አዲስ አበባ፦ በመስከረም ወር የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን መሠረት ያደረጉ የጉብኝት ጥቅሎች (ፓኬጆች) መዘጋጀታቸውን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በመስከረም ወር ቀጣይ ቀናት መስቀል፣ ኢሬቻ እና የዓለም ቱሪዝም ቀን እንዲሁም የተለያዩ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላት ይከበራሉ።
ሚኒስቴሩም በወሩ የሚከናወኑ የተለያዩ በዓላት ለቱሪዝም ገቢ ዕድገት ያላቸውን ሰፊ ጠቀሜታ በመረዳትና ከክልሎች ጋር በመነጋገር የተለያዩ የጉብኝት ጥቅሎችን አዘጋጅቶ እያስተዋወቀ ይገኛል ብለዋል።
በደቡብ የሀገሪቷ ክፍል ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላትን በመስከረም ወር እንደሚያከብሩ አመላክተው፤ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እንግዶች ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ከጫሞ ሐይቅ ጋር የተያያዙ የጉብኝት መርሐግብሮች ላይ እንዲሳተፉ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ ሌሎች የቱሪስት መስሕቦችን በመለየት የማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ለማድረግ ተቋሙ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡና አዲስ የለሙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዜጎች በልዩ ሁኔታ ለማስጎብኘት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥር የምታስተናግድባቸው ወቅቶች የዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ናቸው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ በተያዘው ወር የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገሪቷን የሚጎበኙበት ወቅት በመሆኑ በርካታ ገቢ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅበት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሲከበሩ በርካታ ሚሊዮን ሕዝቦች አደባባይ ወጥተው በአብሮነት፣ በፍቅርና በአንድነት የሚያከብሯቸው በዓላት ከመሆናቸው ባሻገር ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታደሙባቸው ደማቅ ሥነሥርዓቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ስለሺ እንደተናገሩት፤ በዓላቱ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባሕላዊ ትውፊት የሚፈጸሙባቸውን ሁነቶች ይዘዋል። ከሃይማኖታዊና ባሕላዊው ሥርዓታቸው ባለፈም ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሚናቸው የጎላ ነው።
የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለመጨመር እንግዶች በሚሄዱበት አካባቢ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለሆቴል አሠሪና ሠራተኞች፣ ለአስጎብኚዎችና ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው ምቹ አገልግሎቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በማቅረብ የቱሪዝም ገቢውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
በተጠናከረ ሁኔታ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑ ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል።
ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን እንዲጎበኙ እንዲሁም ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሁነቶች ላይ የተመሠረቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ አቶ ስለሺ ግርማ ጥሪ አቅርበዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም