የኢትዮጵያ ስፖርት በተለያዩ የእድገት ደረጃዎች እየተጓዘ አሁን ካለበት ይድረስ እንጂ የወደፊት ጉዞው ግን ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት የተዛባ ስለመሆኑ ለስፖርቱ ቅርብ የሆነ ሁሉ ሊታዘበው ይችላል። የወራሪውን ጣሊያን ቆይታ ተከትሎ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው ዘመናዊው ስፖርት በሂደት የስፖርት ማህበራትን በመመስረትና በበላይነት የሚመራውን ተቋም በማደራጀት እንዲሁም ሃገራት በሚወከሉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ሊጎለብት ችሏል። በመንግስት አደራጅነትም የልማት ድርጅቶች አምስትና ከዚያ በላይ በሆኑ ስፖርቶች ክለቦችን እንዲያቅፉ በመደረጉ የተሻለ እድገት አሳይቷል።
ይህ ህግ ተሽሮ የስፖርት ፖሊሲ ከተዘጋጀ በኋላ ግን ስፖርት ህዝባዊ ነው ከሚል ብሂል የዘለለ ለውጥ ሳያሳይ እነሆ ሶስት አስርት ዓመታትን ተሻግራል። ፖሊሲው የኢትዮጵያ ስፖርት በመንግስታዊ አካል እየተመራ በህዝባዊ አደረጃጀት እንዲስፋፋ እና ሃገርም የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ አቅጣጫ ቢያስቀምጥም ባለፉት ዓመታት ግን ይህ ተግባራዊ አልሆነም። በመሆኑም አዲስ ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ በቅርቡ እንዲዘጋጅ አስገዳጅ ሆኖ ተገኝቷል። ነገር ግን ይህም በትክክል ተግባራዊ ሳይሆንና በየጊዜው እንደሚቀያየረው የስፖርት አመራር ውል ያለው አቅጣጫ ሳይዝ መድረሻውም በውል ሳታወቅ እያዘገመ ይገኛል።
በእርግጥ በግል ጥረታቸውም ሆነ ባላቸው ምቹ ሁኔታ ታግዘው ሃገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክሉ በስኬታቸውም የኢትዮጵያን ሰንደቅ በክብር የሚያውለበልቡ ስፖርተኞች አልጠፉም። ይሁንና ዓለም ከደረሰበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ ካላት ምቹ ሁኔታ እንዲሁም በዘርፉ ከሚገኘው ጥቅም አንጻር የዘርፉ ጉዞ የኋልዮሽ ነው። ለዚህ ደግሞ አብነት መሆን የሚችለው አሁናዊው ሁኔታ ነው፡፡
ከ20 የሚልቁ የስፖርት ማህበራት ባላት ሃገር በተለይ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ሲሆኑ፤ ሌሎች በውጤት እምብዛም የማይታወቁ ነገር ግን በተሳትፎ ደረጃ ሃገራቸውን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ስፖርቶች ተሳትፏቸው በእጅጉ ቀንሷል። የተገኙ ተሳትፎዎችም ሃገርን እንደመወከላቸው የሚያግዛቸውና የሚደግፋቸው በማጣታቸው ብዙ ርቀት መጋዝ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአንድ አህጉራዊ ውድድር ላይ ተካፋይ የነበረ የቴኳንዶ ብሄራዊ ቡድን በገንዘብ እጦት ምክንያት ውድድር ከማቋረጥ አልፎ በሄደበት ሃገር ኑሯቸውን ባያደረጉ መልካም ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውና ጉዳዩም በቀላሉ ተድበስብሶ ማለፉ በቅርቡ ነው የተሰማው። መሰል ሁኔታ እንዳይፈጠርባቸው ስጋት ያደረባቸውና ራሳቸውን ያልቻሉ የስፖርት ማህበራትም ዓለም አቀፍ ተሳትፏቸውን በመግታት በሃገር ውስጥ ውድድሮች ተገድበዋል። በመንግስታዊው አካል በተደጋጋሚ ለዚህ የሚነሳው ምክንያትም ሃገሪቷ ያሳለፈችውን እንዲሁም ያለችበትን አስቸጋሪ ወቅታዊ ሁኔታ ነው። ይህንንም የትኛውም ዜጋ ሊረዳው የሚችል ጉዳይ ቢሆንም ላልተሰሩት የቤት ስራዎች ሰበብ እንጂ አሳማኝ ነጥብ ግን ሊሆን አይችልም፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት አቅጣጫው ተዛብቷል የማለቴ ምክንያትም ይኸው ነው። ስፖርቱን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ ይበጃል የተባለው አቅጣጫ በስፖርት ፍኖተ ካርታው በግልጽ ይቀመጥ እንጂ ተግባራዊ ሳይሆን የአንድ ወጣት እድሜን አስቆጥሯል። አሁንም የስፖርት ማህበራት አደረጃጀት የጠራ እና ከመንግስት ድጎማ የተላቀቀ አይደለም።
ይህንን በኃላፊነት የመምራትና የመቆጣጠር ስራው የመንግስታዊው አካል ሆኖ ሳለ በየዓመቱ በሚበጅትላቸው ጥቂት ገንዘብ ከመወሰን አላላቀቃቸውም፤ ከውጤታማነት አንጻርም ክትትል አይደረግባቸውም። ይህ ሁኔታ ታዲያ አንድ ቡድን ለዓለም አቀፍ ውድድር የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገለት በኋላ የሃገርን አንገት የሚያስደፋ ተሳትፎ አድርጎ ቢመለስም እንኳን ተጠያቂ እስከማይሆንበት የሚዘልቅ ነው። ለዚህም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነበረውን ሁኔታ እና ከተሳትፎ መልስ የመንግስታዊው አካል ሚና የአሸማጋይነት እንጂ አጥፊዎችን ተጠያቂ አለማድረጉን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል።
ሌላው የሃገሪቷ ስፖርት ወደፊት የሚመራው ኮምፓስ አለመኖሩ በግልጽ አስረጂ የሆነ ጉዳይ በእግር ኳስ ስፖርት እየሆነ ያለው ነው። ተወዳጅ በሆነው ስፖርት ሃገር እስካሁን ድረስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ ማግኘት አልቻለችም። ይባስ ብሎ በሃገር ውስጥ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዳይካሄድ በመከልከሉ ምክንያት ወዲህ ጅምር ስታዲየሞችን ለመፈጸም ወዲያ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑ ውድድሮች ሲኖሩበት ለውሰት ሜዳዎች የውጪ ምንዛሬ ወጪ መንግስታዊው አካል ተወጥሯል። በዚህም እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ተነጥቆ ለዚህ ዓላማ ይውላል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የችግሩ መንስኤ ራሱ መንግስታዊው አካል ነው ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም ህዝባዊ የሆነውን ጉዳይ ለህዝብ ከመተውና አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በድጎማና ድጋፍ የስፖርት ማህበራትም ሆኑ ክለቦች ራሳቸውን እንዳይችሉ አለማምዶ እዚህ አድርሷቸዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአደራጃጀትም ሆነ በገንዘብ አቅም ትልቅ በሚባለው ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ‹‹ክለብ›› የሚለውን ስያሜ የሚያሟላ ቡድን የለም።
በሊጉ ከሚካፈሉ 16 ክለቦች ራሳቸውን የቻሉት ሁለቱ ሲሆኑ፤ የተቀሩት በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ ናቸው። በመሆኑም የራሳቸው የሆነ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ለመገንባት ቀርቶ የሚተዳደሩትም ከእነዚሁ አካላት በተገኘ ገቢ ነው። አጠቃላይ የእነዚህ ክለቦች ዓመታዊ ወጪ ሲሰላ ደግሞ 1ቢሊየን ብር ይደርሳል። ይኸውም በአፍሪካ ካሉ ሊጎች በጥቂቶች የተበለጠ መሆኑን በቅርብ የተሰራ አንድ ጥናት አመላክቷል።
‹‹ትበላው የላት ትከናነበው አማራት›› ይሉት ዓይነት ብሂል የብሄራዊ ስታዲየምን ግንባታ ለማጠናቀቅ የተጠየቀውን ገንዘብ ቸግሯት ከቻይና መንግስት ጋር ምክክር የተቀመጠች ሃገር፤ ራሳቸውን መቻል ሲገባቸው ከልጅነታቸው አንላቀቅም ላሉ ክለቦች በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በየዓመቱ ታወጣለች።
ከስታዲየሞች ጋር በተገናኘ በግል ባለሃብት የተገነባውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀው ዘመናዊው የወልዲያ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) መስፈርትን ለማሟላት የጎደሉትን ጥቂት ነገሮች አሟልቶ ችግሩን መቅረፍ የሚቻል ቢሆንም ይህ ሳይሆን በሃገሪቷ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጉዳት አስተናግዷል። አሁንም ቢሆን ከ1ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ስታዲየም የደረሱበትን ጉዳቶች በመጠገን እንዲሁም የጎደሉትን መስፈርቶች በማሟላት ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት ይቻላል፡፡
እንደ ሩጫ ውድድር ግልጽ መነሻ፣ መድረሻ እንዲሁም ርቀቱን የሚሸፍንበት አቅጣጫ ያለው አካል መንገዱን ሊስት አይችልም። ሩጫውን ለመፈጸምም በሚሮጥበት መም ላይ የተቀመጠለትን ምልክት ሲከተል፤ ለአሸናፊነትም ሆነ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ደግሞ የራሱን የሩጫ ዘዴ ተግባራዊ ያደርጋል።
ስፖርቱን የሚመራው አካልም ማወዳደር ብቻም ሳይሆን ራሱን የሩጫው አካል በማድረግ ከሌላው ዓለም ጋር ራሱን መመዘን ይኖርበታል። እንደ ኮምፓስ የተቀመጠለትን ፍኖተ ካርታ በመከተልና በማስተግበርም ስፖርት የሃገርን ስም በማስጠራት እንዲሁም አንገብጋቢ ችግሮች ያሉባትን ሃገር በጀትም ከመሻማት ይልቅ የገቢ ምንጭ ማድረግ ይቻላል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም