ለነቀምት ከተማ እድገት ማነቆ የሆኑ አመለ ካከቶችን፣ ከህዝቡ የሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎችን፣ እንዲሁም ከተማዋ አሁን ስላለችበት የሰላም ጉዳይና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ በሆኑ ሀሳቦች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከምስራቅ ወለጋ ዞን የነቀምት ከተማ ማዘጋጃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ቶሌራ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡– መሰረተ ልማቶችን ለማሟላትም ሆነ የከተማዋን ቱሪዝም ለማሳለጥ ሠላም ወሳኝ እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት የነቀምት ከተማ የሰላም ሁኔታ ምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
አቶ ደረጀ፡– በምስራቅ ወለጋ በተለይም በነቀምት ከተማ የሚወራውና የሚታየው ነገር አንድ አይደለም፡፡ ነቀምት ማለት እንደ ስሟ የሠላም አምባ ነች፡፡ ለሁሉም አመቺ የሆነች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኖርባት ከተማ ናት።
በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ማኅበረሰቦች ከሌላ አካባቢ የሚመጡትን ተቀብለው በማስተናገድ ሁሉም ባይተዋርነት ሳይሰማው እንደራሱ ቤት ቆጥሮ የሚኖርባት ናት፡፡ ለመሰረተ ልማትም ሆነ ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የምትሆን አካባቢ አይደለችም፡፡
ወለጋን እንዳታድግ የሚያደርጓት ሰፊ ተቀናቃኝ ቡድኖች በመኖራቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በምንም ሁኔታ ከህዝብ ጋር አይገናኝም፡፡ ህዝብና ሀሳብ የተራራቁ ናቸው፡፡ ወለጋን የፈጠራትና ወለጋ ውስጥ የኖረ ህዝብ የወለጋን እድገት የሚጠላ አይደለም፡፡ ሩቅ ሆኖ በመኖርና ቀረብ ብሎ በማየት ውስጥ የሚኖረው ግንዛቤ የተለያየ ነው።
በአሁኑ ወቅት ለኢንቨስትመንትም ለቱሪዝምም ምቹ ስለሆነች ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ መስራት ይችላሉ፡፡ የአካባቢው ህዝብም የሚመጣውን መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ለመቀበል ዝግጁ ነው፡፡
ትናንት የነበሩ አመራሮች ህዝብን ለማጋጨት የማጠላላት ሴራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ይህ ተሰብሮ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎችም ባለ ሥልጣናት በከተማዋ ተገኝተው ከህዝቡ ጋር መወያየት መቻላቸውና የአካባቢውን ሰው የአቀባበል ሥነ ስርዓት መመልከት አካባቢው ምን ያህል ሠላም የሰፈነበት መሆኑን ማሳያ ነው።
ወለጋ የጸጥታ ችግር አለባት ብለው የሚያወሩ ለወለጋ ጥሩ ነገር አስበው አይደለም፡፡ የእነዚህ አካላት ፍላጎትም የወለጋን እድገት ማቀጨጭ ነው፡፡ አሁን የደረስንበትን እድገት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ህዝቡ ተሳትፎ በማድረግ መታገል ይገባዋል፡፡ ወለጋ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር የተጀመረውን የመደመር ስሌት ማስቀጠል ይገባል፡ ፡ የመደማመጥና የመቻቻል ባህላችንን በማስቀጠል እንደ አጠቃላይ አገርን ማልማት ይጠበቅብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የህዝቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምን ያህል ተመልሰዋል?
አቶ ደረጀ፡– እንደሚታወቀው የህዝቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችና በመንግሥት በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ ተመጣጣኝ አይደለም።
በነቀምት ከተማ ትልልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ አልተገነቡም፡፡ በእርግጥ ከተማዋ ትናንት የነበራት ገጽታና ዛሬ ያላት ገጽታ አንድ አይደለም፡፡ ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ነው።
ህዝቡ ትናንት በየሰፈሩ የኮብል ስቶን ዝርጋታ ይጠይቅ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ የአስፓልት መንገድ ይሰራልኝ እያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍላጎትና አቅርቦት ጋር ያልተጣጣመ ነው፡፡ ይብዛም ይነስም አቅም በፈቀደ መጠን በተለይ በከተማዋ የሚነሱትን መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮብል ስቶንም ሆነ ሌሎች የመንገድ ዝርጋታዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከህዝቡ ጥያቄ ጋር ሲነጻጸር የተፈለገውን ያህል ተሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡– በመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ የህዝብ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
አቶ ደረጀ፡– የህዝብ ጥያቄ መምጣቱ በአሉታዊ መንገድ የሚታይ አይደለም፡፡ ጥያቄዎች በተነሱ ቁጥር በአመራር ደረጃ ያሉትን ለሥራ ያነሳሳል። በአሁኑ ወቅት በነቀምት ከተማ ውስጥ በክልል መንግሥትም ሆነ በከተማ ደረጃ የህዝብን ተሳትፎ መነሻ ያደረጉ የፕሮጀክት ግንባታዎች ተከናውነዋል። የህዝብ ተሳትፎ የሌለው ፕሮጀክት ተደራሽነት አይኖረውም።
የታለመለትን ግብም አይመታም፡፡ ለአብነት ያህል በከተማዋ ከተገነቡት መሠረተ ልማቶች አንዱ የወለጋ ስታዲየም ሲሆን፤ ይህም ከሌሎች ለየት የሚያደርገው መነሻው የህዝብ ተሳትፎ መሆኑ ነው።
ጥያቄውም የተነሳው ከህዝብ ነው።
እንዲህ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በመሀል እንቅፋት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ የህዝብ ቁርጠኝነት በመኖሩና በበጀት እጥረት ምክንያት የክልሉ መንግሥትም ጣልቃ ገብቶ ፍጻሜ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም ምን ያህል የህዝብ ተሳትፎ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች የከተማዋ አንኳር ችግር ምንድነው?
አቶ ደረጀ፡– በከተማው በስፋት ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ ሥራ አጥነት ዋነኛው ነው።
ብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ እየፈለሱ ነው፡፡ የሥራ አጥ መብዛት ደግሞ የጸጥታ ችግር እየሆነም ነው።
ይህ የሆነውም በከተማው ፋብሪካዎችና ሌሎች ሰፊ የሥራ ዕድሎች አለመኖራቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም ለአካባቢው ፀጥታ መደፍረስ ሥራ አጥነት ዋነኛ ምንክንያት ነበር፡፡ በክልሉ መንግስትም ሆነ በፌዴራል መንግስት ደረጃ ችግሮች በስፋት ታይተው በከተማዋ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲከናወኑ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ አሁንም ቢሆን በመንግስት ደረጃ ሰፊ ፕሮጀክቶች ታቅደዋል፡፡ ይህ ማለት በነቀምት ከተማ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ብዛትን ሊቀንስ እንደሚችል ይታመናል፡፡
ትላልቅ ፕሮጀክቶች ካልተተገበሩ በስተቀር በመንግሥት በጀት ብቻ የሥራ አጥነትን ችግር መቅረፍ አይቻልም፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ አቅሙን እየሸጠ ነው እየኖረ ያለው፡፡ ብዙዎች በሥራ እጦት ምክንያት በየጎዳናው ላይ በመው ጣት ሌላ ዝንባሌ አሳይተዋል፡፡ አሁንም ሰፋፊ ፕሮጀክቶችና ፋብሪካዎች የማይገነቡ ከሆነ ሁኔ ታው አስጊ ነው፡፡
በከተማዋ የህዝብ ጥያቄ የሥራ ማጣት ብቻ ሳይሆን ፍልሰቱም በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የቆዳ ስፋቷም እየተለጠጠ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ጉዳይም አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል፡፡ ሰው ሥራ ከሌለው ሀሳቡ ወደ ግጭት ያመራል።
ወደ ሥርቆትም ይገባል፡፡ ስርቆት ካለ ባለ ንብረት ዝም ብሎ ስለማይመለከተው ከፍተኛ ውጥረት ያጋጥማል፡፡ አላስፈላጊ ለሆኑ ጎጂ ሱሶች ይዳረጋል። ይህም ደረጃ በደረጃ ወደ ብጥብጥና ሁከት እንዲያመራ ያደርገዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው ራሱን ወደ ሥራ ካስገባ ግን አሉታዊ ነገሮችን ለማሰብ ጊዜ አይኖረውም።
ሰውና ሰውን የሚያጋጭ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ሥርቆት የሚያስገባውም የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈንም ሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሰው በሥራ ላይ መጠመድ ይኖርበታል፡፡ ራስን በሥራ ውስጥ ማሳለፍ ለጸብና ለግጭት ጊዜ እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ነቀምትም ሆነ በነቀምት ዙሪያ ለነበረው የፀጥታ ጉዳይ አብዛኛው ተስፋ ቆራጭና ተምሮ እድል ያላገኘ ወጣት ነው፡፡ በሥራ ተስፋ በመቁረጥ ወዳልተፈለገ ግጭት ውስጥ የመግባት ሁኔታ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ ብቻ ሳይሆን ባደጉ አገራት ላይ የሚስተዋል ነው፡፡
ይህ ሁሉ ከከተማዋ አቅም በላይ ነው፡፡ ያልተ ማረውም ሆነ የተማረው ኃይል የሚያነሳው ጥያቄ በዚህ ከተማ ውስጥ ፋብሪካ ይገንባ የሚል ነው። ፋብሪካ ከተቋቋመ ደግሞ ብዙ የሰው ኃይል ስለሚፈለግ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል። ራስን በሥራ የጠመደ ማኅበረሰብ ለማፍራትም የፋብሪካዎች መገንባት ሚና ቀላል አይደለም። በስርቆትና መሰል ወንጀሎች ላይ ለመሰማራት የሚሰራውን ቀመር ያጠፋል።
በዚህ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ችግር ሲከሰት ብቻ ካልሆነ በአብዛኛው አካባቢው በልማት እንደተጎዳ በመዘገብ ደረጃ ክፍተት አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ሥራ አጥነትን ለመቀነስና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በከተማ ደረጃ ምን ታቅዷል?
አቶ ደረጀ፡– በቅርቡ የገበያ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል፡፡ በቅርቡም አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ የሥራ ዕድልን ይፈጥራሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ ዙሪያ በተለይ በገበያ ማዕከል ላይ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚኖር ተስፋ ተደርጓል፡፡ በተቻለ አቅም ሥራ አጥ የሆኑት የሥራ ፈቃድ አውጥተው የሥራ ዕድሉ ተፈጥሮላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ተወዳድረው እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡አካባቢው ከለማ ህዝቡ አብሮ ኢኮኖሚውን ያሳድጋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በራሱ በቂ አቅም ስለሌለው መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግለትም እየተጠየቀ ነው፡፡ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ይህንን ተገንዝቦ በራሱ ተነሳሽነት የሥራ ዕድል ፈጥሮ እንዴት መስራት እንዳለበት ባለን አቅምና ኢኮኖሚ ገንዘብም ሆነ እውቀት አክለንበት ህዝቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አቅደን እየሰራን ነው፡፡ ለዚህም የህዝብ መድረክ በመፍጠር በየጊዜው ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለሠጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ደረጀ፡– እኔም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011
በአዲሱ ገረመው