የሀገራችን የግብይት ሥርዓት ስሙ “ነፃ”፣ ባህርይው ባርነት፣ ተግባሩ ሽፍትነት መሆኑን በድፍረትና በአደባባይ የምንመሰክረው እኛ የእለት እንጀራ አሮብን ጦም ማደርን ባህል ያደረግን ዜጎች እንጂ በቁጥር እንቆቅልሽ የሚያማልሉን መንግሥታዊና ምሁራዊ እስታስቲክሶች አይደሉም። ርሃባችን የዳቦ እጦት ጠኔ ብቻ ሳይሆን የፍቅር ርሃቡም ተጨምሮ ስምና ትርጉም አልባ ክስተት ከሆነብን ሰነባብቷል።
“ምግብማ ሞልቷል አምላክ መች ነሳኝ፣
የፍቅር ርሃብ ነው እንዲህ ያከሳኝ።
ሁልጊዜ እበላለሁ ሆዴ መች ጎደለ
ፍቅራችን ብቻ ነው ያልተደላደለ። ”
በማለት ያዜመው ነፍሰ ሄሩ ጥላሁን ገሠሠ ዛሬ በሕይወት ኖሮ “ይህንን የዜማ ግጥም በአስረቅራቂው ድምጽህ አንጎራጉርበት” ቢሉት “እጄን ለካቴና፤ እግሬን ለብረት ሰንሰለት” እሰጣለሁ በማለት ጨክኖ እምቢታውን ሳይገልጽ የሚቀር አይመስልም።
ምክንያቱም፡- ሌሎች ስንኞች እንኳን እንዳሉ ቢሆኑ፤ “ሁልጊዜ እበላለሁ ሆዴ መች ጎደለ” የሚለውን ስንኝ እንደነበረ አዜመዋለሁ ቢል ቁርሱን ጥሬ ቢቆረጥምም ለምሣና ለእራቱ ይቺንው አጥቶ ድፍት ብሎ የሚያድረው የሀገሬ አዳሜና ሔዋኔ ወፈ ሰማዩ ሕዝባችን በሰላማዊ ጥሪ ድምጻዊውን ለመቃወም አደባባዩን ማጥለቅለቁ አይቀርም። ለሠልፍ ለሠልፍማ እኛን ማን ብሎን! “ምግብማ ሞልቷል ወዘተ.” የሚሉ ፉከራዎች ከእነ ጥላሁን ገሠሠ ጋር ሳይቀበሩ የቀሩ አይመስልም።
አንድ ኪሎ ሥጋ የአንድ ምስኪን ዜጋን የወር ደመወዝ ያህል ተቆርጦለት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር በላይ ባሻቀበበት በዚህ ለጉድ በጎለተን ዘመን የተወለዱት ልጆቻችን፤
“ሞልቷል በሀገራችን የምግብ ዓይነቶች፣
አትክልትና ፍሬ የሥጋ ብልቶች”
የሚለውን ሙዚቃ በትዝታ እየተብከነከንን ስናንጎራጉር ቢሰሙን “በስብስቴ ዘመን የተረት ትዝታ የምንብከነከን” እየመሰላቸው ሳይሳለቁብን አይቀሩም።
“በንጉሡ ዘመን ተሸሞንምኖ በላስቲክ እየታሸገ በአሥር ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የወንጂ ስኳር ይተዋወቅ የነበረው በመኪና እየተዞረ ሰዎች ገዝተው እንዲሞክሩት በልምምጮሽ ጭምር እየተለመኑ ነበር። በዘመነ ደርግም እንዲሁ ሀገሪቱን እያንገበገበ የነበረው ጦርነትና ድርቅ እያለ እንኳን የአንድ ኪሎ ስኳር ዋጋ ሁለት ብር ከአሥራ አምስት ሣንቲም ነበር። አንድ ኪሎ ጨውም በሃያ አምስት ሣንቲም ገዢ አልነበረውም።
አንድ ኪሎ ሥጋ በአምስት ብር፣ ሩዝ በተፈለገው መጠን ከሌላ ሸቀጥ ጋር በመጣያነት ያውም የአብዮት ጠባቂዎች ማስፈራሪያ ታክሎበት ጭምር ይሸጥ የነበረው በግዴታ ነበር…ወዘተ.” እያልን ብናላዝን ልጆቻችን “እሺ ተረቱ አለቀ!?” ብለው ኩም አድርገው እንደሚያሳፍሩን አንጠራጠርም። ልጆቻችን ብቻም ሳይሆኑ ዘመንኞቹ የዛሬዎቹ ፖለቲከኞችም “በዱሮ በሬ ያረሰ የለም” እያሉ ሊያፌዙ እንደሚችሉ ቀልብያችን ይነግረናል።
ዛሬ ዛሬማ ባህርይው ያልሆነውን ገበያ በስም ብቻ “ነፃነት” አጎናጽፎ ከማሞካሸት ይልቅ ከባርነቱ ነፃ እንዲወጣ መዋጀት ቢቻል በእጅጉ በተሻለ ነበር። በባርነት የተያዘው በየጊዜው መንግሥት በሚያወጣቸው የይስሙላ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተጠፍንጎ መሆኑን እንኳን እኛ የቤተሰብ ቀለብ አቅራቢ ወላጆች ቀርተን ከጡጦ ያልተላቀቁ ልጆቻችንም ቢሆኑ በደመ ነፍስም ቢሆን በሚገባ ይረዱት ይመስለናል።
እንዴት ቢሉ እኛ ወላጆች የኑሮ ውድነቱን ጫና መቋቋም ተስኖን ሌት ተቀን እንባችንን ስናፈስ እነሱም ጡጦ ጎደለብን ብለው እሪ እያሉ ሲያለቅሱ አብረን ስለምናላቅሳቸው አንድ ሀገራዊ ችግር እንዳለብን ሳይረዱ አይቀርም፤ ያውም በጨቅላ አእምሯቸው። ምናልባትም ጠባቂ መላእክቶቻቸው እውነቱን በሚገባቸው ቋንቋ ሹክ ሊሏቸው ይችሉ ይሆናል። ማን ያውቃል!
ለአባባሉ ይቅርታ ጠይቀን “ባሪያና ቃሪያ እንዳቃጠለ ይኖራል” የሚለውን የአበው አባባል “በነፃነት ስም ባርነት ለገባው የግብይት ሥርዓት” ብሂሉን ብንዋስ ጡንቸኞቹ “አትንኩን ባይ ሹሞቻችን” የሚቆጡን አይመስልም። ቢቆጡንስ ማን ያደምጣቸዋል፤ ምንስ የሞራል ብቃት ይኖራቸዋል።
የትናንቱን አንድ አብነት ብቻ እናስታውስ። ካስፈለገም ከትናንትናና ከትናንት ወዲያ ተሞክራችን ሰባት ጊዜ ሰባ የሚደርሱ መረጃዎችን ማቅረብ እንችላለን። ለምሳሌ፡- የመብል ዘይት ከመንግሥት እጅ እንደማይወጣ በሥልጣን የተበየነብን ውሳኔ ጭራሹኑ ችግሩን አባብሶ ምን ደረጃ ላይ እያደረሰን እንዳለ የምናየው ነው። ይህ መንግሥታዊ የኢኮኖሚ ቁጥጥር ሊፈረጅ የሚገባው “በነፃ ገበያ ስያሜ ወይንስ በባርነት!?” ባርነት የነፃነት ተለዋጭ ስም ከሆነ ደግ፤ እንዳሉን እንቀበላለን።
ከባርነት ግዞት ዛሬም ድረስ “ነፃ ያልወጣው” የስኳር ጉዳይም “ሻሂ! ሻሂ” እንዳሉ ማለዳ ላይ ወደ ትምህርት ቤታቸው እያነቡ የምንሸኛቸው ልጆቻችን እምባቸው ተሟጦ እርማቸውን ስላወጡና “ባዶ ሻሂ” መጣጣትን ስለለመዱልን ሸክማችንን አቃለውልናል። ደግነቱ ዘመናዊዎቹ ሐኪሞቻችን ከጤንነት ጋር አያይዘው “ስኳርን” ስለሚኮንኑ ልጆቻችንን ማሞኛ ዘዴ ስላላጣን እናመሰግናቸዋለን።
እግረ መንገዱን ግን የሕክምናው ወጪና የመድኃኒቱ ዋጋ ንረትም ንብረትም ተሸጦ ቢሆን ስለማይመከት የሚሻለው የሕመም ሁሉ መቅሰፍት እንደ እስራኤላውያን ፋሲካ ሳይነካን እንዲያልፈን በጾምና በጸሎት መቃተት ብቻ ነው።
በኢኮኖሚክሱ የጥናት ዘርፍ “ነፃ” ተብሎ የሚጠራው የግብይት ሥርዓት በንግድ ልውውጦች ሂደት የመንግሥት ቁጥጥር ወይንም ፖሊሲ ጫና ሳይኖርበት በአምራች/አቅራቢ እና በሸማች/ተጠቃሚ መካከል ምንም ዓይነት ቁጥጥር ያለመኖሩን ለማመልከት ነው። በነፃ የገበያ ሥርዓት ውስጥ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ የሚወሰነው በፍላጎትና በአቅርቦት ሕግ መሠረት እንጂ “በደንብ አስከባሪዎች ወይንም በፖሊሶች” የዱላ ማስፈራሪያ ወይንም ሱቅን በማሸግ በሚወሰድ እርምጃ አይደለም።
በነፃ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ተዋንያኑ ተግባብተው የሚገበያዩት በድርድር እንጂ “የምንትስ ቢሮ ሹመኞች” ፈርመው በሰጡት የሸቀጦች ዋጋ ዝርዝርና ሻጩም ለይምሰል ያህል በፍሬም ውስጥ አቆነጃጅቶ ለይስሙላ ያህል በሚለጥፈው ሰንጠረዥ መሠረት አይደለም። “አንዳንዴ መንግሥትም እኮ ገበያውን ለማረጋጋት መብትም ግዴታም አለበት” የሚለው መከራከሪያ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚጨበጥ እውነት አይደለም፤ ሲሆንም አላየንም።
የሀገራችን ነፃ ገበያ በምን መስፈርት ተለክቶ “አርነት” እንደታወጀለት ቢብራራልን አንጠላም። የሰሞኑን የሲሚንቶ ገበያ ትራዤዲ ውሎ ብቻ ለአብነት ማስታወስ ይቻላል። መንግሥት “የሲሚንቶ ስርጭቱንና ግብይቱን እቆጣጠራለሁ” ባለ ማግሥት አንዲት ከረጢት ሲሚንቶ ለቀብር ማስፈጸሚያ ማግኘት የተሳናቸው ቤተሰቦች እንደምን ኀዘኑ እንደከፋባቸው ደጋግመን ያየነው ነው። ለቤት ግንባታማ ምን ሲደረግ ሲሚንቶ በገበያ ላይ ተገኝቶ።
መንግሥት የሲሚንቶ ቁጥጥሩ አላዋጣ ብሎ ናላውን ሲያዞረው “ለቅቄዋለሁ እንዳሻችሁ ተገበያዩ” ብሎ በወሰነበት ማግሥት ገበያው “ሕግን ሽፋን ባደረጉ ሽፍቶች” እጅ ወድቆ እንደምን ሕዝቡ እንደሚሰቃይ እያስተዋልን ነው። “ቤተ ሰሪ ደም የለውም” የሚለው የተለመደ አባባል “እምባንም” ቢያክልበት ተገቢ ይሆናል።
“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉ ወደ ዳቦ ጉዳያችን እንመለስ። በቅርቡ ይህ ጸሐፊ አዘውትሮ የማለዳ ቁርሱን የሚገዛበት ዳቦ ቤት በአንድ እሽግ የተሸነሸነ ዳቦ ላይ ስድስት ብር እንደጨመረ ለደንበኞቹ የገለጸው በኩራት ነው። “ስመ ገብስ” መልክ ባለው ጠይም ዳቦ ላይ ደግሞ አሥር ብር ተጨምሯል።
ይህ የሆነው በሙስና ድርጊት ስሙ በጎደፈው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው። ያገባኛል ባይ አካል ሄዶ ዳቦ ቤቶቹን ይፈትሽ። የግራሙ ጉዳይማ ባይነሳ ይሻላል። የቀድሞዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ዳቦ ለተራበ!” እያሉ የተሟገቱበትን መፈክር ዳግም አንስተን በካርዳችን መንበረ ሥልጣኑን ባነጠፍንለት መንግሥታችን ላይ ብንፈክርና ብንጮኽ አግባብ ይመስለናል።
የዚህን ጸሐፊ ልብ በእጅጉ ያቆሰለን አንድ ሁኔታ ልጥቀስ። ድርጊቱ እንኳን በኢትዮጵያ ምድር ቀርቶ በየትም ዓለም የማይደረግ መሆኑ እንደ ሀገር እፍረት ነው ቢባል ማጋነን አይገባም። አንዲት ብላቴና የሃያ አምስት ሳንቲም ቆሎ ሰፍራ ስትሸጥ ያስተዋልኳት በቆርኪ ወይም በቆርኪ መሰል መስፈሪያ ነበር።
በአጭሩ የቆርኪውን ስፍር እንቁጠረው ካልን ከሃያ አምስት ጥሬ መብለጡን እጠራጠራለሁ። በአጭሩ ለነፃ ገበያችን ትሩፋት ማሳያነት ይህ ልብ ሰባሪ ገጠመኝ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ምኑን ከምኑ ጋር አመሳሰልክ እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ። ኑሮ ካሉት መቃብር መሞቁን ያመንነው በዘንድሮ ኑሯችን ነው።
የእስታስቲክሱ የቁጥር ጨዋታና የኑሯችን ገመና እንደተኳረፈ ኖረን የምናልፈው እስከ መቼ ድረስ ይሆን? ችግሩስ ስለምን በግልጽነትና በዝርዝር አይገለጽልንም? የንግድ ሥርዓቱን እመራለሁ የሚለው መንግሥታዊ ተቋምስ እስከ መቼ “ይህንን ያህል ቶን ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቻለሁ፣ ይህንን ያህል ሜትሪክ ቶን ስንዴ አከፋፍያለሁ፣ ይህንን ያህል ሊትር ዘይት ለሕዝብ አቅርቤያለሁ በማለት እያማለለን ይኖራል?”፤ “ነገሩ ከሆነ የተገላቢጦሽ፤ አህያ ወደ ሣር ውሻ ወደ ግጦሽ” ይሏል ይሄኔ ነው።
መቼም መንግሥታት ሁሉ ሕዝባቸውን የሚደልሉበት ብልሃት አያጡም። አንዳንዴ በዓለም ገበያ ይመካኛል። አንዳንዴ በተፈጥሮ የአየር መዛባት ይኮነናል። አዘውትሮም የሂሳብ ቁጥሮች ለማደነጋሪያነት ሥራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል። ይህ ከዘመን ጋር የሸበተው ዘዴ በእኛ ላይ ሲተገበር እያየን ነው። አሮጌ አስተሳሰብና ርእዮተ ዓለም ለማስተናገድ ማን ብሎን?
ዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎች ተመረቁ የሚል ዜና ስናደምጥ እልልታችንን ሳንጨርስ በማግስቱ የዳቦው ግራም ተቀንሶ መጠኑ ቀንሶ ውስጡ ባዶ ሆኖ ወደ ዕንቁላል ደረጃ ዝቅ ሲል እናያለን። አብሮም የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበት ተገልጋዩ ሕዝብ እንዲማርር ሲዘየድ እናስተውላለን።
ስኳርና ዘይት ገባ በተባለበት ቀን በከተማ ሽፍትነት የመሸጉ ጨካኞች እንዴት ባለ ዘዴ እንደሆነ በማይታወቅ ረቂቅ ስልት “ገባ” የተባለውን ሸቀጥ ሙልጭ አድርገው ወደ መጋዘናቸው በማስገባት በመቶ እጥፍ እየቆነጠሩ ለመከረኛው ሕዝብ እንዲቸረቸር ያደርጋሉ።
ይህ ጸሐፊ አንዳንዴ ለመንግሥታችን ምነው የደርግ መንግሥትን ያህል ጥቂት ኮስታራ ሀሞት በሰጠው እያለ ይመኛል። ይህ ምኞቱ የቢቸግር ዘዴ እንጂ በርግጥም ያ ሥርዓት የሚናፈቅ ሆኖ አልነበረም። በዚያ ዘመነ ደርግ “የሕዝብ ሱቅ” ይባል በነበረው መዋቅር ይገለገል የነበረው ሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል ነበር። የኑሮ ከፍታና ዝቅታ እጅግም ፕሮቶኮሉ አይጠበቅም።
በቤተሰብ ቁጥር የስኳር ኮታ ይደለደላል። በቤተሰብ ቁጥር ዳቦ ይታደላል። በቤተሰብ ቁጥር ዱቄትም ጤፍም ይከፋፈላል። ይህንን አስተዳደር የሚመሩት ደግሞ በደመወዝ የተቀጠሩ ሠራተኞች ሳይሆኑ በነዋሪው ሕዝብ የተመረጡ አመራሮች ናቸው። ይህ ጸሐፊ የወጣትነቱ ዕድሜ ገደብ ሳይጥልበት በ25 ዓመት ዕድሜው ግድም በቅንነትና በታማኝነት በመኖሪያው አካባቢ (ከፍተኛ 25 ቀበሌ 02) የሕዝብ ሱቅ ሰብሳቢ በመሆን ማገልገሉን የሚያስታውሰው በኩራት ነው።
በዚሁ አገልግሎቱ ምክንያትም ሕዝቡ የሰጠው የክብር እውቅና በዘመኑ ሁሉ ማሕበረሰብን ሳይታክት እንዲያገልግል ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖታል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያስ በሕዝብ የተመከረባቸው አንዳንድ መሰል ወይንም የተሻሉ ዘዴዎች ቢተገበሩ አዋጭ አይሆን ይሆን? ሰሚ ጆሮ ካለ መመካከሩ አይከፋም።
መንግሥታችን ሆይ!
የዴሞክራሲ መብታችንን ተጠቅመን እንድንማጸን ይፈቀድልን። ለመሆኑ በርግጡ የሀገራችን ገበያ “ነፃ” የሚል ስም ሊሰጠው ይገባል? ከመንግሥት ቁጥጥር ባርነትስ አርነት ወጥቷል? የገበያውን ሥርዓት እንደፈለጋቸው የሚያተረማምሱትንና የንግዱን ሥርዓት እንዳሻቸው የሚያምሱት የከተማ ሽፍቶችን በውኑ መቋጣጠር ከአቅምህና ከመዋቅርህ ውጭ ሆኖብሃል? ሕዝቡ ጮኾ ጮኾ ድምጹ ሰልሏል።
ከልማት ስኬቱ ዜና ጎን ለጎን ቢያንስ ገበያው ተረጋግቶለት በገፍ ባይሆንም የእለት ጉርሱን እንኳ ሳይሳቀቅ እንዲያገኝ የገበያ ሥርዓቱን ከእብደቱ ለመፈወስ ስለምን ተሳነህ። በቅርቡ እንኳን በሣምንቱ ቀናት እንዲቆሙ በተፈቀደላቸው የከተማችን የአደባባይ ገበያዎች ላይ ደላሎች እንደፈለጉ ሲፈነጩ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል። አንዳንድ የወረዳና የክፍለ ከተማ ሹመኞች ላይ ክትትል ቢደረግ አይከፋም።
ለፖለቲካው የወገኑና በሁሉም ስብሰባ ላይ “የመንግሥትን እድሜ በሺህ ዓመት የሚመኙትን ቤተኞች ብቻ ከመጥራት በመቆጠብ” ከተርታው ሕዝብ የተመረጡ ግለሰቦች በገበያው እብደት ላይ እንዲወያዩና እንዲመክሩ መድረክ ቢመቻችላቸው እውነቱ ከመፍትሔ ጋር ተፍረጥርጦ ይወጣ ነበር።
ቢቻልም እነዚሁ “ነፃ” ነዋሪዎች ለየክፍለ ከተሞቹ፣ ወረዳዎቹና ቀበሌዎች በኮታ የሚደርሳቸው ሸቀጥ በግልጽነትና አሰልቺ ባልሆነ ተራና ወረፋ በየሸማቾቹ ጣቢያዎች እንዲከፋፈል የራሳቸውን ዘዴ ቀይሰው እንዲያስፈጽሙ ሙሉ መብት ቢሰጣቸው የተሸፋፈነው ጉድ ይገላለጥ ነበር።
ከላይ የተጠቀሰው ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ካስፈለገ በሁሉም ሕዝባዊ ጉዳዮች ጥልቅ ካላልን የሚሉት የሠፈር ፖለቲከኞች ለጊዜው ከዚህን መሰሉ አሠራር እጃቸውንም ሆነ አፋቸውን እንዲሰበስቡ ማዕቀብ ይጣልባቸው። መንግሥቴ ሆይ! ያኔ ውጤቱን ታየዋለህ።
ይህ አንድ ዘለላ የመፍትሔ ጥቆማ አቅጣጫ እንጂ ለውስብስቡ ችግራችን ሁሉ መፍትሔ ይሆናል ማለት አይደለም። የሀገራዊ ችግሮቻችን ጉዳይ ቢዘረዘር አንድ ሺህ አንድ ሌሊት ስለሚፈጅ ሃሳባችንን በዚሁ እንቋጭ። “ቢቸግር ጤፍ ብድር” የተባለው ስለምን ነበር? አባባሉስ ለዛሬ ይሠራል። እንጃ። ሰላም ለሕዝባችን፤ በጎ ፈቃድ ለዜጎች ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም