“ቤት ገመና ነው“ ሁሉን ነገራችንን በተለይ ለሌሎች ገልጠን የማናሳየውን ሁሉ የሚሸፍንልን ክትት አድርጎ የሚይዘን ነው። ምንም ሁሉም የሚኖርበት ቤት እንደ አቅም እንደ ኪሱ ጥራቱና ምቾቱ የተለያየ ቢሆንም አንገት አስገብቶ እግር አዘርግቶ ካሳደረ ግን ሁሉ ቤት ተብሎ ነው የሚጠራው:: አንዳንድ ቤቶች ቤት ይባሉ እንጂ የክረምቱን ዝናብ የበጋውን ጸሀይ ለመከላከል እንኳን ሲያቅማሙ ይታያሉ:: እንደዛም ሆኖ ደግሞ በተለይ ለመከራየት የሚጠራባቸው ዋጋ ጆሮን ጭው ያደርጋል::
እንዳንዴ ከቤቶቹ አቅመ ቢስነት የተነሳ ሰዎች ክረምት ላይ የሚዘንበውን ዝናብ ጨምሮ በብርድና ውርጭ የታጀበውን አስፋልት እየመረጡ ያሉበት ሁኔታ እየተበራከተ ነው። “ቤት በመጠኑም ቢሆን ለኑሮ ምቹ መሆን አለበት። ቢያንስ በመኝታ ለምናሳልፈው ሌሊት ምቹ ሊሆን ይገባል” የሚሉት አቶ ፈሩ ሰጤ በቤቶቹ ሁኔታ ከሚማረሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አንዱ ናቸው። የሥራ ቦታቸውም ሆነ መኖሪያ አድራሻቸው ጎጃም በረንዳ አካባቢ ነው:: ጎጃም በረንዳ ብዙ የሕይወት ገጠመኞች እንደላትም ይናገራሉ:: እሳቸው እንደሚሉት በተለይ መውደቂያ ላጡ ምስኪኖች በጥቂት ብሮች ከተቻለ አልጋ ካልተቻለ ደግሞ ኬሻ በጠረባ ጥሎ ቀን በድካም የዛለ ሰውነትን ማሳረፍ ይቻላል:: 20 ብር ያለው ምስኪን አልጋ ተከራይቶ የበላይ ሆኖ እንቅልፉን ሲለጥጥ ማደር ይችላል:: ያልሆነለት ደግሞ አስር ብሩን ከፍሎ አልጋ ስር ጉዝጓዙን አንጥፎ ጎኑን ማሳረፍ ማንም አይከለክለውም:: ካልሆነም በሰባት ብር (አሁን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ አስር ገብቷል) ኬሻ በጠረባ ጥሎ መ ልካም ህ ልም ማ ለም ማ ንም አ ይከለክለውም:: አቶ ፈሩ እንደነገሩን ጎጃም በረንዳ ከመምጣታቸው በፊት አውቶቡስ ተራና ሰባተኛ በርካታ አመታትን አሳልፈዋል:: ከሀገራቸው በፈጣኑ አውቶቡስ መጥተው አዲስ አበባ የቀሩትም በድንገት ነው:: ለመቅረታቸው ዋናው ምክንያት ህክምና ነበር:: ለሕክምና ከገጠር እንደመጡ አውቶቡስ ተራ ሻንጣ አሸክመው የሚያድሩበትን እየፈለጉ ሳሉ የተሸከመላቸውና ‹‹ የሚያድሩበትን መኝታ አሳዮታለሁ› ያላቸው ልጅ ከነሻንጣው የያዙትን ገንዘብ በሙሉ ይዞባቸው ተሰወረ:: ያን ቀን ማታ እንደሞኝ የተሸከመላቸውን ልጅ በመፈለግ ሌሊቱን ሙሉ ማሳለፋቸውን እና ‹‹ያውና ይሄውና በማለት ማሾፊያ መሆናቸውን አይረሱትም:: የኋላ የኋላም አካባቢውንና የጉልበት ሥራውን እየተለማመዱት ሲመጡ ሰባተኛ አካባቢ ላሉ ማደሪያዎች በወር እየከፈሉ ማደር ጀመሩ:: እሳቸው በነዚሁ ቤቶች ጦስ ለወራት ታመው ራሳቸውን በመሳት መንገድ ዳር ወድቀው ያገኟቸው ሰዎች ሆስፒታል ወስደዋቸው መዳናቸውን ይናገራሉ:: ድነው ከሆስፒታል ከወጡ በኋላም ወደ ሥራቸው ተመለሱ ::
በኋላም አሁን ወዳሉበት ጎጃም በረንዳ አካባቢ መምጣታቸውንም ያነሳሉ:: ጎጃም በረንዳ ከመጡ በኋላም የጉልበት ሥራዎች በመሥራት ኑሯቸውን ይገፋሉ:: ሲገኝ ደህና አልጋ ተከራይተው ተመስገን ብለው በጥሩ ህልም የታጀበ ሌሊት ያሳልፋሉ:: ካልሆነም አልጋ ስር ተከራይተው አልጋው ላይ የተከራየውን ሰው እንቅስቃሴና ማንኮራፋት እያዳመጡ ተመስገን ብለው ጎናቸውን ያሳልፋሉ::
ጎጃም በረንዳ ሁሉንም ሰው በእኩልነት ታስተናግዳለች:: በአንድ አልጋ ከላይና ከስር ሆኖ ሳይተዋወቁ አድሮ መለያየትም የጎጃም በረንዳ አንዱ የሕይወት ክፍል ነው:: ሁሉም አልጋም ሆነ አልጋ ስር ተከራይ አረቄም ሆነ ጠጅ ቀማምሶ ስለሚመጣ አንዱ የአንዱን ሁኔታ የሚያስተውልበት ጊዜ የለም:: ሁሉም ‹‹ከመቼ ገብቼ በወደቅኩ›› ነው የሚለው::
አቶ ፈሩና መሰሎቻቸው በእዚህ አካባቢ ላይ ተከራይተው የሚያርፉባቸው ስማቸው ቤት የሚባሉት መጠለያዎች እጅግ የተጠጋጉ ወይም እንደ ልብ የማያንቀሳቅሱ ከመሆናቸውም በላይ ጣሪያውን ተጠግቶ ብዙ ሰዎች እንዲይዝ ታስቦም ፎቅና ምድር ተደርገው እንደሚሰሩም ሳቅ እያፈናቸው ይናገራሉ:: በለስ ቀንቷቸው ቀበሌ የፈቀደላቸው እነዚህኑ ቤቶች እስከ ሦስት ደረጃ የቆርቆሮ ቤቶች ወደላይ ተሰርተው ለኪራይ ያውላሉ:: አፓርታማ የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸዋል::
አፓርትማንታዎቹ በኮምፕለሳቶ የተካፈሉና እጅግ ጠባቦች ናቸው:: በአንዱ ክፍል የሚሰራው በሌላው ክፍል በቀላሉ ይሰማል:: በስሱ የሚተነፈስ ትንፋሽ እንኳ በቀላሉ ይሰማል ይላሉ አቶ ፈሩ:: ሌላው አደጋ ደግሞ ደረጃ ተብሎ በቁርጥራጭ እንጨቶች የተሰራው መወጣጫ በዘዴ ካልተወጣበት ወደታችኛው ክፍል አምዘግዝጎ ይጥላል:: ተሰናክሎ መቅረት በራሱ ሳይበቃ በተከራዩ ላይ ቁርጥራጭ ቆርቆሮ ወይም እንጨትና ብረቶቹ የመቆራረጥ እንዲሁም በደንብ ባልተመቱት ሚስማሮቹ የመወጋጋት ተጨማሪ አደጋ ይደርሳል:: ከታች የተኛ ሰው ላይ መውደቅም ብዙ ጊዜ እንደሚያጋጥምም ይናገራሉ::
አቶ ፈሩ እንደሚያስረዱትም በቤቶቹ ውስጥ ያለው ፈተና በዚህ አያበቃም ኮርኒሳቸው አጭር በመሆኑ ዝናብ ሲጥል ብርዱ በጋ ሲሆን ሙቀቱ የምድር ገሃነብ ያደርጋቸዋል:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ሲበዙበት ደግሞ መጥፎ ጠረን የመፍጠራቸው ነገር ያየ ብቻ ነው ሊያውቀው የሚችለው::
እነዚህ የአከራዮቻቸው የእለት ጉርስ የተከራዮቻቸው ደግሞ የደከመ ጎን ማሳረፊያ የሆኑ አፓርታማ በቤቶች ለዘመናት በነተቡ አልጋዎቻቸው ይታወቃሉ:: አልጋው በቱሃን፤ በቁንጫና ቅማልና ሌሎች ተባዮች የተመላ ነው:: ጆንያ በለበሰ ወለል ላይ ብርድ ልብስና አንሶላ ጭምር ተጎዝጉዞባቸው የተሟላለት አልጋ ተብለው ይከራያሉ::
አቶ ፈሩ አላበቁም ብዙዎቹ ቤቶች በርና ቁልፍ የላቸውም፡፤ ቤቶቹ በርና ቁልፍ ያላቸውም ቢሆን እንደልብ ለመዝጋትም ሆነ ለመክፈት አይመቹም:: ደግሞ አልጋ ተከራዮቹ የሚመጡበት ሰዓት የተለያየ በመሆኑ ክፍታቸውን መቆየታቸው ግድ ነው:: ብዙዎቹ አልጋዎች ከሌሊቱ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ባሉት ሰዓታት ይከራያሉ:: አልጋዎቹ ተከራይተው እንዳበቁ የቤቶቹ አከራዮች ከውጭ ቆልፈው አስፋልት ላይ ሌሊቱን ያነጋሉ:: እሳት ቢነሳ እንኳን አብሮ ከማረር ውጭ ማምለጫ የለም::
አልጋዎቻቸውን አከራይተው አስፋልት ላይ ያደሩትም አከራዮች ጠዋት 12 ሰዓት መጥተው በሮቹን በመክፈት ተከራዮቻቸውን ማሰናበት ይጀምራሉ:: ቀኑም በሌላ አዲስ ሕይወት ይቀጥላል::
እዚህም ግን ሌላ ምቾት የሚነሳ ነገር ማጋጠሙ አልቀረም እንቅልፍ ሲጥላቸው ጠብቆ ቀን የለፉበትን ገንዘብ ለመውሰድ የሚሻና እሳቸው ውስጥ አዋቂ ነው የሚሉት ወሮበላ አንገት ለአንገት በመተናነቅ ጭምር ገንዘብ የሚዘርፍም አለ:: ሆኖም ከዘራፊዎቹ ጋር እየተለማመዱ ሲመጡና ቤተኛ መሆናቸው ሲረጋገጥ ዝርፊያው ይቆማል::
‹‹ቀስ በቀስ ወሮበላዎቹ እያወቁንና እየለመዱን ሲመጡ ዘረፋውን ተውን›› የሚሉት አቶ ፈሩ ንፁህ አየር እየተነፈሱ ያለምንም ኮሽታ ተኝተው የሚያድሩ መሆናቸውንም ፈጣሪያቸውን ከማመስገን ጋር ይናገራሉ:: አንዳንድ ጊዜ ከቁንጫው መብዛት፤ ከሰው መተፋፈግ በሚፈጠር መጥፎ ጠረንና ከኪስ ብርበራና ዘረፋ ጋር ተያይዞ ከቤቶቹ ይልቅ ጎዳና አሥር እጅ እንደሚመረጥና የተሻለ መሆኑንም ደጋግመው ያረጋግጣሉ:: ከተከራዩበት አልጋ ቤት ለቀው በጠፍ ጨረቃ አስፋልት ላይ ወጥተው የተኙባቸው አጋጣሚዎችም በርካቶች መሆናቸውን ይናገራሉ::
ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉት ሌላው የአቶ ፈሩ ጓደኛ ከአልጋ ቤቶቹ ይልቅ የጎዳና ሕይወት የተሻለ መሆኑን ያምናሉ:: በተለይ የቁንጫው ነገር በጣም አማራሪ መሆኑን ይናገራሉ:: ‹‹ቁንጫ ቢሉህ ቁንጫ እንዳይመስልህ፤ ደም የጠገበ ነው:: ሲመጠምጥህ ይሉንታ የለውም›› ይላሉ የአልጋ ቤቶችን ሁኔታ የኋሊት እያስታወሱ:: በዚህ ላይ ደግሞ ለአልጋ የሚከፈል ገንዘብ ስታጣና ኬሻ በጠረባ ስትከራይ የበረታ ስቃይ ያጋጥምሃል:: ሰው በዝቶ ወለሉ ሁሉ ሲጨናነቅ በአንድ ጎንህ ብቻ ለመተኛት ትገደዳለህ:: ልገላበጥ ብትል እንኳ ቦታ ስለሌለ እንደ እንጨት ተገጥረህ ታድራለህ:: ልገላበጥ ብትል እንኳን ከጎንህ ከተኙት ጋር ጸብ ከማትረፍ ውጭ ዕድል የለህም:: ስለዚህ እግርህ እንደታጠፈ ጀርባህ መሬት ሳይነካ አድረህ ትነሳለህ::‹‹ ቆመህ እንዳደርክ›› ቁጠርው ይላሉ እየተንገፈገፉ::
