“በቀጣናው ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች በትብብር በማልማት ለተተኪው ትውልድ ማሻገር ይገባል” – ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የኢጋድ ዋና ጸሐፊ

አዲስ አበባ፡- በቀጣናው ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች በትብብር በማልማት ለተተኪ ትውልድ ማሻገር ይገባል ሲሉ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢጋድና አባል ሀገራቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ዕውን ለማድረግ ያዘጋጁት የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) በትናንትናው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኢጋድ አባል ሀገራት የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ባሕል፣ ዕሴትና ወግ የተትረፈረፈበት ቀጣና ነው።

በቀጣናው ያሉትን የቱሪስት ሀብቶች በሚፈለገው ደረጃ በማልማት ለመጠቀም እና ለትውልድ ለማሻገር በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በኢጋድ አባል ሀገራት በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የቀጣናውን ባሕል፣ ወግ፣ እሴት እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሚፈለገው ደረጃ መጠቀምና ማስተዋወቅ አልተቻለም ያሉት ጸሐፊው፤ በቀጣይ የቀጣናውን ሀገራት ሠላም በማስፈንና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢጋድ አባል ሀገራት የተለያየ አይነት የቱሪዝም ሀብት ያላቸው ሲሆን፤ የቱሪዝም ሀብቶቹን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የተዘጋጀው ማስተር ፕላን እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2030 የሚተገበር ሲሆን፤ ለቱሪዝም መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ለመረጃ ልውውጥ፣ የዘርፉን ተግዳሮት ለመፍታት እንዲሁም በአባል ሀገራቱ መካከል ነፃ የቪዛ ሥርዓት እና ወጥ የሆነ የቱሪዝም ፖሊሲና አሠራር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

 

ማስተር ፕላኑ የቀጣናውን ሀገራት በቱሪዝም ዘርፉ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

ቱሪዝም በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የቀጣናው ሀገራት የቱሪዝም ዘርፉ የሚያበረክተውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በአግባቡ በመረዳት ማስተር ፕላኑን ተፈጻሚ ማድረግ፣ ሠላምን ማስፈንና የተጠናከረ የመንገድ፣ የአየርና የባሕር መሠረተ ልማትን ማስፋፋት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

ኢጋድም በቀጣናው ሀገራት መካከል የተጠናከረና የተሳለጠ መሠረተ ልማት እንዲኖር የተለያዩ አጋር አካላት በመሠረተ ልማት ግንባታው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ በቀጣናው ያሉት የቱሪስት ሀብቶች በአግባቡ ካለመልማታቸውና ካለመተዋወቃቸው ባለፈም በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ ነፃ ቪዛና የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ በዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ የቀጣናው ሀገራት ዘርፉን በማልማትና በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን ያዘጋጁ ሲሆን፤ ለማስተር ፕላኑ ተግባራዊነት ኢትዮጵያ ከሌሎች የአባል ሀገራት ጋር በቅንጅትና በቁርጠኝነት እንደምትሠራ አስታውቀዋል።

የቀጣናው ሀገራት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የቱሪዝም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ከአምስቱ የልማት ምሰሶዎች ውስጥ በማካተት እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችንና የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የማልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተሠሩት ሥራዎችም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ የመጣ ሲሆን፤ የቀጣናው ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ ማጋራትና ድንበር ተሻጋሪ የቱሪዝም ልማት ላይ በትብብር መሥራት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You