የሰላምን ጥቅም በአግባቡ ለመረዳት በእጅ ያለውን ሰላም አቅልሎ ማየት አስፈላጊ አይደለም ፤ ከዛ ይልቅ በዘመናት በሰላም እጦት ምክንያት የከፈልናቸውን ዋጋዎች ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት ፤ ዛሬ ላይ ያለንበትን ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች/ተግዳሮቶች ማስተዋል ተገቢ ነው።
ሀገራችን እንደ ሀገር በቀደሙት ዘመናት ከፍያለ ሥልጣኔ (ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልእልና የተጎናጸፈች) ፤ ባህር የተሻገረ ስምና ዝና ያላትና ይህንን ማድረግ የቻለም ትውልድ ባለቤት እንደነበረች የታሪክ መዛግብት በስፋት ዘግበውታል።
ከየትኛውም ሥልጣን (ማህበራዊ ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልእልና) በስተጀርባ ትልቁ ቁምነገር ሰላም ከመሆኑ አንጻር፤ ሀገሪቱን ለዛ ከፍያለ ታሪክ ባለቤትነት ያበቃት ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ የነበረው ሰላምና መረጋጋት ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።
በርግጥም ከነዛ ወርቃማ የታሪክ ምዕራፎች ቀጣይ የሆኑ ምዕራፎችን ስንመለከት ፤ የሰላም እጦት እና ከዚሁ የሚመነጭ ሀገራዊ አለመረጋጋት፤ የቀደመውን ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልእልና እንደሀገርና እንደ ሕዝብ ናፋቂዎች እንድንሆን አድርገውናል።
የቀደሙትን ረጅም ዘመናት ትተን ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ውስጥ እንኳን ያሰብናቸው ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ህልሞቻችን እውን ያልሆኑት በመካከላችን በነበረ አለመደማመጥና ይሄው በፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ነው።
ይህ ዘመን የተሻገረ ችግራችን ዛሬም ቢሆን እንደ ሕዝብ/ትውልድ ያሰብናቸውን ትላልቅ ህልሞች አፉን ከፍቶ ሊውጣቸው እያዛጋ ባለበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይህን የታሪክ ምዕራፍ ዘመኑን በሚመጥን የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቆመን መሻገር ካልሞከርን ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ቀልሎ የሚታይ አይደለም።
አንድም አሁን እንደሀገር ያለንበት ማሕበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራትና ከዚህ የሚመነጩ ሀገራዊ ችግሮችን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ የሚያራግቡ ኃይሎች በብዛት መኖራቸው፤ ከዚህም በላይ እነዚህን ኃይሎች በሁለንተናዊ መንገድ በመደገፍ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት የሚተጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከጎናቸው መሰለፋቸው ነገሮችን አሳሳቢ ያደርጋቸዋል።
በመሰረታዊነት ቁጭ ብሎ ካለመነጋገርና ካለመደማመጥ የሚመነጨው ሀገራዊ ችግራችን ፤ እንደ ትናንቱ የከፋ ዋጋ አስከፍሎን ፤ ወደ ቀደመው የጥፋት አዙሪት እንዳንመለስ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በሰላማችን ዙሪያ ከፍ ባለ ኃላፊነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
በተለይም ካለንበት ሀገራዊ የለውጥ የታሪክ ምዕራፍ አንጻር ፤ ለውጡ ይዟቸው የመጣቸውን ሀገራዊ ትሩፋቶች በአንድም ይሁን በሌላ፤ ትርጉም አልባ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በሀገሪቱ ሁከትና ግርግር በመፍጠር እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት እየሄዱበት ያለውን የጥፋት መንገድ በቁርጠኝነት ልንታገለው ያስፈልጋል።
መላው ሕዝባችን ከፍያለ ተስፋ ሰንቆ በብዙ መስዋዕትነት ያገኘውን የተሻለ የለውጥ አጋጣሚ ፤ እንደቀደመው ዘመን ከእጁ እንዳይወጣ ነገሮችን ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ መንፈስ ሊያጤናቸው ያስፈልጋል። የሚወስናቸው ውሳኔዎች ዛሬን ብቻ ሳይሆን በነገዎች ላይ ያለውን ተስፋ ታሳቢ ሊያደርጉም ይገባል።
በተለይም ከትናት የወረስናቸው ችግሮቻችን እንደ ሀገር የመሻታችንን ያህል ወደፊት አላራምድ ብለው ወደኋላ እየጎተቱን ባሉበት በዚህ ወቅት ፤ በራሳችን ላይ ተጨማሪ ችግሮችን በመፍጠር ነገሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆኑብን ነገሮችን በትዕግስት፣ በርጋታና በኃላፊነት መንፈስ ደግመን ደጋግመን መመርመር ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም