የአገርን የምጣኔ ሀብት በመፈተን ከሚታወቁት መካከል አንዱ ኮንትሮባንድ ነው። በኮንትሮባንድ ንግድ የአገር ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ይጎዳል፤ ህጋዊው ነጋዴ ከገበያ ለመውጣት ይገደዳል፤ የምርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ በተለይም እንደ አደንዛዥ እጽና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችና የታሸጉ ምግቦች በኮንትሮባንድ ወደ አገር እንዲገቡ ሲደረግ፣ ኮንትሮባንድ በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ከሚያደርሰው ችግር በተጨማሪ በሕዝብ ጤናና ሕይወትም ጠንቅ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ይህን የኮንትሮባንድ ንግድ አስከፊነት በሚገባ በመገንዘብ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ጸረ ኮንትሮባንድ ተግባር ማከናወን ከጀመረች ቆይታለች። በዚህም በተለይ ከአገራዊው ለውጥ ወዲህ ውጤታማ ተግባሮች ተከናውነዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የኮንትሮባንድ ንግድ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን መረጃዎች እያመለከቱ ናቸው።
በተለያየ ጊዜ የወጡ የጉምሩክ ኮሚሽንና ቅርንጫፍ ተቋማቱን ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ ብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች፣ በተለያዩ አካባቢዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ እንዲሁም ከአገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል። ጉምሩክ ኮሚሽንን ዋቢ ያደረገው ሰሞኑን የወጣው የኢፕድ ዘገባ እንዳመለከተውም፤ በአገሪቱ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውም አገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ በሚያጋልጥ ደረጃ እየጨመረ ነው።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው፤ በአገሪቱ ከ2011 በጀት ዓመት አንስቶ የተከናወነው የጸረ ኮንትሮባንድ ንቅናቄ እየተጠናከረ ቢመጣም ችግሩም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በ2011 በጀት አመት በሕገወጥ ንግድና በሕጋዊነት ሽፋን ሲንቀሳቀስ የነበረ የ9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ በ2012 በጀት አመት የ26 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ፣ በ2013 በጀት አመት 36 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ፣ በ2014 በጀት አመት የ50 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም በተያዘው 2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት ብቻ ደግሞ 40 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ኮንትሮባንድ መቆጣጠር ተችሏል።
ኮሚሽኑ እንዳለውም በርግጥም ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የተጠቀሱት የኮሚሽኑ መረጃዎች የሚያመለክቱትም፤ ከሚሽኑ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ሰፊ ተግባር ማከናወኑን ነው። ኮሚሽኑ ለእዚህ ተግባር ሊመሰገን ይገባዋል።
ጉምሩክ ይህን የአገር ጠንቅ ለመቆጣጠር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ባከናወነው ተግባር በየአመቱ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን መያዝ ችሏል። ይሄ አንድ ስኬት ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ይህን ስኬት አስመዝግቤያለሁ ብሎም አልተኩራራም፤ ችግሩ እየሰፋ መምጣቱንም አስገንዝቧል። የኮንትሮባንድ ተግባሩ በየአመቱ በብዙ ቢሊዮን ብር እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ሌላው የችግሩን አሳሳቢነት የሚያመለክት መረጃ ነው። ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥራው የያዛቸው የኮንትሮባንድ ሸቀጦች የተገመቱበት የገንዘብ መጠንም ችግሩ እጅግ ሰፊ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህን የኮንትሮባንድ ሸቀጥ መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ የንግድ ሥርዓቱን በማዛባት፣ አገር በታክስና በመሳሰሉት ማግኘት ያለባትን በማሳጣት በምጣኔ ሀብት ላይ ምን ያህል ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ቀጥሎም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ለአገር ስጋት እየሆነ የሚገኘው። በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን ብር የተገመተ የኮንትሮባንድ ሸቀጥ እየተወረሰም ነው እንግዲህ የኮንትሮባንዱ እንቅስቃሴ የበለጠ ተጠናክሮ የቀጠለው። ችግሩ እየሰፋ መምጣቱ ሌላ የላቀ ሥራን የሚጠይቅ ተግባር ከአገሪቱ ፊት ለፊት መደቀኑን ያስገነዝባል።
ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ጉምሩክን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እንደሚሳተፉ ይታወቃል። በዚህ ላይ የኅብረተሰቡ ሚና አለ። አሁንም የእነዚህን አካላት ሚና ይበልጥ በማሳደግ መሥራት እንደሚያስፈልግ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት በሚገባ ይጠቁማል።
መንግሥት እንደ መንግሥት በጉምሩክ ከሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላቱ በኩል ሰፊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፤ ለዚህም የጸረ ኮንትሮባንድ ሥራው በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ስለመሆኑና በቀጣይም በእዚህ ላይ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ያስገነዘበውን የኮሚሽኑን መረጃ በአብነት መውሰድ ይቻላል። በጸረ ኮንትሮባንድ ሥራው የሚሳተፉ አካላት ትብብርም ከመቼውም ጊዜ በላቀ መጎልበት ያለበት ስለመሆኑ መሬት ላይ ያለው እውነታ ያስገነዝባል።
ሕዝቡም ይህንን አገር ጎጂ የሆነ የኮንትሮባንድ ተግባር መዋጋት ላይ አተኩሮ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የጉምሩክ ከሚሽንም ኅብረተሰቡ በጸረ ኮንትሮባንድ ሥራው እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረቡ የሕዝቡን ሚና ታሳቢ በማድረግ ነው።
ስለሆነም ኅብረተሰቡ ለኮንትሮባንዲስቶች ባለመተባበር፣ እንደተለመደው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ ጥቆማዎችን በመስጠት፣ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችንም ባለመጠቀም ይህን የአገርና የሕዝብ ጠንቅ የመዋጋት ኃላፊነቱን ላቅ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መወጣት ይገባዋል።
ኮንትሮባንድ በሰፋና በከፋ ቁጥር የሚጠቀሙት ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሲሆኑ የሚጎዱት ደግሞ አገርና ሕዝብ ናቸው። በኮንትሮባንድ ተግባር ውስጥ እጅግ ብዙ ቢሊዮን ብሮች እንደሚንቀሳቀሱ የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ብቻውን በቂ ነው። ይህ ገንዘብና ሸቀጥ በሕጋዊ ገበያ ውስጥ ቢገባ አገር ልታገኝ የምትችለው ጥቅም ምን ያህል ትልቅ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
በአጠቃላይ ያሉት መረጃዎች ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር አሁንም የላቀና የተጠናከረ ሥራ ማከናወንን እንደሚጠይቅ ያመላክታሉ። ስለሆነም ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት አሁንም በላቀ ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም