በመዲናዋ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ119 ቢሊዮን ብር በላይ ወደኢኮኖሚው ፈሰስ ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በ2017 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ119 ቢሊዮን በላይ ብር ወደ ከተማው ኢኮኖሚ ፈሰስ ለማድረግ መታቀዱን የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ሳምሶም አይናቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2017 ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ቱሪስቶች 119 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወደከተማው ኢኮኖሚ ፈሰስ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት የነበሩ ጥንካሬ እና ድክመቶችን በመለየት የተሻለ አፈጻጸም ላይ ለመድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከዘጠኝ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 55 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥርን አንድ ሚሊዮን በማድረስ 64 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ፈሰስ ለማድረግ ታቅዶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች 119 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከጎብኚዎች ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ የሚሰላው በጉብኝት መግቢያ፣ በአስጎብኚ ማኅበራት ገቢ፣ ለትራንስፖርት እና ሆቴል አገልግሎቶች በሚከፈል ክፍያ እንዲሁም በሌሎች የቱሪዝም ተዋናዮች በሚገኝ ገቢ መሆኑን አቶ ሳምሶም አስረድተዋል፡፡

ወደ ከተማዋ የሚመጡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ባዛር እና ለሃይማኖታዊ በዓላት ለመታደም፣ የሕክምና እና የሥልጠና አገልግሎት ለማግኘት፣ እንዲሁም ለጉብኝትና ሰው ጥየቃ ዓላማ የሚመጡትንም የሚያጠቃልል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋን የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት ቁጥር ለማሳደግ በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ቁጥር የማሳደግ፣ ነባር መዳረሻዎች ላይ ዕሴት የመጨመር፣ ሳቢ እና ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ከተማዋን ብሎም መዳረሻዎችን የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ለዓለም የማስተዋወቅና ተደራሽነታቸውን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራም አቶ ሳምሶም አስታውቀዋል፡፡

በከተማዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በተለይም በመስከረም ወር ላይ የሚከበረው የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት ከተማዋን በማስተዋወቅ መዳረሻ ከማድረግ በተጨማሪም ገጽታ በመገንባት ከሀገር ውስጥ ሁነቶች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ኩነቶች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ የሚያስችል መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል

በዚህም በመስከረም ወር የሚከበሩትን የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ለሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ የተለያዩ ሁነቶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

Recommended For You