ኬንያዊቷ አን ዋፉላ ስትራይክ ታዋቂ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪ ስትሆን የሕይወት ታሪኳን በመጽሐፍና በዘጋቢ ፊልም ለሕዝብ አቅርባለች። የዛሬ 47 ዓመት የሁለት ዓመት ህጻን እያለች በያዛት የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) ምክንያት አካል ጉዳተኛ የሆነችው አን በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋ ስኬትን እንደተጎናፀፈች ዛሬ በሙሉ ልብ ትናገራለች። እኛም የአንን ታሪክ ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም::እንደ አን ሁሉ በርካታ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች ብዙ ነገሮች ሳይሟሉላቸው ታግለው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ::ይህ አልሆን ያላቸው ደግሞ ከአካል ጉዳታቸው በተጨማሪ አስከፊ የሕይወት ውጣ ውረድን እየተጋፈጡ ይኖራሉ::
‘’እንደ ዕድል ሆኖ በቤተሰቤም ሆነ ባደግኩበት ሰፈር በአካል ጉዳተኛነቴ የደረሰብኝ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አልነበረም። እንዲያውም አካል ጉዳተኛ መሆኔንም አላውቀውም’’ የሚሉ ያሉትን ያህል በአካል ጉዳታቸው ምክንያት ቤተሰብ እንኳን ዞር ብሎ የማያያቸው ማህበረሰብ የረሳቸው በቤታቸው ቁጭ ብለው የማይነጋውን ቀን የሚናፍቁም ስለመኖራቸው አጠያያቂ አይደለም::
እውነት ነው አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስኮች እኩል መካተታቸውን እንዲሁም የሚሰሩት ስራዎች እነሱን ያማከሉ የሚመቹ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህም የሚሆነው ከሚሰሩ ግንባታዎች ጀምሮ በማንኛውም አገልግሎቶች ላይ ቢያንስ 50 በመቶ እንኳን ተጠቃሚ ሆነዋል ወይ ምቾት ተሰምቷቸው እየኖሩ ነወይ የሚለውን ማካተት ሲቻል ነው።
አካለ ጉዳተኝነት በየትኛውም ጊዜ ሊመጣ በማንም ላይ ሊደርስ የሚችል ነው:: እነዚህም ሰዎች ፈልገው ባላመጡት ችግር ብዙ ፈተናን ቢያዩም በተለይም ተደራራቢ የአካል ጉዳት (ማየት መስማት አለመቻል) ከሁሉም የከፋ ይሆናል::
እነዚህ ሰዎች በዓይናቸው አይተው ራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ አልያም በጆሯቸው ሰምተው መልስ መስጠት ስለማይሆንላቸው ለተደራራቢ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ሁሉ በእጥፍ የጨመረ ይሆናል::
በሌላ በኩልም ለመማርም ሆነ ለመስራት የተለየ እገዛን የሚፈልጉ በመሆኑ ያሰቡበት ሳይደርሱ መሆን የሚመኙትን ሳይሆኑ መቅረት ደግሞ እጣ ፋንታቸው እስሚመስል ድረስ በሁሉም ላይ የሚንጸባረቅ ነገር ነው:: እንደማንኛውም ሰው የሚያስፈልጋቸው ተሟልተውላቸው በነፃነት የመኖር መብታቸው መጠበቅ ያለበት ቢሆንም አሁን ላይ እራሳቸውም እንደሚገልጹት ማንም መታዘብ እንደሚችለው ብዙ ነገሮች እነሱን ማዕከል ያደረጉ አይደሉም::ይህ ደግሞ መፈጠራቸው ትርጉም እንዲያጣባቸው በራሳቸው እንዳይተማመኑ አልፎ ተርፎም ተስፋ ቆርጠው እንዲቀመጡ እያደረጋቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል::
ከውልደትም ይሁን ከጊዜ በኋላ አደጋው ሲከሰት ማግለል ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ማኅበራዊ ሕይወታቸው በተመቻቸ መንገድ መምራት እንዲችሉ ማድረግ ቢያስፈልግም ከቤታቸው ጀምሮ እስከ ማህበረሰቡ ብሎም ተቋማት ድረስ ያለው ግንዛቤ በጣም ውስን ከመሆኑም በላይ እነሱንም አንድ እርምጃ የሚያራምድ ሳይሆን ቆይቷል::
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ይህንን ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ምንም ዓይነት አስቻይ ሁኔታዎች ስለማያጋጥሟቸው በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ልጆቻቸውን አልያም ቤተሰቦቻቸውን መደበቅን እንደ አማራጭ ይወስዱታል::
እንደ ኢትዮጵያ እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ አካል ጉዳተኛ ለሆነ ሰው ብዙ አዳጋች ነገሮች አሉ። በተለይም ተደራራቢ የአካል ጉዳት ሲሆን ደግሞ ትምህርት ካለማግኘት አንስቶ እስከ ሥራው ዓለም ድረስ ብዙ የሚከብዱ ነገሮች ማስተናገድ የግድ ነው። ለተደራራቢ የአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚዘጋጁ የትምህርት ማሟያ መጻሕፍት አቅርቦትና የትምህርት ዕድል የማግኘት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በመሆኑ በትምህርታቸው ገፍተው የሚሄዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው ።
ብዙ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ይገለላሉ። በየቤቱ ተደብቀው የሚያድጉ በመሆናቸው ከማህበረሰቡ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ መድሎና መገለል ይደርስባቸዋል። ብዙ ሁኔታዎችም አልጋ በአልጋ አይሆኑላቸውም። እነዚህ ችግሮች ሁሉንም አካል ጉዳተኞችን የሚያጋጥሙ ቢሆኑም በእነዚህ ላይ ግን ይበረታሉ። ከቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም እንደውም እርባና እንደሌላቸው ይቆጠራሉ። እነዚህን ተግዳሮቶች ቢያልፉ እንኳን አካባቢያቸው ምቹ አይሆንላቸውም።
እነዚህ በተደራራቢ አካል ጉዳት ውስጥ ያሉ ሰዎች ለራሳችው ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከትም ይጨመርበታል። አቅማቸውን እንዲጠራጠሩ ይሆናሉ፤ በቂ መረጃ አለመኖሩም ችግር ሆኖ ይነሳል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲደመሩ ይህች ዓለም የአካል ጉዳት ለሌለባቸው ሰዎች ምቹ ሆና የተሠራች አስመስሏታል። ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በቂ ቦታ አለመሰጠቱ ኢ-ፍትሐዊ ነው በማለት ብዙዎች ያነሳሉ ከመረጃ አንስቶ እስከ መንገድና የሀገር ኢኮኖሚ ድረስ አካል ጉዳተኞችን የማካተት ሥራ መሰራት አለበትም ባይ ናቸው።
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ያሉበት ቦታ በበቂ ሁኔታ አይታወቅም ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መገለል ለማስረዳት አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላቸው ለማሳወቅ እንኳን የሚያሳፍራቸው ወላጆች አሉ። ይህ ግን እነሱም ላይ አያስፈርድም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላቸው ያሳውቁ ሰዎች ብዙ ችግር ሲደርስባቸው አይተዋልና መደበቃቸው ትክክል ነው።
በአንድ ወቅት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መስማትና ማየት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሮማን መስፍን አካል ጉዳተኞች እንደ አገር ችግራቸው ታይቶላቸዋል ለእነሱ መኖር ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸው በተለይም እሳቸውን ጨምሮ ተደራራቢ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከባድ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረው ነበር:: “አካታች ይባላል ነገር ግን ምንም ነገር የለም:: በየጊዜው ስልጠና ሰልጥኑ ይባላል ነግር ግን ለእኛ ስልጠና አይደለም የሚጠቅመን:: ይልቁንም እንደማንኛውም ማህበረሰብ የምንማርበት፣ የምንሰራበት፣ በቴክኖሎጂ ታግዘን ሰው የምንሆነውን ሁኔታ ነው ሊመቻችልን የሚገባው “ ሲሉም ተናግረዋል::
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን የሚወክልና ድምፃቸውን የሚሰማ እንደሌለ ይነሳል:: እነዚህን ወገኖች በማኅበራቸው አማካይነት የሚደግፉ ተቋሞች ቢበራከቱ ቢያንስ መሠረታዊ የክህሎት ሥልጠና ለሕፃናት መስጠት ይቻሉ ነበር:: አሁን የሚሰጠው አገልግሎት በአገሪቱ ካሉት ጉዳተኞች ቁጥር አንፃር አናሳ ነው::
ዓይነሥውርና መስማት የተሳናቸው ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ባለማወቅ ልጆቻቸውን መሠረታዊ የአኗኗር ክህሎት ሳያስተምሩ ይዘገያሉ:: ይህ ሊቀረፍ የሚችለው በአፋጣኝ ወደ ባለሙያ በመሄድ ክህሎቱን እንዲማሩ ሲደረጉ ነው:: ተደራራቢ የአካል ጉዳት የሚገባውን ያህል ሰፊ ትኩረት ስላላገኘ ለኅብረተሰቡ ስለ ችግሩ ውስብስብነት ማስረዳት ትንሽ ከበድ ይላል::
የቀለም ትምህርት ለማግኘት በከፊል መስማት ወይም በከፊል ማየት የሚችሉ የተሻለ ዕድል አላቸው:: ተደራራቢ አካል ጉዳት ያለባቸው እንደማንኛውም ሰው መኖር እንዲችሉ የማኅበረሰቡ ቀና አመለካከት የግድ መታከል አለበት::
ዓይነ ሥውራንና መስማት የተሳናቸው ተደራራቢ ጉዳታቸው ሕይወታቸውን ፈታኝ ያደርገዋል:: በዳሰሳ ወይም በሌላ መንገድ የመግባባት ልምዱ ስለሌለ አንዳንዴ መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ይማረራሉ:: በአደባባይ ወጥተው ከሚታዩ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ሰለባዎች ቁጥር ቤተሰቦቻቸው በየጓዳው የደበቋቸው እንደሚበልጡ መገመት ቀላል ነው:: ችግሩን የመቅረፍ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ግለሰብ እንደሆነም ግልጽ ነው:: አካል ጉዳት አማክሮ አይመጣም በማንም ላይ ሊደርስ ይችላል ነግ በኔ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው::
በእርግጥ ተደራራቢ አካል ጉዳተኝነት በዓለም አቀፍም በአገራችን ያለበት ደረጃ ቅር የሚያሰኝ ነው::በተለይም እንደ እኛ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በኩል የሚታየው ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው::በመሆኑም መንግስት በሚችለው ሁሉ ተደራራቢ አካል ጉዳተኞች አምራች ናቸው ለልማቱም አስፈላጊ ናቸው ብሎ በማመን በተለያዩ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ቢያመቻች::ማህበረሰቡም “ነግ በእኔ” በሚል ስሜት ከግንባታ ስራው ጀምሮ በተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች ውስጥ እነዚህን ሰዎች ማግለል ሳይሆን ማቀፍን ቢለምድ ተደጋግፈን እናድጋለን የእነሱም ችግር ሁሌ ችግር ሆኖ አይቀርም፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015