( ክፍል አንድ )
ሕብረተሰቡ ለዓባይ ግድብ ያለውን አጋርነት የማጠናከርና ገቢ የማሰባሰብ አላማ ያለው “ሕዳሴ ግድብ ቱር” የተሰኘ የጉዞ መርሐ ግብር ሰሞኑን መጀመሩን ከ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ስመለከት ስለ ታላቁ ወንዛችን ዓባይ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ወደድሁ ።
የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አህጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል። በዓለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው። የዓባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት። ከቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ ዓባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር ዓባይ ነው። ለዓባይ ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነ ለም አፈሩ በመገበር ጥቁር ዓባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው።
ለራሱ ለጥቁር ዓባይ ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር ዓባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በአመት ይገብራሉ። የጥቁር ዓባይ የፍሰት መጠን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር በጠቃሚ ማዕድናትም የበለጸገ ነው። ጥቁርና ነጭ ዓባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና ዓባይ /ናይል/ ይሆናሉ።
ዳሩ ግን የናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ናቸው። የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም አልቻሉም። በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢፍትሐዊ ውል መሰረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል።
የሚገርመው ከጥር እስከ ሐምሌ ያለውን ፍሰት ያካትታል። ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ ሀገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እኤአ እስከ ተፈራረሙበት 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን ፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት፣ “ ከግብፅ መንግስት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ስራዎችን በአባይ ገባሮችና ሀይቆች ላይ መገንባት አይቻልም። “ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ “ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት። ” የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው። እኔ ግን ግብፅ የአባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው።
ጥንታዊ ስልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ህልውናዋ ከአባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ መስራቱ ይቅርና የምታሳየን ንቀት ያበግናል። ከግርጌዋ ተፋሰስ ሀገራት ለዛውም ከሱዳን ጋር ስለ ዳግም የውሃ ክፍፍሉ ምክክር ካደረገች ከ15 አመታት በላይ እንደሆናት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፈርኦኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል። ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም።
የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀመረች። የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጠለች። የተፋሰሱን ራስጌ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፤ ኢትዮጵያና ሰባቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቃሉ።
የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ ሀገራት የ1959ኙ ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች። ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ሀገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ ። ሆኖም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የዓባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም።
ሱዳንና ግብፅ ዓባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብደር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው።
የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል። በዚህም ጭው ባለበርሀ ግዙፍ መስኖዎችን ፣ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በዓለማችን ረጅሙን የዓባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል። የአስዋን ግድብ 10 አመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል። በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር፣ ከአሜሪካ ደግሞ እርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም ከእስራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያው ፊቷን ወደ ሶቪየት ሕብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች ። ግድቡ 90ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል።
እነዚህ ተፈናቃዮች ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብጻውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስተገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች ሀገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም። ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል።
የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ማለትም ግማሹን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል። ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም ከውኃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ640ሺህ በርሜል በታች ነው።
የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮ የሚጠጋ ኩም የሚጠጋ ሲሆን እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩም የሚጠጋ ብቻ ነው። እንዲሁም 547ሺህ 500 በርሜል በቀን የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች። ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ ሁሉ አማራጭ የኃይልም ሆነ የመስኖ ሀብት እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ ዓባይ ላይ ነው። እሷ የተሻለ አማራጭ ያላት መሆኑን አይኔን ግንባር ያርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች፣ እየተገዘተችና እየካደች ፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር ዓባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦ ፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ የአዞ እንባዋን እየረጨች ነው።
ግብፅ የአባይን የተፈጥሮ ፍሰት በመቀየር በርሀውን ለማልማት 30ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦዮችን ገንብታለች። ከአስዋን ግድብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ውሃ በመሳብ ቶሽካ የተባለውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመገንባት በርሀውን እያለማች ትገኛለች ። በአሁኑ ሰዓት ግብፅ 3 ነጥብ 76 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች ። ከአስዋን ግድብና ከአባይ ወንዝ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ። በትነትና በስርገት የተነሳ በየአመቱ ከ12 እስከ 14 በመቶ የሚደርስ ውሃ ከግድቡና ከመስኖ ቦዮች ይባክናል። ለመስኖ ከሚያስፈልገው ውሃ በላይ በመጠቀም ማባከንና ጥራት የሌለው የፍሳሽ መውረጃ በግድቡ ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ይጠቀሳሉ።
ከአሜሪካው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ የግብፅና የእስራኤል ግንኙነት በመሻሻሉ ፤ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ችግር የሚፈታ ከሆነ ከዓባይ ወንዝ 365 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በየአመቱ ለእስራኤል ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። ይህ የጂኦ ፖለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ውስብስብ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
ሌላዋ የግርጌ ተፋሰስና ጎረቤት ሀገር ሱዳን ግድቦችን ገንብታለች። እአአ በ1926 ሴናርን ለመስኖ፣ በ1936 ጀበል አውሊያ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ገንብታለች። በ1950 3ኛውንና 420ሺህ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም ያለው የሮሴሪስ ግድብን እንዲሁም ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን ገንብታለች። በዚህም በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬቷ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ችላለች። በግብፅና በሱዳን በመስኖ እየለማ ያለ መሬት የዓባይን 86 በመቶ ከምታበረክተው ሀገራችን ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል።
እንግዲህ ከፍ ብሎ እንደተመለከትነው በዓባይ የውሃ ሀብት ላይ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብፅ ናት። በሌላ በኩል የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የከፋ ድህነት ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የግብርና ድርጅት /ፋኦ/ ይፋ ያረገው መረጃ ያመለክታል። ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርታቸው እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ፋኦ ያትታል። በተፋሰሱ ሀገራት የሚገኝ አብዛኛው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም ።
አማካኝ የሀገሪቱ ኤሌክትሪክ የማዳረስ ፍጥነት ከ30 በመቶ የተሻገረ አይደለም። ከዜጋዋ ከ65 በመቶ የሚልቀው ሕዝቧ ለልጆቹ ማጥኛ፣ ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰያና ለምሽቱ ብርሃን የሚያገኝበት የኤሌክትሪክ ኃይል የለውም። ጸሎቱ የማታ እራትና መብራት አታሳጣኝ ቢሆንም አልሰላለት። የውኃ ሀይል ማመንጫ በተለይ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ለምቶ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በእድገታቸውና በልማታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ። ይህ የሀይል እጥረት ዜጎች ፊታቸውን ወደ ከሰልና የማገዶ እንጨት እንዲያዞሩ በማድረጉ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋን ከማስከተሉ ባሻገር የአየር መዛባትንና ብክለትን እያስፋፋ ይገኛል። ለዚህ ነው በተመጣጣኝ ዋጋ ኃይል ማቅረብ የግድ የሆነው ።
የራስጌ ሀገራት ግብርና በዋናነት የዝናብ ጥገኛ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአየር ፀባይ ለውጥ የተነሳ በየአመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ድርቅ ስለሚከሰት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ስለዚህ እንደ መስኖ ያለ አማራጭ የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ነው። የናይልን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነትና በኃላፊነት የመጠቀም ጉዳይ ከአመት አመት እየገፋ ከመምጣቱ ባሻገር የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ታንዛኒያ ከቪክቶሪያ ሀይቅ 170 ኪሎ ሜትር በተዘረጋ ቧንቧ ውሃ በመውሰድ በሀገሪቱ በከፋ ድህነት የሚታወቀውን ካሃማ የተባለውን አካባቢ በመስኖ ለማልማት እየሰራች ነው ። ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም ከወንዙ ድርሻቸውን በመጠቀም የውሃ ኃይል ማመንጫና የመስኖ ግንባታዎችን በማካሄድ ርሀብንና ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተዋል። ለዓባይ ወንዝ ውሃ 86 በመቶውን የምታበረክተው ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ የምትገነባው ከከፋ ድህነት ለመውጣትና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ለማረጋገጥ ነው።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም