ከለውጡ ዘመን ወዲህ መንግስት ሀገራዊ ስብራቶችን ለመጠገን ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። በተለያዩ ዘርፎች የፖሊሲ ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ ዘርፎችን በአግባቡ በመገምገም በተጠና መንገድ ሪፎርም ተግባራዊ አድርጓል፤ እያደረገም ነው። በዚህም እየተገኘ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጪ ሆኗል።
እነዚህ የሪፎርም ስራዎች ሀገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረችባቸውን ያለፉት ሁለት ዓመታት ተቋቁማ ማለፍ እንድትችል አድርገዋል፤ በተሞክሮ ደረጃም ካስገኙት ስኬት አንጻርም ለቀጣይ ሀገራዊ ጉዟችን ተስፋ ሰጪ ምልክት መሆን ችለዋል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያመላክቱት የለውጥ መንግስት ከቀደመው የፖለቲካ ስርአት የሚወርሳቸው ችግሮች ለለውጥ ጉዞው ስኬት ትልቅ ፈተና እንደሚሆኑበት ይታመናል፤ እነሱን ለመቅረፍ የሚሄድባቸው ስትራቴጂክ መንገዶች እና መንገዶቹ የሚገዙበት ጠንካራ ዲሲፕሊንም ሊያስመዘግብ ለሚችለው ስኬት ወሳኝ አቅሙ ናቸው።
ከዚህ አልፎ የለውጡ መንግስት ከቀደመው የፖለቲካ ስርአት የሚወርሳቸው ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች የሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ቀጣይ ጠንቅ እንዲሆኑ መቆመሪያ ካርድ አድርገው የሚሰሩ/ የሚሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ካሉ፤ ችግሩ አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ የለውጥ መነቃቃት የከፋ ፈተና ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው።
ይህ ደግሞ በኛ ተጨባጭ እውነታ የዕለት ተዕለት ክስተት ከሆነ ውሎ አድሯል። እነዚህ ኃይሎች መንግስትን የሚገዳደሩ አጀንዳዎችን በየወቅቱ በመፍጠርና በተሳሳተ ትርክት በሕዝብ ውስጥ በማሰራጨት፤ መንግስት ከጀመረው የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል ፤ መላው ህዝብ ለለውጡ የከፈለውን ዋጋ ትርጉም አልባ ለማድረግ ረጅም ርቀት ሄደዋል፤ እየሄዱም ነው።
መንደርና ሰፈርን፤ ቋንቋና ሃይማኖት መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ከመፍጠር ጀምሮ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ የተለያዩ ሀገራዊ ስብራቶችን ለመፍጠር ተግተዋል ፤ በዚህም ሀገርና ሕዝብን ያስከፈሉት ዋጋ ከፍያለ ነው። የፈጠሩትም ሀገራዊ የልብ ስብራት ገና አላገገመም።
ለዚህም በዲጅታል ሚዲያ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ጨምሮ፤ ራሳቸው ሳይነቁ የህዝብ አንቂ ነን በሚል በዘረኝነት መርገም በተያዙ ግለሰቦች እየተደገፉ ሀገራዊ የፖለቲካ መድረኩ፤ የዘመናዊ የፖለቲካ ልምምድ መድረክ እንዳይሆን እያደረጉ ነው።
ህዝባችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የጓጓለትን በውይይትና በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት የፖለቲካ ባህል እንዳይለማመድ፤ በዚህም ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዳይሸጋገር ዋነኛ ተግዳሮት ሆነዋል። ለዚህ ደግሞ በሐሰት ዘገባ፣ ግጭትን በመስበክ፤በሴራ ፖለቲካ አደባባይ የሞሉ ፖለቲከኞቻችንን ለአፍታ መታዘብ ፤ የፌስቡክ እና ትዊተር ገጾችን መመልከት በቂ ነው።
ይህ በአንድም ይሁን በሌላ የመንግስትን የለውጥ ጉዞ በመቀልበስ ሕዝባችንን ወደቀደመው የጥፋት የፖለቲካ አዙሪት ለመመለስ የሚደረግ ርብርብ በሀገሪቱ የነበሩ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን በፍጥነት ጠግኖ ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል።
የፖለቲካ ገበያ ነጋዴዎች መንግስትን ፋታ በመንሳት፤ ከጀመራቸው የለውጥ ስራዎች ለማደናቀፍ እያደረጉት ያለው ርብርብ መላው ህዝባችንን እያስከፈለ ያለው ሆነ ፤ ወደ ፊት ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከፍያለ ነው። ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ዜጋ እነዚህ ኃይሎች በሀገር ህልውና ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ በአግባቡ ሊረዳ ይገባል።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ በነዚህ ኃይሎች የተፈጠሩ ወይም ሊፈጠሩ በሚችሉ ሀገራዊ ስብራቶች የመጀመሪያ ተጠቂ በመሆኑ ከስሜታዊነት ወጥቶ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ፤ ሀገርና ህዝብን በሚያስቀድም በኃላፊነት መንገድ በማስተዋል ሊንቀሳቀስ ይገባል። እንደ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከእርሱ የሚጠበቀውም ይሄው ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም