ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ሰው ሲማር ሕይወቱ ያማረ የሰመረ ይሆናል። ብዙዎቹ የዓለማችን ሀገሮች የተሻለ ቦታ ላይ የደረሱት ለትምህርት በሰጡት ትኩረት ነው። ከበደ ሚካኤል የፃፉት ጃፓን እንደምን ሰለጠነች መጽሐፍም ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው።
ቻይና የሕዝብ ቁጥሯ ስጋት ሳይሆንባት ዜጎቿን በትምህርትና በሥልጠና አብቅታ አሁን ላለችበት ትልቅ ደረጃ የበቃችው በትምህርት ነው። ትምህርት የዕድገት የሥልጣኔ መሠረት ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂው፣ ኢንዱስትሪው የትምህርት ትሩፋቶች ናቸው።
በአየር የምንበረው፣ ባህርን የምናቋርጠው መሬት ለመሬት ጋራ ሸንተረሩን የምንሽከረከረው ዘመኑን የዋጁ መጓጓዣዎች ስለተሠሩ ነው ። ይህም ትምህርት ያመጣልን በረከት ነው።
ከርሰ ምድርን በርብረንም ሆነ መርምረን ወርቅን የመሳሰሉ ማእድናት የምናወጣው፤ በዘመናችን ተፈላጊ የሆነውን ፈሳሽ ነዳጅ የምናፈልቀው ሳይንስና ምርምሩ በሚሠሩት ሥራና ግኝት ነው።
ለዚህ ደግም ትምህርት ሁነኛ ሚና አለው። ወታደሩ በልበ ሙሉነት የሚዋጋው ዘመኑን የዋጀ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስድ ፤ ጦር መሣሪያ መፈታታትና መሰካካት ሲችል ነው። ሐኪሙ የሚያክመው፤ በሽታን የሚዋጋ፤ ሕመም ለሰዎች ስጋት እንዳሆኑ የሚረዳው ባገኘው ትምህርት ነው። ጋዜጠኛውም የትምህርት ውጤት ነው ።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር ሰሞኑን ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍልን ብሔራዊ መልቀቂያ አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የብዙዎች የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖል። ፈተናውን ከወሰዱት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ወደ 30 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው።
በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከተፈተኑ 339 ሺህ 642 ተማሪዎች መካከል 22 ሺህ 936 ተማሪዎች፤ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ከተፈተኑ 556 ሺህ 878 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 6 ሺህ 973ዎቹ ከግማሽ በላይ ውጤት አምጥተዋል።
በአጠቃላይ 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ከ 50 በመቶ በላይ ሲያስመዘግቡ ፣ ቁጥሩ በመቶኛ ሲሰላ 3.3 በመቶ ብቻ ነው። ከአጠቃላይ ተመዝጋቢዎች ውስጥ 77 ሺህ 98 ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ፈተናውን አልወሰዱም ። 50 ሺህ 170 የሚሆኑት ደግሞ በደንብ ጥሰት፣ ለመኮራረጅ በመሞከር እና በሌሎች ምክንያቶች አልተፈተኑም ።
ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በብሔራዊው ፈተና ይከሰት የነበረውን የፈተና ስርቆት እና ኩረጃ ለማስቀረት ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ ማድረጉ ተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ አድርጓል። በቀጣይ ጠንካራ ተማሪዎችን ለማውጣት የሚረዳ፣ የኩረጃ አጀንዳ፣ ወደ ቆሻሻ ገንዳ እንዲጣል የሚረዳ ጭምር ነው።
በአጠቃላይ ውጤቱ በኩረጃ ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው ማለት ይቻላል። ለወደፊት መምህራን በትኩረት አስተምረው፤ ተማሪዎችም አመርቂ ውጤት አምጥተው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚረዳ ነው።
ለዚህ ጽሑፍ የነጋገርኳቸው ተማሪዎች በሰጡኝ አስተያየት በየትምህርት ቤቱ በመደበኛ ትምህርት ሰዓት ከመምህራን ዕይታ ውጪ ሆነው የኪስ ስልክ በማየት ‹ፌስ ቡክ› ከፍተው ጊዜያቸውን በዋዛ በፈዛዛ የሚሳልፉ እንዳሉ ነግረውኛል ።
አንዳንድ መምህራንም ተማሪዎቹን አስመልክቶ በሰጡኝ አስተያየት፤ አብዛኛው ተማሪ ለንባብ ብዙም ትኩረት እንደማይሰጥ ፣ አስተማሪ ከነገራቸው በተጨማሪ የትምህርት መጽሐፋቸውን ለማንበብ ዳተኝነት እንደሚታይባቸው። ከዚህ ይልቅ በፈተና መኮራረጅ እየተለመደ መምጣቱን ጠቁመውኛል።
በፈተናው ተማሪዎች ጥሩ ውጤት አምጥተው እንዲያልፉ ያደረጉት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው፤ ይህ ደግሞ ከእነዚህ ትምህር ቤቶች ሌሎቹ መማር እንዳለባቸው አመላካች ነው። የግል ትምህርት ቤት መምህራንም ብቃታቸው ሊፈተሽ የሚችልበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል።
ለስማቸው እና ለገቢያቸው ሲጨነቁ የነበሩ የግል ትምህርት ቤቶች ለኩረጃ መስፋፋት እንደ አንድ ምክንያት መነሳታቸውም በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባል። የፈተና ኩረጃን በየአውራጃ የመሰባሰቢያ መረዳጃ አድርገውት የነበሩም ነበሩ።
መቼም ኩረጃን የፖለቲካ ሂሳብ ማወራረጃ ለማድረግ የሚቃጡም ፤ በአደባባይ ኩረጃ ወይም ሞት ባይሉም በኅቡዕ ኩረጃ ወይም ሞት የማለት ያህል ሆነው የተገኙም አልነበሩም ማለት አይቻልም። በአዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር አሰራር ዛሬ ላይ ቅስማቸው ተሰብሯል ።
ይህን ስንል ብዙ ተማሪዎች በመውደቃቸው ደስተኞች ነን እያልኩ አይደለም። ነገር ግን ለቀጣይ ለትምህርቱ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጠውና መንግሥት ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድ ለማምጣት ሁነኛ ሚና መጫወት መጀመሩ ውጤቱ የሚያሳየን ነገር አለ ለማለት ነው።
በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ለማስታወቂያና ለቀጣይ ተማሪ ለመመዝገብ ስለሚረዳቸው ብዙ ተማሪ አሳለፉ የሚለውን ይፈልጉት ነበር፤ ከዚህ የተነሳ አሁን በተገኘው ውጤት ከሁሉም በላይ መደናገጣቸው አይቀርም።
እነዚህ ጥምህርት ቤቶች ከመደናገጥ ወጥተው እራሳቸውን በአግባቡ መመርመር ይጠበቃባቸዋል። ‹‹ያለሽ መሽሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል›› እንደሚባለው ብሂል ትምህርት ቤቶቹ በስም እያሉ የሌሉ ሆነው እንዳይቀጥሉ ስለሚጠብቃቸው ጥልቅ ስራ ጊዜ ወስደው ሊያስቡ ይገባል። የመንግሥት ትምህርት ቤት አካባቢም ለተገኘው ውጤትችግሩ ምንድነው የሚለው መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው።
ለቀጣይ ለመምህራኑና ለትምህርት ባለሙያዎች ማነቃቂያ ሥልጠና መስጠት። ችግሩን ለመቅረፍ ትምህርት ቢሮዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መመካከር ይጠበቅባቸዋል፤ ለተማሪዎች በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራትም ያስፈልጋል።
ጥምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሺቲዎች ያላቸው የመቀበል አቅም በመገምገም እስከ 100 ሺ የሚደርሱ በፈተናው ከ50 በመቶ በታች ያስመዘገቡ ተማሪዎች ዝቅ ባሉባቸው የትምህርት ዓይነቶች ትምህርት ወስደው በመጪው ዓመት የፈተና ዕድል እንዲያገኙም የደረሰበት ውሳኔ የሚበረታታ ነው።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም