠሩ ተቋማትና ዲዛይነሮች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም