‹‹አባት›› የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ የአንድ ነገር ምንጭ ወይም ጀማሪ የሚል ትርጓሜን ይይዛል። ‹‹አባት›› ማለት ተፈጥሮውን ‹‹ለልጆቹ›› የሚያስተላልፍ ማለት ነው። ‹‹አባት›› ማለት በልጆቹ ላይ ሥልጣን ያለው ማለት ነው። ምድራዊ ልጆች ሰውነታቸውንና ነፍሳቸውን ከወላጆቻቸው ይወስዳሉ። አባትነት በሰው ሰውኛ ሲገለፅም ልዩ ምስጢር አለው።
አባትነት እምነት፤ እናትነት እውነት በሚል ብሂልም አባት መሆኑን በእምነት አምኖ ተቀብሎ ለልጆቹ ጥላ ሆኖ ከመከራ ከልሎ ሲያሳርፍ፤ ማደጋቸውን በጉጉት እየተመለከተ ነጋቸውን በአይነ- ህሊናው ሲቃኝ፤ በእርጅናው ደግሞ በፀሎት የልጆቹን ቀና መንገድ ሲመኝ የሚኖር ታላቅ ገፀ በረከት ነው – አባትነት።
ታዲያ ይህን የአባትነት ምስጢር ያፈረሰ፣ ትስስሩን ባልተገባ መንገድ የበጠሰ ልጅን በአባት ላይ በጭካኔ እንዲነሳ ያደረገ ታሪክን ከፍትህ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ ተመለከትኩኝ። አባት ብቻ መኖሩ መከታ ለሚሆነን የእኔ አይነቷ አባት ወዳድ አሰቃቂ ቢሆንም አንባቢ ይማርበት ዘንድ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ቆይታ።
ልጅ አይውጣልህ የተባለው አባት
ዘላለም ገብረ ሚካኤል ይባላሉ። እድሜያቸው በስልሳዎቹ መጨረሻ የሚገመት አዛውንት፤ እንዲሁም፣ ሀብት ሞልቶ የተረፋቸው አይነት ባለፀጋ አባት ናቸው። ልጆቻቸውን ባላቸው የሀብት መጠን አንቀባርረው “ውድ” የሚባል ትምህርት ቤት አስተምረው አሳድገዋል። ልጆቹም አጀማመራቸው ላይ የት ይደርሳሉ የተባሉ፣ በጣም ጎበዝ፤ ለቤተሰቦቻቸው ታዛዥ፤ ሰውን አክባሪ ልጆች ነበሩ።
ልጆቹ እያደጉና እየጎረመሱ ሲሄዱና ያለስስት አባታቸው የሚሰጧቸውን ገንዘብ መጥፊያ ሆኗቸው እንደ አይን ጠፉ። የት ይደርሳሉ የተባሉት ወጣቶች ፈር ለቀው ያልተገባ ባህሪን ያሳዩ ጀመር። ይባስ ብሎ ያለምንም እፍረት ውጭ ማደርንና መዋልን የዘወትር ተግባራቸው አደረጉት። ከሶስት ልጆቻቸው አንዷ በከባድ የሱስ ሕይወት ውስጥ ገበታ መውጣት ተስኗት በአእምሮ ህመም ላይ ትገኛለች።
ሌላው ልጃቸው ደግሞ ከአባቱ ኪስ አንስቶ ያልፈተሸው ኪስ የለም በሚባል ደረጃ ለሱሱ ማስታገሻ የሚሆን ገንዘብ ፍለጋ ሲዘርፍና ሲቀማ ቆይቶ በአንድ የተረገመ አገጣሚ ገንዘብ ለመቀማት በትር የሰነዘረባቸው አዛውንት እንደወደቁ እስከ ወዲያኛው በማሸለባቸው የተነሳ በፖሊስ ሲታደን ቆይቶ ወህኒ ከወረደ ሰነባብቷል።
ሶስተኛው ልጃቸው ባህሪው መልካም ቢመስልም የገንዘብ ነገር የማይበቃው፣ ዘወትር ከአባቱ ጋር ብር ስጠኝ አትስጠኝ በሚል ሙገት የሚገጥም አይነት ልጅ ነው። እሳቸውም በልጆቻቸው አለመባረክ ዘወትር እያነቡ ጤናቸው ተጓድሏል።
“የቱ ጋ ነው የተሳሳትኩት?” እያሉ ሁል ጊዜ እራሳቸውን ይጠይቃሉ። አስበው አስበው ለበጎ ያሉት ወደ ክፉ ተቀይሮባቸው እንጂ ልጆቻቸው በእንዲህ አይነት ሥነምግባር ውስጥ እንዲወድቁ አስበው ምንም አለማድረጋቸው ደግሞ አንጀታቸውን ድብን ያደርጋቸዋል። ቀናና ተገቢ ነው ያሉት አስተዳደግ ልጆቻቸውን የማጣመሙ ነገር ከውስጣቸው አይወጣላቸውም።
ከሰው እንዳያነሱብኝ ሲሉ የሰጧቸው ገንዘብ ከሰው በታች ያዋላቸው ልጆቻቸው ለማንም የማይጠቅሙ ብኩን የመሆናቸው ነገር ቆሽታቸውን አድበኖ እኚያ በኩራት የሚጎማለሉት ታላቅ ባለፀጋ አባት አንገታቸውን የደፉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
አዛውንቱ አባት በኀዘን ኩርምት ከማለታቸውም በላይ ሶሰተኛ ልጃቸው ገንዘብ ካልሰጡት የሚያሳየው ያልተገባ ባህሪ በፍርሃት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። አይኑን ማጉረጥረጡን፤ ዛቻና ማስፈራራቱን ሲመለከቱ “አንደው አንድ ቀን ደፍሮ እጁን ያነሳብኝ ይሆን?” የሚለው የዘወትር ጥያቄያቸው ሆኖ ልባቸውን አስጨንቆታል። የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል አይነት ነገር ደርሶባቸው ዛሬ የዘወትር ስጋታቸው እውን ሆኗል …
ሱስ አቅሉን ያሳተው ወጣት ነቢዩ
የአቶ ዘላለም ሶስተኛ ልጅ ነቢዩ ዘላለም ከልጆቻቸው መካከል በአመለ ሸጋነቱ ነበር የሚታወቀው። ከእናቱ እቅፍ የማይወጣ የሳሎን ጌጥ አይነት ልጅ ነበር። በትምህርቱም ጎበዝ ከመሆኑ የተነሳ በየአመቱ ሽልማት ይዞ የሚመጣ፤ ከቤተሰብም አልፎ በዘመድ አዝማድ የተወደደ ልጅ ነበር። አባቱ በስስት ስ ለ ሚ መ ለ ከ ቱ ት አርጉልኝ ያላቸውን በሙሉ ያደርጉለት ነበር።
ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪን በከፍተኛ ውጤት አልፎ ዘጠነኛ ክፍል የገባ የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ነበር ነቢዩ ያልተገባን ባህሪ ማሳየት የጀመረው። መጀመሪያ አካባቢ የጉርምስና ብቻ የሚመስሉ የባሀሪ ለውጦችን ቢያሳይም፣ እየዋለ እያደር ግን ከዛ ትሁት ልጅ የማይጠበቁ ቃላትን ያወጣ ጀመር። ከፀያፍ ቃላቱ በላይም የትምህርቱን ነገር ቀስ በቀስ እርግፍ አድሮጎ ተወ።
ትምህርት ቤት ከሚገባበት ቀን የሚቀርባቸው ቀናት በለጡ። ውሎው ጫትና ሺሻ ቤት ሆነ። እሱ በሚያመጣው ገንዘብ እንዲያዝናናቸው ዙሪያውን የከበቡት ጓደኞቹ እሱ ከአባቱ ከሚሰጠው ትንሽ የኪስ ገንዘብ በላይ እንዲያመጣ ዘወትር ይገፋፉት ጀመር።
እንደ ቀልድ የገባበት የሱስ ሕይወትም እንዳይወጣ አድርጎ እግር ከወረች ያሰረው ወጣት ነቢዩ በአብዛኛው አባቱን ጨቅጨቆ፣ ገንዘብ ተቀብሎ፤ ይህ ካልሆነም ሰርቆ ለሱና ለጓደኞቹ የሚሆን ገንዘብ ይዞ ይወጣ ጀመር። እለት በእለት ከሱስ ቤት አካባቢ የማይጠፋው ከጫትና ከሲጋራ አልፎ ወደ አደንዛዥ ሱስ ውስጥ ገባ። ለዚህ ሱሱ የሚሆን ገንዘብ ባጣ ጊዜ ደግሞ እንደ እብድ የሚያደርገው ሲሆን፣ በዚሁ ምክንያትም ሰው እስከመግደል ድረስ ወንጀል ሊፈፅም የሚችል አይነት ወጣት ሆነ።
ነጋ ጠባ አባቱን አስፈራርቶ፤ ሲለውም ሰድቦና ዝቶ ገንዘብ ሲቀበላቸው ኖሯል። ገንዘብ ሲጨርስ ብቻ ወደ ቤት ብቅ የሚለው ወጣት ልጅ አይውጣሎት የተባሉ የሚመስሉትን አባት አቶ ዘላለም ቁም ስቅላቸውን ያሳያቸው ጀመረ።
ከስድብና ዛቻ አልፎ ሽጉጥ ይዞ በመምጣት እያስፈራራቸው በርካታ ገንዘብ እንዲሰጡት ማስገደድ ከጀመረ ሰነባብቷል። ላባቸውን ጠፍ አድርገው ለልጆቻቸው ሕይወት መቃናት ድጋፍ ያደርግልኛል፤ በእድሜዬ መጨረሻ እጦርበታለሁ ያሉትን ጥሪታቸውን ሊያሳጣቸው የተነሳውን ልጃቸውን በሽማግሌ ቢያስጠይቁት፣ ተንበርክከው ቢለምኑት አሻፈረኝ፣ ገንዘብ ወይም ሞት በማለት የጭካኔ እርምጃ ለመውሰድ እየፎክረ ገባ።
እሳቸውም “ዘመኔን ሙሉ ከኖርኩበት ቤት ሬሳዬ ይውጣ እንጂ ቤት ንብረቴን ሸጬ ለአንተ አልሰጥም” በማለት ቁርጠኛ አቋማቸውን አስቀመጡ። አባቱ ሃሳባቸውን እንደማይቀይሩ የተረዳው ልጅም ቂም ቋጠሮ ሊያጠፋቸው ተነሳ።
ወላጅ አባት ላይ የተሳበው ቃታ
ወሩ ህዳር ነው። ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም ህዳር የሚታጠንበት ቀን። ሰው ሁሉ የቤቱን ቆሻሻ አውጥቶ በማቃጠል በሽታው ክፉ ሃሳቡ በሙሉ ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ተጠራርጎ እንዲጠፋ የሚመኝበት ቀን። አቶ ዘላለምም እንደ ጎረቤቶቻቸው በጠዋት በመነሳት ግቢያቸውን ጠራርገው አቃጥለዋል። እለቱ የቅዱስ ሚካኤል የንግስ በዓል ስለነበር በአቅራቢያቸው ወዳለው ቦሌ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ደርሰው ለመምጣት ከቤታቸው ይወጣሉ። መድረሻቸውን ቤተክርስቲያን እንዲሆን ተመኝተው ቢወጡም መንገድ ላይ ደካክሟቸው ወደ ቤት ይመለሳሉ።
“ምነው ያለወትሮዬ እንዲህ አቅም አነሰኝ?” በማለት ቤታቸው ተመልሰው ለንግስ በዓሉ የተዘጋጀውን ቀማምሰው አረፍ ይላሉ። ቀኑን ሙሉ ተኝተው የዋሉት አባት አመሻሹ ላይ ተነስተው ግቢያቸው ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር ልጃቸው ነቢዩ ወደ ግቢ የገባው። ከወትሮው በተለየ ተቆጥቷል፤ ገና በጊዜ መጠጥ እንደጠጣ አፉ ያስታውቃል። አባቱን ሊያናግራቸው እንደሚፈልግ አስረድቶ ወደ ውስጥ ይጋብዛቸዋል።
“ለመጨረሻ ጊዜ ልጠይቀህ ቤቱን ሸጠህ ትሰጠኛለህ ወይስ …?” በማለት ይጠይቃቸዋል። እሳቸውም በምንም አይነት ሁኔታ አቋማቸውን እንደማይቀይሩ ያስረዱታል። ያኔ ነው እንግዲህ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ቴዲ ባር አካባቢ ወላጅ አባቱን፣ ሟች ዘላለም ገ/ሚካኤልን በሽጉጥ ጭንቅላታቸውን ሶስት ቦታ በመምታት ሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገው።
ነቢዩ ዘላለም አባቱ ላይ ያደረገውን የተመለከቱት እናቱና ጎረቤቶች ባሰሙት ጩኸት በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር አዋሉት።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጎጂው በሕይወት እንደሌሉ በማረጋገጥ ለምርመራ ከላከ በኋላ ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ማረፊያ ቤት ይወስደዋል። የሰነድና የሰው ማስረጃውን በአግባቡ ያጠናቀረው የወንጀል ምርመራ ቡድን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ፣ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ያቀርባል።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ወላጅ አባቱ የሆነውን በሽጉጥ ጭንቅላቱን በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ባደረገው ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶበት በ22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አድርጓል። ተከሳሹ ከማህበራዊ አገልግሎት ለ5 ዓመት እንዲታገድ ሲልም ወስኖበታል። ተከሳሽ ዳኞችን በችሎት ፊት ውሳኔያችሁ የማይረባ ነው ከተፈታሁ በኋላ አሳያችኋለሁ በማለቱ ችሎቱ በተጨማሪነት በ 1 ዓመት ቀላል እስራት ቀጥቶታል፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ነቢዩ ዘላለም ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ቦሌ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ቴዲ ባር አካባቢ ወላጅ አባቱ ሟች ዘላለም ገ/ሚካኤልን በሽጉጥ ጭንቅላቱን ሶስት ቦታ ላይ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 (1) (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡
ውሳኔ
ክርክሩን የመራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ሲሆን ተከሳሹ ክሱ በችሎት ተነቦለት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ተጠይቆ ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ በበቂ ማስረጃ በማቅረብ አረጋግጧል።
ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተከሳሹ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት በደረጃ 1 እርከን 38 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ተከሳሹ የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ፣ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በእርከን 37 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል፤ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በተከሳሹ ላይ በ22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣና ከማህበራዊ አገልግሎት ለ5 ዓመት እንዲታገድ ሲል ወስኖበታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም