የሠላማዊ ትግል ፋናወጊው ሕይወት

የሠላማዊ ትግል ፋናወጊው እና ተምሳሌቱ በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሥርዓተ ቀብራቸው ትናንትና ተፈጽሟል።

ፕሮፌሰሩ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለብዙዎች የዕውቀት አባት፣ በአመራርነት ደግሞ ቅን አገልጋይ መሆናቸው ይወሳል፡፡ በፖለቲካ ተሳትፏቸው የሠላማዊ ትግል ተምሳሌት በመሆንም አብዝተው ይታወቃሉ። ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለው ባሰቡበት ቦታ ሁሉ ቀድመው መገኘት መገለጫቸው ነው ይሏቸዋል በቅርበት የሚያውቋቸው፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በአሁኑ አጠራር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን በመጋቢት ወር 1942 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ምሥራቅ ባደዋቾ በሾኔ፣ በኩየራ፣ በአዳማ የተከታተሉ ሲሆን፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአሜሪካን ሀገር ተከታትለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት የትምህርት ዘርፍ በመምህርነትና በተመራማሪነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በማስተማርና ምርምር ላበረከቱት ሙያዊ አስተዋፅዖ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

የደርግ መንግሥት ወርዶ የኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ሲቋቋም በየነ (ፕ/ር)፣ ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል። ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የትውልድ አካባቢያቸው እንደራሴ በመሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። ከ30 ዓመታት በላይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ተሳትፈዋል።

ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ባሉት የሀገሪቷ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፋቸው የሚገለጸው ፕሮፌሰር በየነ፤ በኋላም በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሲሠሩ ቆይተዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ነበር፡፡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚሊኒየምም አዳራሽ በተካሄደው የበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሀገርን መውደድ፣ ተግቶ መሥራትን ቀጣዩ ትውልድ ከበየነ (ፕ/ር) ታሪክ ሊማር ይገባል ብለዋል፡፡

በየነ (ፕ/ር) በሕይወት በነበሩበት ወቅት ታታሪና ሀገር ወዳድ ምሑር እንደነበሩ አስታውሰው፤ ለሀገራቸው በርካታ ሥራዎችን ሠርተው አልፈዋል፤ ይህ ሥራቸውም ከመቃብራቸው በላይ ሲታወስ ይኖራልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሁላችንም እንደእርሳቸው ጊዜ ሳናባክን ለሀገር ጠቃሚ ሥራዎችን ሠርተን ማለፍ አለብን ሲሉ ዐቢይ (ዶ/ር) መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ አባልና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ በየነ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፈታኝ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ለሕዝብ ድምፅ ሆነው መቆም የቻሉ ሰው እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያን አብዝተው የሚወዱና ስለኢትዮጵያ በተጠሩበት ጊዜ ሁሉ ቀድመው መገኘት መገለጫቸው እንደነበር የገለጹት ራሔል (ዶ/ር)፤ ምክትል ሚኒስትር ሆነው የሚኒስትርነት ደመወዝ፣ የሕዝብ ተመራጭ ሆነውም የተመራጭነት ጥቅማጥቅም አልፈልግም ብለው በመምህርነት ደመወዛቸው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ማገልገላቸውንም አንስተዋል።

ሁላችንም ቅንነት፣ መልካምነትና ሀገርን መውደድ ምን እንደሆነ ከበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ልንማር ይገባል ብለዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You