እሳቸው እንደሚሉትም በአልጋ ቤቶች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተማረው ጎዳናን ከመረጡ አምስት አመታት አልፏቸዋል:: አሁን ጎዳናን ቤታቸው አድርገው ኑሮን ተያይዘውታል:: ሆኖም ጎዳናም ቢሆን ችግር አያጣውም:: ‹‹…. ክረምት ሲሆን ከባድ ችግር ይደርስብናል:: አሁን ያለንበት ሥፍራ ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ ቦታ ክረምት ሲመጣ ቦታ እንደሚቀይሩ ይናገራሉ:: ብርዱም እጅግ ይፈትናቸዋል::
ባለፈው ክረምት ግን ጎርፉ ወደ ሌላ አካባቢ ተቀይሶ የሚሄድበትን ቦይ በመሥራታቸው ተገላግለዋል:: ከላይ የሚመጣውን ዝናብ ለመከላከልም ጥሩ ላስቲክ ወጥረው ነው ያሳለፉት:: ቢሆንም ደንቦች በተደጋጋሚ እያፈረሱባቸው ተቸግረው ቆይተዋል:: አሁን ግን በጋ በመሆኑ ላስቲክም ሆነ ሌላ ነገር ሳይወጥሩ ጎዳና ላይ በነፃነት ያድራሉ:: ለሥራ ወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ ዕቃቸውንም በላስቲክ አስረው እዛው ማደሪያ ቦታቸው ላይ ያኖራሉ:: አሁን በአካባቢው ስለታወቁና በአብዛኞቹም እንደቤተኛ ስለሚታዩ ማንም አይነካባቸውም:: እሳቸውም እንደ አቶ ፈሩ ለረጅም ዓመታት በስቃይ ከኖሩባቸው አስቀያሚ ቤቶች ይሄ ጎዳና እንደሚሻል ያነሳሉ:: ከምንም በላይ ለሚተነፍሱት ንፁህ አየር ደጋግመው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ::
‹‹በነዛ ቤቶች እኖር በነበርኩበት ጊዜ ልብሴና ቀን ስሸቅል የዋልኩት ገንዘብ በተደጋጋሚ ይሰረቅ ነበር›› ሲሉም ያስታውሳሉ:: እዚህ ግን እሰረቃለሁ የሚል ስጋት በፍፁም የላቸውም፡፤ ለዓመታት በጎዳናው ሲያድሩና በላስቲክ ጠርዘው ትተውት ሲሄዱ አንድም ሰው ንክች አድርጎባቸው አያውቅም::
እንዲህም ሆኖ በአካባቢው ንጽህናው የተጠበቀና ለኑሮ በተነፃፃሪም ቢሆን አመቺ ቤት ቢያገኙ ተከራይተው የመኖር ፍላጎት አላቸው:: ቢሆንም እንዲህ ያሉት የግል ኪራይ ቤቶች ከጎጃም በረንዳ እስከ አውቶቡስ ተራ ባለው አካባቢ ዋጋው የሚቀመስ አይደለም:: የዕለት ሕይወታቸውን የሚገፉበት በመሆኑም ከእዚህ አካባቢ ደግሞ መራቅ አይፈልጉም::
ስለዚህም ለአቶ ፈሩም ሆነ ለጓደኛቸው ጎጃም በረንዳ ሕይወታቸው ናት:: ጎጆ ባይቀልሱም፤ ትዳር ባይመሰርቱም ጎጃም በረንዳ ሁሉንም ሆና ተስተናግዳቸዋለች::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም