ሰላም ለአንድ ሃገርም ሆነ ማህበረሰብ ያለው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ወሳኝ ነው። ያለ ሰላም ምንም ሊታሰብ፤ ሊደረግ አይችልም። ስለ ነገዎች ሳይሆን ስለሚቀጥሉት ደቂቃዎች እንኳን አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው ሰላም በሚፈጥረው አስቻይ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው። ይህ እውነታ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከከፈልነው ተዘርዝሮ የማያልቅ ዋጋ አንጻር ፤ ለሰላም ያለን መሻት ከፍ ያለ ነው። ለዚህም ሁሌም ቢሆን ለሰላም ዋጋ ለመክፈል የተነቃቃ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች ባለቤቶች ነን። እንደ ሕዝብ ያሉን የቀደሙት ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የረጅም ዘመናት ታሪኮቻችንም ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው።
በየዘመኑ እንደ ሀገር የሚገዳደሩንን ችግሮች ተሻግሮ ለመሄድ እንደ ሕዝብ የተጓዝንባቸው መንገዶች ፣ ትናንቶችን ሳይሆን ነገዎችን ተስፋ አድርገው ፤ በሰላም መሰረት ላይ የተዋቀሩ፤ የሰላምን ትሩፋቶች ተሻግረው መመልከት የቻሉ ናቸው። ይህም እንደ ሕዝብ ያልተገቡ ተጨማሪ ዋጋዎችን እንዳንከፍል አድርጎናል። እንደ ሀገርና ሕዝብም ጸንተን እንድንቆም ረድቶናል።
ዛሬም ቢሆን እንደ ትናንቱ እንደሃገር እና ሕዝብ ጸንተን እንድንቀጥል ዋንኛ አቅም የሚሆነን ይሄው ስለ ሰላም ያለን የጸና መሻት እንደሚሆን ይታመናል። በተለይም ሰለማችንን በብዙ መልኩ የሚፈታተኑና ሰላማችንን የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርገው ለመጠቀም የሚሺ ኃይሎች አደባባዮችን በሞሉበት በዚህ ወቅት ስለ ሰላማችን ዘብ መቆም የሁላችንም ትልቁ ኃላፊነት ነው።
አሁን ያለንበት ወቅትና ወቅቱ ይዞት የመጣውን ሃገራዊ ፈተና አሸንፎ ለመሻገር የቀደሙት አባቶቻችን ተመሳሳይ የታሪክ ክስተቶችን በጽናት ማለፍ የቻሉበትን ማኅበራዊ ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የሰላም እሴቶቻችንን ከጣልንባቸው ስፍራዎች ልናነሳ፤ አቧራቸውን ልናራግፍ ይገባል። በእሴቶቹ ዙሪያ ያለ ያልተስተካከለ አተያይ ከአእምሯችን ልንፍቅ ይገባል።
እስካሁንም ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ያሉት ችግሮቻችን ፤ አሸንፎ መሄድ ያልቻልነው ለዛ የሚሆን ሃገራዊ አቅም ስላጣን ሳይሆን ፤ያለንን አቅም በአግባቡ ተረድተን ፤አቅማችንን የችግሮቻችን ዋነኛ የመፍትሄ አካል ማድረግ ስላልቻልን ነው። ባልተገባ መንገድ እና ምልከታ የጣልናቸውን ሃገራዊ አቅሞቻችንን ጎንበስ ብለን ለማንሳት የዘገየን በመሆናችን ነው።
የወቅቱ ሀገራዊ እውነታ ከሁሉም በላይ የሚጠይቀን በቀደሙት ዘመናት አባቶቻችንን ከክፉ ቀናት ያሻገሯቸውን ማኅበራዊ ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የሰላም እሴቶቻችንን ከጣልንበት አንስተን ካለንበት አስቸጋሪ ወቅት የመሻገሪያ አቅም፤ የቀጣይ ሰላማችን ዋነኛ መሰረት እንድናደርግ ነው። ይህን ለማድረግ አለመፍቀድ በነገዎቻችን ላይ ጽልመት የማልበስ ያህል የሚቆጠር ነው።
ለአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የማይመች ፤ለዚህ የሚሆን መደላድል የሌለው ነው ፤ ከዛ ይልቅ ለዘመናት ጥላ ሆነው ሲከተሉን ፤በመንገዳችን ሁሉ እንቅፋት እየደረደሩ መውደቃችንን በጽኑ ሲመኙ ለኖሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ምኞት ፤ ለሀገራችን በጎ ለማይመኙ የውስጥ ባንዳዎችም ፍላጎት ስኬት የተሻለ እድል የሚፈጥርላቸው ነው ።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር አሁን እንደሃገር መልካቸውን እየቀያየሩ እያጋጠሙን ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው ተሻግረን ፤የምንፈልጋትን ሰላማዊና የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ከስሜትና ከእልህ ወጥተን በእጃችን ያለውን ሀገራዊ ሰላም ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ልንጠብቀው፤ ልናሳድገውና የነገዎቻችን ተስፋ መሰረት ልናደርገው ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም